ከፍተኛ ሊግ | ዲላ ከተማ ወደ መሪነቱ ሲመለስ ሀላባ ወደ መሪዎቹ ተጠግቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተስተካካይ መርሀ ግብሮች መካሄዳቸውን ቀጥለው በእለተ እሁድ በሶስት የተለያዩ ሳምንታት ያልተደረጉ ጨዋታዎች ተስተናግደዋል። ጨዋታዎቹንም በዚህ መልኩ ተመልክተናቸዋል።

የምድብ ለ አንደኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች

(በአምሀ ተስፋዬ)

ዲላ ከተማ ሀምበሪቾን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የምድብ ለ መሪነቱን መልሶ ከደቡብ ፖሊስ ላይ ነጥቋል። ለረጅም ደቂቃዎች ያለ ግብ በዘለቀው ጨዋታ ከእረፍት መልስ ተደጋጋሚ ጫና የፈጠሩት ዲላዎች በ87ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ፍቃዱ ባስቆጠረው ጎል አሸንፈው ወጥተዋል።

የምድቡ መሪ የነበረው ደቡብ ፖሊስ ነጥብ ጥሎ ወደ ሁለተኛ ተንሸራቷል። መቂ ላይ በተደረገውና በቂ የፀጥታ ኃይል በሰዓቱ ባለመገኘታቸው  ዘግይቶ የጀመረው የመቂ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቀው።

በተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ከመሪዎቹ ቡድኖች ጋር ያለውን ልዩነት ማጥበብ የቻለው ሀላባ ከተማ ወደ ድሬዳዋ አምርቶ የውድድር አመቱን የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ድል በማስመዝገብ 2-0 አሸንፏል። በ44ኛው ደቂቃ አቦነህ ገነቱ ቀዳሚውን ግብ ሲያስቆጥር በ89ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ይልማ ተጨማሪውን አክሏል። 25 ነጥብ ላይ የደረሰው ሀላባ ከተማ በተስተካካይ ጨዋታ ሀምበሪቾን ካሸነፈ (በሀላባ 1-0 መሪነት 10 ደቂቃ ሲቀረው የተቋረጠ ጨዋታ ነበር።) የምድብ ለ መሪ በመሆን አንደኛውን ዙር ያጠናቅቃል።

ከፊቱ ሶስት ተስተካካይ ጨዋታዎች የሚቀሩት ወልቂጤ ከተማ በናሽናል ሴሜንት ላይ ግማሽ ደርዘን ጎሎች በማዝነብ 6-0 አሸንፏል። አክሊሉ ተፈራ በ6ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት የመጀመሪያውን ግብ ሲያስቆጥር በ17ኛው ደቂቃ ሐብታሙ ታደለ ፣ በ28ኛው ደቂቃ ብስራት ገበየው እንዲሁም በ45ኛው ደቂቃ በድጋሚ ሐብታሙ ታደለ አስቆጥረው ወደ መልበሻ ክፍል ያመሩ ሲሆን ከዕረፍት መልስ በ57ኛው ደቂቃ አክሊሉ ተፈራ እና ብሩክ በየነ በ88ኛው ደቂቃ ቀሪዎቹን ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል። በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የሜዳው ጨዋታዎቹ ወደ ሌላ ጊዜ ሲተላለፉበት የነበረው ወልቂጤ ከተማ ከ ነገሌ ቦረና (መጋቢት 28)፣ ከሀዲያ ሆሳዕና (ሚያዝያ 3)፣ ከድሬዳዋ ፖሊስ (ሚያዝያ 8) ጨዋታዎቹን ያደርጋል። ሶስቱንም ጨዋታዎች በድል ከተወጣም ከመሪዎቹ ተርታ የመሰለፍ እድል አለው።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከተማ ከ ነገሌ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል። በርከት ያለ የግብ ማግባት ዕድል አግኝቶ ያልተጠቀሙት ቡታጅራዎች በሁለተኛ ደቂቃ ላይ በመስቀሌ መንግስቱ የመጀመርያ ሙከራ ሲያደርጉ ኤፍሬም ቶማስ በ14ኛው፣ በ29ኛው እና በ44ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጎ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የነገሌ ከተማ ግብ ጠባቂ ሁሴን ዘላ ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል። ከዕረፍት መልስ የነገሌ ከተማ አጥቂ አብሌ ሁሴን በ47ኛው እና በ54ኛው ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሲችል ቡታጅራዎች በዚህኛውም አጋማሽ በርካታ ጠንካራ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው ተጠናቋል።

ሻሸመኔ ላይ ካፋ ቡናን የገጠመው ሻሸመኔ ከተማ 3-1 አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው ለጊዜውም ቢሆጅ ወጥቷል። በ12ኛው ደቂቃ ላይ ሣሙኤል ፋንታሁን ባስቆጠረው ጎል በሻሸመኔዎች መሪነት እረፍት ሲወጡ በ60ኛው ደቂቃ አብርሀም አለሙ እና በ81ኛው ደቂቃ ላይ ይድነቃቸው ብርሃኑ ቀሪዎቹን የሻሸመኔ ጎሎች አስቆጥረዋል።

የ15ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ 

(በቴዲ ታደሰ)

በ15ኛው ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ጅማ ላይ ሀዲያ ሆሳዕናን ያስተናገደው ጅማ አባ ቡና 1-1 አቻ ተለያይቶ ከመሪዎቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት የማጥበብ እድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች የጎላ እንቅስቃስሴ አልነበረም። ይልቁንም በጥላ ፎቅ እና ካታንጋ የሚገኙ ደጋፊዎች የቅብብል ህብ ዜማ ቀልብ የሚስብ ነበር። ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ ሀዲያዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲወስዱ አባቡናዎች ደግሞ የጎል አጋጣሚ በመፍጠር የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። በ11ኛው ደቂቃ ሱራፌል አወል ያሻገረው ኳስ ዳዊት ተፈራ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ አግዳሚን ታኮ ሲወጣበት በ19ኛው ሱራፌል ጌታቸው ከዳዊት ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው ኳስ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። በ27 እና 29ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከዳዊት ተፈራ የተነሱና ሀይደር ሸረፋ እና ሱራፌል አወል ያልተጠቀሙባቸው ሙከራዎችም በጅማ በኩል የሚያስቆጩ ነበሩ።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች የመጀመርያ የጎል አጋጣሚ ለመፍጠር ረጅም ደቂቃ የፈጀባቸው ሲሆን በ42ኛው ደቂቃ መልካሙ ፉንዱሬ የመታውን ኳስ ሒድር ሙስጠፋ ከጎሉ መስመር በእጁ በማውጣቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶ የፍፁም ቅጣት ምት ለሀዲያ ሆሳዕና ተሰጥቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ኄኖክ አርፊጮ ወደ ግብነት ለውጦ ሀዲያ ሆሳዕናን መሪ አድርጓል። የቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው ጅማ አባ ቡናዎች መረጋጋት ያልታየባቸው ሲሆን በ44ኛው መልካሙ ፉንዱሬ የሀዲያ ሆሳዕን መሪነት ከፍ ልታደርግ የምትችል ግልፅ የማግባት እድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከእረፍት መልስ የተለያዩ ሁነቶች ተከሰውበታል። ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ ጅማ አባ ቡና አቻ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ ሀዲያዎች በአንፃሩ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ በመከላከል እና ሰአት ማባከን ላይ ተጠምደዋል። በዚህም 5 የማስጠንቀቂያ ካርዶች ተመዘውባቸዋል። 61ኛው ደቂቃ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ብዙዓየሁ እንደሻው በመጠለፉ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኪዳኔ አሰፋ ሲያመክን በ85ኛው ደቂቃ ብዙዓየሁ እንደሻው በግል ጥረቱ ተከላካዮችን በማለፍ ጅማ አባቡናን አቻ አድርጓል። ከጎሉ በኋላ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ኳሱ ከውጪ በኩል መረቡን ነክቶ ተመልሷል እንጂ አልቆጠረም በሚል ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ምክንያት ለ15 ያህል ደቂቃዎች ጨዋታው ተቋርጦ ቆይቷል። ጨዋታው ከተቋረጠበተ ቀጥሎ ተጨማሪ ጎሎች ሳይተስተናገዱበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

ምድብ ሀ

በ14ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ሱሉልታ ላይ ሱሉልታ ከተማ ከ ኢኮስኮ ያደረጉት ጨዋታ በሱሉልታ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በ8ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተስፋዬ ሱሉልታን ቀዳሚ ሲያደርግ በ41ኛው ደቂቃ ላይ የኋላሸት ኢኮስኮን አቻ አድርጓል። ጨዋታው በዚህ ውጤት ሊጠናቀቅ ቢቃረብም አምበሉ ቶሎሳ ንጉሴ በ89ኛው ደቂቃ ኳስና መረብ አገናኝቶ ሱሉልታን ሶስት ነጥቦች አስጨብጧል።

የከፍተኛ ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታዎች በቀጣዮቹ ቀናት የሚቀጥሉ ሲሆን ዛሬ ረፋድ 4:00 ላይ በአአ ስታድየም አአ ከተማ ከባህርዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ትልቅ ግምት ተሰጥቶታል።


ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *