አሰልጣኝ ስዩም አባተ ዳግመኛ ሆስፒታል ገብተዋል

አሰልጣኝ ስዩም አባተ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ከወራት በፊት ሆስፒታል በመግባት ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው  የጤናው ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ ወደ ቤታቸው በመመለስ መቻላቸው ይታወሳል። ሆኖም በትላትናው ዕለት ዳግመኛ ህመማቸው በማገርሸቱ ቀድሞ ህክምናቸውን ወደተከታተሉበት ታዝማ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአልጋ ቁጥር 215 ተኝተው ይገኛሉ።

የአሰልጣኙ ህመም አይነት የተለያየ መሆኑ የህክምናውን ሂደት አስቸጋሪ እያደረገው እየተገለፀ ሲሆን የሳንባ ህመም ሆስፒታል እንዲገቡ ዋንኛ ምክንያት መሆኑን ወንድማቸው አሰልጣኝ ሰለሞን አባተ ለሶከር ኢትዮዽያ ተናግረዋል። “አሁን የጤንነት ሁኔታው ምንም አይልም፤ ደህና ነው። ትንሽ የሳንባው ሁኔታ ወደ ሆስፒታል እንዲገባ አድርጎታል።” ብለዋል ።