በሶከር ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የወሩ ምርጦች (መጋቢት-ሚያዝያ)

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ የውድድር ዘመን አጋማሽ ከተጀመረ የ4 ሳምንታት ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እንደተለመደው በመጋቢት እና በሚያዝያ ወር መጀመርያ የተካሄዱትን 4 ሳምንታት ጨዋታዎች መሰረት ባደረገ መልኩ የወሩ ምርጦችን ተመልክታለች፡፡


ዳንኤል አጃዬ (ጅማ አባ ጅፋር)

የጅማ አባ ጅፋሩ ጋናዊ ግብ ጠባቂ ዳግም ወደ ክለቡ ከተመለሰ በኃላ የተረጋጋ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሶስቱ ግብ ሳይቆጠርበት እንዲወጣም የግብ ጠባቂው ሚና የጎላ ነበር።


ኃይሌ ገብረትንሳይ (ኢትዮጵያ ቡና)

የቀድሞው የመስመር ተከላካዮቹን ካጣ በኃላ በቦታው ሁነኛ ሰው ማግኘት ተቸግሮ የነበረው ኢትዮጵያ ቡና በኃይሌ ጥያቄው የተመለሰለት ይመስላል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች በቀኝ መስመር ተከላካይነት በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የተካተተው ኃይሌ ካሳየው ወጥ አቋም ባለፈ አንድ ግብ የሆነ ኳስ አመቻችቶ አቀብሏል።


አዳማ ሲሶኮ (ጅማ አባ ጅፋር)

በሁለተኛው ዙር ጥሩ የመከላከል ሪከርድ ባስመዘገበው እና አንድ ግብ ብቻ በተቆጠረበት የጅማ አባ ጅፋር የኃላ ክፍል ውስጥ አዳማ ሲሶኮ ወጥ አገልግሎት አበርክቷል። ተጨዋቹ ከተለያዩ አጣማሪዎች ጋር በመሀል ተከላካይነት ቦታ ላይ ቢሰለፍም እርሱ ግን በወጥነት የቡድኑ የኃላ ደጀን በመሆን ወሩን አገባዷል።


አንተነህ ተስፋዬ (ድሬዳዋ ከተማ)

ድሬደዋ ከተማ አሁንም ከባድ ከሆነው የውድድር አመቱ ባያገግምም መጠነኛ መሻሻል አሳይቷል። በተለይ በመከላከሉ ረገድ ቡድኑ በአራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ነበር መረቡ የተደፈረው። በዚህ ሂደት ውስጥም የአምናው የሲዳማ ከተማ የመሀል ተከላካይ አንተነህ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ብዙሀንን ያስማማል።


መሀሪ መና (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

በቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር የግራው ቦታ ላይ እምብዛም የመሰለፍ ዕድል ሳያገኝ የቆየው መሀሪ ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሌሎች ክለቦች ካሉ የቦታው ተሰላፊዎች የተሻለ እንቅስቃሴን አሳይቷል። ከመከላከሉ ባለፈም ተጨዋቹ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የነበረው ተአሳትፎ ተሻሽሎ ታይቷል።


አማኑኤል ዮሀንስ (ኢትዮጵያ ቡና)

በውድድር አመቱ ከአራት በላይ የሆኑ ተጨዋቾችበተፈራረቁበት የኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ አማካይ ሚና ላይ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ልባቸው ከሀሳብ ያረፈ ይመስላል። በተከታታይ በቦታው እንዲሰለፍ ዕድል የሰጡት አማኑኤል ዮሀንስ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ እና የተጋጣሚ ፈጣሪ አማካዮችን ነፃነት በማሳጣት ትልቅ ሚና እየተወጣ ይገኛል።


ሙሉዓለም ረጋሳ (ሀዋሳ ከተማ)

የአማካይ ክፍል እንቅስቃሴን ፍጥነት የሚቆጣጠር እና የማጥቃት ፍሰቱን የሚያመጣጥን ልምድ ያለው አማካይ ቢያስፈልግ ከአንጋፋው ሙሉአለም ረጋሳ በላይ ተጠቃሽ አይገኝም። ተጨዋቹ በአራቱ ጨዋታዎች ከዚህ የግል ብቃቱ በመነሳት ለሀዋሳ ወሳኝ ተጨዋች መሆን ሲችል በጅማ አባ ጅፋር ላይ ድል ያስገኘችውን ብቸኛ ግብም ማስቆጠሩ ይታወሳል።


ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን (ሀዋሳ ከተማ)

ሀዋሳ ከተማ ደደቢትን 1-0 ሲያሸንፍ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ፍቅረየሱስ በመስመር አጥቂነት ክለቡን እያገለገለ ይገኛል። ታታሪ መሆኑና ብዙ የሜዳ ክፍል ሸፍኖ መጫወቱ ደግሞ ጥሩ የመከላከል ተሳትፎ እንዲኖረው እና የቡድኑ የወገብ በላይ እንቅስቃሴም ጉልበት የተላበሰ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል።


ሳሙኤል ሳኑሚ (ኢትዮጵያ ቡና)

በመጀመሪያው ዙር ኢትዮጵያ ቡና አንደኛው ደካማ ጎኑ የነበረው ከአጥቂ መስመሩ ግቦችን አለማግኘቱ ነበር። ሆኖም ያሳለፍነውን ወር በእንቅስቃሴው ተሻሽሎ የታየው ሳሙኤል ሳኑሚ ከአማካይ ክፍሉ ጋር ከፈጠረው መግባባት ባለፈ ሁለት ግቦችን ማስቆጠርም ችሏል።


ኦኪኪ አፎላቢ (ጅማ አባ ጅፋር – የወሩ ኮከብ ተጫዋች)

የሊጉን ከፍተኛ ግብ አግቢነት እየመራ የሚገኝፕው ኦኪኪ ለአባ ጅፋር የዋንጫ ተፎካካሪነት አሁንም ወሳኝ ተጨዋች መሆኑን ያስመሰከረበትን ወር አሳልፏል። ቡድኑ ካሳካቸው ሰባት ነጥቦችም ስድስቱን ያስገኙት ሁለቱ የኦኪኪ አፎላቢ ግቦች ነበሩ።


ኣሜ መሀመድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

የአምናውን የጅማ አባ ቡና አቅም በቅዱስ ጊዮርጊስ መድገም ተስኖት እና ጉዳትም አጋጥሞት የነበረው አሜ በሁለተኛው ዙር ዳግም የተወለደ መስሏል። አሜ በሶስት ጨዋታዎች ሶስት ግቦችን አስቆጥሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መሻሻል ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል።


የወሩ ኮከብ ተጫዋች ፡ ኦኪኪ አፎላቢ (ጅማ አባ ጅፋር)

የወሩ ኮከብ አሰልጣኝ ፡ ዲዲዬ ጎሜስ (ኢትዮጵያ ቡና)

የውድድር አመቱ ከጀመረ በኃላ ቡድኑን የተረከቡት ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ነገሮችን ለማስተካከል ጊዜ ወስዶባቸዋል። ምንም እንኳን በመጨረሻ በአርባምንጭ ቢሸነፉም በሁለተኛው ዙርም ከ13ኛው ሳምንት ጀምሮ የዘለቀውን የቡድናቸውን ከሽንፈት የራቀ ቆይታ በሶስት ተከታታይ ድሎች ማስቀጠል ችለው ነበር። ይህ በመሆኑም ኢትዮጵያ ቡና በሰንጠረዡ አጋማሽ ከነበረው የረጅም ጊዜ ቆይታ በኃላ ወደ ዋንጫ ተፎካካሪነት መምጣት ችሏል