የዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር በወልዲያው ጨዋታ ዙርያ መግለጫ አወጣ

በወልዲያ እና በፋሲል ከተማ ጨዋታ ላይ የተፈጠረውን አሳዛኝ ድርጊት አስመልክቶ የኢትዮዽያ ዳኞች እና ታዛቢዎች ሙያ ማህበር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። 

ማህበሩ ያወጣው መግለጫ ዋና ሀሳብ የሚከተለውን ይመስላል።

” ትላንት በወልዲያ እና በፋሲል ከተማ መካከል በተደረገው የ19ኛው ሳምንት የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ 89ኛው ደቂቃ ላይ የሜዳውን አጥር ጥሰው የገቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኞች በመደብደብ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል። የእለቱ ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ ህክምና ተደርጎላቸው ከሆስፒታል የወጡ ሲሆን ረዳት ዳኛው ሙስጠፋ መኪ ግን በደረሰባቸው ከፍተኛ ጉዳት በወልዲያ አጠቃላይ ሆስፒታል ከፍተኛ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛሉ። ይህ ሌሎች የጨዋታ አመራሮች እና የእለቱ ኮሚሽነር ከቦታው አረጋግጠውልናል።

” ይህ ጉዳይ በትላንትናው ዕለት ብቻ ሳይሆን አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰቱ ቆይቷል። በመሆኑም በተፈጠረው ጉዳት ማህበራችን የተሰማውን ከፍተኛ ሀዘን እየገለፀ በቀጣይ የጨዋታው አመራሮች በሚያቀርቡት ሪፖርት መሰረት የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህግና ደንቡን ተከትሎ እርምጃ እንዲወስድ ማህበሩ በፅኑ ይጠይቃል።

” ፌዴሬሽኑ አስተማሪ ውሳኔ የማይሰጥ ከሆነ ግን ማህበሩ ከተቋቋመበት አላማ አንዱ የዳኞችን መብት ማስጠበቅ ስለሆነ ወደፊት የራሱን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እናሳውቃለን ። ”