ቡሩንዲ 2018 | ቀይ ቀበሮዎቹ ለነገው የመክፈቻ ጨዋታ ዝግጁ ሆነዋል

በቡሩንዲ አስተናጋጅነት ዛሬ በተጀምረው የሴካፋ ከ17 አመት በታች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የምድቡ የመጀመርያ ጨዋታ ነገ ከማድረጉ አስቀድሞ ዛሬ የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል።

ረቡዕ ረፋድ ላይ 27 የሉዑካን ቡድን አባላትን በመያዝ ወደ ስፍራው ያቀናው ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ቡጁምቡራ ከተማ ከደረሰ በኋላ የመጀመርያ ጨዋታውን ወደሚያደርግበት ኒጎዚ ከተማ የ2፡35 የመኪና ላይ ጉዞ በማድረግ የገባ ሲሆን ያለፉትን ሦስት ቀናት ለጨዋታው በቂ ዝግጅት ሲያደርጉ በመቆየት ዛሬ ጠዋት ነገ በሚጫወትበት ስቴዲዮም የመጨረሻ ልምምድ አከናውኗል። ቀለል ያሉ ከኳስ ጋር መሰረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች የልምምድ አካላቸው ነበረ ሲሆን ሁሉም ተጨዋቾች ለነገው ጨዋታ በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ሰምተናል።

በልምምዱ ወቅት ዝናብ ያጋጠመ ቢሆንም ሜዳው ሰው ሰራሽ በመሆኑ ችግሩ የጎላ እንዳልሆነ እንዲሁም ከጨዋታው በፊት ባሉት ጊዜያት ያሉትን ሁኔታዎች ማወቁና ልምምድ ማድረግ መቻሉ የተሻለ ዝግጅት ለማድረግ ጥሩ እድል እንደሚፈጥር እና ለነገው  ጨዋታ ቡድኑ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ዋና አሰልጣንኙ ተመስገን ዳና ተናግረዋል።

ዛሬ የተጀመረው የሴካፋ ከ17 አመት በታች ውድድር በመክፈቻው ኬንያ አስተናጋጇ ቡሩንዲን 4-0 ረታለች። ኢትዮጵያ ደግሞ ነገ 10:30 ላይ የመጀመርያ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዋን ከሶማሊያ ጋር 5ሺህ ተመልካች በሚይዘው እና በሰውሰራሽ ሜዳ በሆነው ኒጎዚ ስታድየም ታደርጋለች።

ከስፍራው ሆና መረጃውን በማድረስ የተባበረችን የፌዴሬሽኑ ህዝብ ግኑኝነት ሰላማዊት ፈቅይበሉን እናመሰግናለን ።