ቡሩንዲ 2018 ፡ ኢትዮጵያ ሶማልያን በማሸነፍ ውድድሩን በድል ጀምራለች

በቡሩንዲ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የሴካፋ ከ17 አመት ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆነው የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ የምድብ ጨዋታውን ከሶማሊያ ጋር አድርጎ በመስፍን ታፈሰ ሐት-ትሪክ 3 – 1 በማሸነፍ በድል ጀምሯል ።

 

ሶማሊያዎች በመልሶ ማጥቃት እና በቆሙ ኳሶች የመጀመርያዎቹን 15 ደቂቃዎች ብልጫ በመውሰድ የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድንን መፈተን ችለው የነበረ ቢሆንም በሒደት ኳሱን ይዞ ተቆጣጥሮ በመጫወት ወደ ጥሩ እንቅስቃሴ የገቡት ቀይ ቀበሮዎች መስፍን ታፈሰ ከሶማሊያ ተከላካዮች መሀል አፈትልኮ በመውጣት ባስቆጠረው ጎል አማካኝነት ቀዳሚ መሆን ችለዋል፡፡ ሆኖም ሶማሊያዎች አቻ የሚያደርጋቸውን ጎል አስቆጥረው 1 – 1 በሆነ በአቻ ውጤት እረፍት ወተዋል ።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያዎች ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን ከመስመር የተሻገረን ኳስ መስፍን ታፈሰ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ኢትዮዽያ 2 – 1 መምራት ቻለች ። በመጀመርያው ኢንተርናሽናል ጨዋታው ጎሎችን ማስቆጠር የቻለው እና ከ17 አመት በታች የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በሀዋሳ ከተማ ማልያ በ6 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው ተስፈኛው አጥቂ መስፍን ታፈሰ ከ16:50 ውጭ አስገራሚ 3ኛ ጎል በማስቆጠር በጨዋታው ሐት-ትሪክ መስራት ሲችል ቀይ ቀበሮዎቹም የመጀመርያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን 3 – 1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የማለፍ ዕድላቸውን አስፍተው ወጥተዋል ።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ተመስገን ዳና እንዲህ ብሏል፡፡ ” ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ የወሰዱብን የብልጫ መንገድ በመዝጋት ኳሱን ተቆጣጥረን በመጫወታችን ውጤቱን ይዘን አሸንፈን ወጥተናል ። በቀጣይ የምድቡ ጠንካራ ቡድን ኬንያን እንገጥማለን፡፡ በጣም የተደራጀ ቡድን ነው፡፡ የዛሬን ጨዋታ ማሸነፋችን ግን መልካም ነው ። ማክሰኞ ከዚህ ጨዋታ በበለጠ ጥንቃቄ አድርገን እንቀርባለን፡፡ ”

 

ትላንት በመክፈቻው ጨዋታ ኬንያ አስተናጋጇ ቡሩንዲን 4 – 0 በማሸነፍ ምድቡን በአንደኝነት ስትመራ ኢትዮዽያ ዛሬ ማሸነፏን ተከትሎ ምድቡን በሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ትከተላለች ። የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ቡድን ማክሰኞ ከኬንያ ጋር ወሳኝ የሆነውን የምድብ ጨዋታ የሚያደርግ ይሆናል ።