ክለቦች የአአ ስታድየም ገቢ አልተከፈለንም ሲሉ በፌዴሬሽኑ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል

የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ2009 የውድድር አመት አጋማሽ አንስቶ በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄዱ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች የአዲስ አበባ ክለቦች ከተመልካች ገቢ በክፍፍል ማግኘት የሚገባቸውን ገንዘብ እስካሁን አልከፈለም በማለት ክለቦቹ ለፌደሬሽኑ ጥያቄ አቅርበዋል። 

ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከ2009 የውድድር አመት አጋማሽ አንስቶ በአዲስ ስታድየም በተደረጉ ጨዋታዎች የተገኘውን ገቢ በሜዳው ለሚጠቀሙ ክለቦች አለማከፋፈሉ የተገለፀ ሲሆን የክፍያው በፍጥነት አለመፈፀምን ተከትሎ አንዳንድ ክለቦች ለተጨዋቾቻቸው ወርሃዊ ደሞዝ ለመክፈል እንደተቸገሩ ሰምተናል። ይህን የክለቦቹን ጥያቄ ይዘን ለፌዴሬሽኑ ባቀረብነው ጥያቄ መሰረት ባገኘነው ምላሽ የተወሰኑ ክፍያዎች ለክለቦቹ መከፈሉን ገልፆ የሚቀሩ ክፍያዎችን ከፋይናንስ ክፍሉ ጋር በመነጋገር በቅርቡ ክፍያው ተከፍሎ ይጠናቀቃል ተብሏል።

ከፍተኛ የፋይናስ እጥረት እንዳጋጠመው እየተነገረ የሚገኘው ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ ድርጅቶች ተከፍሎ ያልተጠናቀቀ እዳ ጭምር እንዳለበት ተሰምቷል።