ሪፖርት | ውጤታማ ቅያሪዎች ለኢትዮጵያ ቡና ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አስገኝተዋል 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት የአዲስ አበባ ስታድየም ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡናን ከወልዋሎ ዓ.ዩ ጋር አጋናኝቶ ቡና ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አሸንፎ መውጣት ችሏል። በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይረው የገቡት ሶስቱ ተጫዋቾችም በጎሎቹ ላይ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ወደ አርባምንጭ ተጉዞ 2 – 0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከመጣው ስብስቡ ውስጥ ኤፍሬም ወንድወሰን ፣ ክሪዚስቶም ንታንቢ እና አቡበከር ነስሩን በማሳረፍ በምትካቸው ትግስቱ አበራ ፣ ወንድይፍራው ጌታሁን እና ኤልያስ ማሞን ለዛሬው ጨዋታ ሲመርጥ በአንፃሩ ወልዋሎ በሜዳው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ግብጠባቂው ዮሐንስ ሽኩር  ፣ ኤፍሬም ጌታቸው እና ሙሉአለም ጥላሁንን በዛሬው ጨዋታ ላይ በመቀየር ለበረከት አማረ ፣ ብርሃኑ አሻሞ እና ማናዬ ፋንቱን የመሰለፍ ዕድል ሰጥቷል።

ከጨዋታው አስቀድሞ በመጀመርያው ዙር አዲግራት ላይ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ላይ የወልዋሎ የክለብ አመራሮች እና ደጋፊዎች በፍፁም ኢትዮጵያዊ ባህል እና መስተንግዶ በመቀበል እና በመሸኘት ላደረጉት መልካም ተግባር የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር አፀፋውን በምስጋ እና ስጦታ መልሷል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት በተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ውስጥ ጥንቃቄ የተሞላባቸው ፣ ባልተደራጀ  የጨዋታ እንቅስቃሴ ኳሶች ከሁለት እና ሦስት ቅብብሎ በላይ መዝለቅ ይልቻሉባቸው ነበሩ። ምንም እንኳን ንፁህ የግብ ዕድል መፍጠር ባይችሉም ወደ ፊት በመሄድ ረገድ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። በ18ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን የግብ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ኤልያስ ማሞ ከመዓዘን ምት ያሻማውን ቶማስ ስምረቱ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ እና በረከት ተሰማ ተረባርበው ያወጡበት ቅፅበት ነበር።  በጥብቅ መከላከልን በመምረጥ በጥንቃቄ መጫወት የፈለጉት እንግዶቹ ወልዋሎዎች ምንም አይነት ጎል እንዳይስተናገድባቸው በመከላከሉ ብቻ ከመጠመድ ባለፈ ኳሱን በማዘግየት ጭምርም የግብ ክልላቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሞክረዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት በተከላካዮች እየከሸፈባቸው በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ሦስት የማዕዘን ምቶች ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ብልጫ ተወስዶባቸው የነበሩት ወልዋሎዎች ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ ተነቃቅተው በመልሶ ማጥቃት  በአጥቂዎቹ ፕሪንስ እና ሪችሞንድ አዶንጎ አማካኝነት የኢትዮዽያ ቡናን መረብ ለመፈተሽ የሚያደርጉት ጥረት መልካም የነበረ ቢሆንም ያን ያህል የጎላ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ከቅጣት ምት ተሻግሮ ግብ ጠባቂው ሀሪሰን ያወጣው ኳስ ለወልዋሎ የመጀመርያ ሙከራ ሲሆን 43ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎ አጥቂ ሪችሞንድ አዶንጎ ጉልበቱን ተጠቅሞ በሰውነቱ በመሸፈን ሳይታሰብ ከሳጥን ውጭ  በቮላ የመታው ኳስ የግቡን ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚ ግን ለቡድኑ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር ። የመጀመሪያው አጋማሽም በዚህ መልኩ በቁጥር የበረከቱ ጠንካራ የጎል ሙከራዎች ሳንመለከትበት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ የነበረው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ብዙ ድራማዊ ትዕይንት አስመልክቶን ተጠናቋል። እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ተመሳሳይ የመከላከል አጨዋወትን መከተል ምርጫቸው አድርገው የገቡት ወልዋሎዎች በመልሶ ማጥቃት የሚፈጥሩት አደጋ ተሳክቶላቸው በ52ኛው ደቂቃ ከቀኝ ከመስመር ቅጣት ምት አፈወርቅ ያሻገረውን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ ወደ ግብ መትቶ ሀሪሰን እንደምንም ሲያወጣው የተፋውን ለኳሷ ቅርበት የነበረው በረከት ተሰማ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ በማድረግ በስታድየም ውስጥ የነበሩትን በርካታ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎችን አስደንግጧል።

ከዚህች ጎል መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሙሉ ኃይላቸው ተጭነው በመጫወት ጎል ፍለጋ ጥረት  በሚያደርጉበት ጊዜ በወልዋሎ በኩል ተቀይሮ እስከወጣበት ድረስ የቡናን ተከላካዮች ሲያስቸግራቸው ያመሸው አጥቂው ሪችሞንድ በ56ኛው ደቂቃ ከርቀት የተጣለለትን ኳስ ወደ ፊት እየገፋ ሲሄድ ወንድይፍው ጌታሁን ጎትቶ በማስቀረቱ የዕለቱ ዳኛ በላይ ታደሰ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ አስወግደውታል። በዚህ ሰአት ነበር አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የተካላካይ ስፋራቸውን ያጠናክራሉ  ተብሎ ሲጠበቅ ተከላካዩ ኃይሌ ገ/ትንሳኤን በማስወጣት አጥቂው ባፕቲስቴ ፋዬን በመቀየር አስገራሚ ውሳኔ የወሰኑት። የተቀሩት 34 ደቂቃዎች ጎል ፍለጋ የተጨዋች ለውጥ በማድረግ የአጥቂ ቁጥራቸውን በማብዛት ተጭነው የተጫወቱን ቡናዎች ሳሙኤል ሳኑሚ በግሉ ከሚያደርገው ጥረት ውጭ ተደራጅቶ በተጠና ሁኔታ ጎል ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ ያልነበረ ሲሆን የወልዋሎ ተጨዋቾች በተደጋጋሚ በመውደቅ ሰአት ለማባከን የሚያደርጉትን ጥረት ተከትሎ የዕለቱ ዳኛ ለሦስት ተጨዋቾች የማስጠንቀቂያ ካርድ ለመስጠት ተገደው ነበር።

የጨዋታው ጊዜ በገፋ ቁጥር ውጥረት በተሞላበት ሁኔታ ቀጥሎ 87ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከግራ መስመር የጣለውን ኳስ የወልዋሎ ተከላካዮችን አልፎ እግሩ ስር የገባውን ኳስ አስቻለው ግርማ መሬት ለመሬት አክሮ በመምታት ወደ ጎልነት ቀይሮ ቡናዎችን አቻ ማድረግ ችሏል። የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቆ 8 ደቂቃ በተጨመረበት ጊዜ ውስጥ ደግሞ 90+5ኛው ደቂቃ ላይ ከመሀል ሜዳ መስዑድ መሐመድ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ሌላው ተቀይሮ የገባው ቁመተ ረጅሙ ባፕቲስቴ ፋዬ በግንባሩ ገጭቶ ወልዋሎ መረብ ላይ በማሳረፍ ስታድየሙን ወደር ወደሌለው የደስታ ድባብ ቀይሮታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

የአሰልጣኝ አስተያየት 

ዲዲዬ ጎሜስ – ኢትዮጵያ ቡና

በውጤቱ እና በኢትዮጵያ ቡና በደጋፊዎች በጣም ተደስቻለው። ከመመራት በመነሳት ትልቅ ትግል አድርገን ፣ በራስ መተማመን ጥረት አድርገን አሸንፈን ወጥተናል። በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ የመጫወቻ ነፃ ቦታ መፍጠር አልቻልንም ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ለማድረግ ጥረት አድርገናል ፣ እግርኳስ ፍላጎት እና ጥረት ይፈልጋል። ይህን አድርገን ከኋላ ተነስተን አሸንፈን ወጥተናል ፤ በጣም ደስ ብሎኛል ።

ፀጋዬ ኪ/ማርያም – ወልዋሎ

ዛሬ የተጋጠምነው በኢትዮጵያ እግርኳስ በርካታ ደጋፊ ያለውና ጥሩ ኳስ ከሚጫወት ቡድን ጋር ነው። የእኛ ቡድን እንደምታውቋቸው ውስን ተጫዋቾች ካልሆኑ ሌሎች ልምድ የላቸውም። እንደዛሬ የጨዋታ እንቅስቃሴያችን ሦስት ነጥብ ማጣት አልነበረብንም። እግርኳስ በባህሪው ጨካኝ ስለሆነ በዕድል መልክ ሦስት ነጥብ ተወስዶብናል።