የአሰልጣኞች ገጽ – ሰውነት ቢሻው [ክፍል 2]


የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን። የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውን ቃለመጠይቅ በክፍል አንድ ይዘን መቅረባችን ይታወሳል።

የዛሬው የክፍል ሁለት መሰናዷችን ደግሞ ስለ አሰልጣኝነት መርሀቸው፣ አሰልጣኝነት እና ተያያዥ ሃሳቦች ላይ ትኩረት አድርጓል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


የቡድን ስነልቦናዊ ጥንካሬ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እንደምታተኩር ይታወቃል፡፡ በእግርኳስ ስኬታማነት ላይ ቁልፍ ሚና የሚጫወተውን የስነልቦና ዝግጅት በሙሉ የቡድን መዋቅር ውስጥ የምታሰርጸው እንዴት ነው?

እንደሚታወቀው ሁሉም ነገር ከአእምሮአችን ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጤናማ አእምሮ ሲኖረን የተሻለ ስራ እንሰራለን፤ በጎ እንቅስቃሴ እናደርጋለን፤ አካላዊ ጥንካሬ ይኖረናል፤ በማንኛውም ነገር ላይ ጥሩ ውሳኔ እንወስናለን፡፡ ውጤታማነት የሚመጣውም አዕምሮአችን ጠንካራ ደረጃ ላይ ሲገኝ በመሆኑ በስነልቦና ጉዳዮች ላይ ወደ ኋላ የምልበት ምንም ምክንያት አይኖረኝም፡፡ ማናቸውም መልእክቶች የሚመጡት ከአዕምሮ ስለሆነ የአእምሮ ጥንካሬ ማለት የአካል ጥንካሬን ይፈጥራል፡፡ አእምሮ “እኔ ይህን ማድረግ እችላለው፡፡” ብሎ ካላሰበ አካል አይችልም፡፡ “Muscles are slaves of brain.” አካላዊ ጡንቻዎች የአእምሮ ባሪያዎች እንደመሆናቸው የፈለጋቸውን ያህል ቢከመሩ በራሳቸው የሚያመጡት ምንም ነገር የለም፡፡ የሆነ ተግባር እንዲከውኑ ከአእምሮ የሚላክን ትዕዛዝ ይጠብቃሉ፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜም እውቀትንና አዳዲስ ነገሮችን ለአዕምሮ መመገብ ያስፈልጋል፡፡ የስነልቦና ነገርም አእምሮአዊ ጉዳይ ስለሆነ በዛ ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን፡፡ ለማንኛውም  ችግር ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ሁሌም ቡድንህን በዚህ ረገድ ማዘጋጀት አለብህ፡፡ እኛ አገር ወጣቶቻችን ስለ ስነልቦናዊ ጥንካሬ እየተማሩ ያደጉም አይደሉም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው “ናይጄሪያዎች እኮ 9-ለ-0 ነው የሚያሸንፏችሁ፡፡” እየተባሉና እየፈሩ ነው ያደጉት፡፡ ያው አስፈራሪው ብዙ ነው፤ ሚዲያው ተመልካቹም ያስፈራራቸዋል፡፡ አንድ ጊዜ እንዲያውም “ቦቅቧቃው ብሄራዊ ቡድናችን ዛሬ ግብጽን ይገጥማል፡፡” የሚል ርዕስ ያለው ጽሁፍ ገጥሞኛል መሰለኝ፡፡ ተጫዋችቻችንን እንደዚህ እያሳነስናቸው እንዴት ተድርጎ ነው ጠንካራ ስነልቦና የሚኖራቸው? ቀድሞ ጠንካራ የነበረ ቢሆን እንኳ ከእንደዚህ አይነት አስተያየት በኋላ በጥንካሬው አይቀጥልም፡፡ ስለዚህ ተጫዋቾቻችን እየፈሩ ስላደጉ ያንን ፍርሀት ከአእምሮአቸው ለማላቀቅ እንዲቻል የስነ ልቦና ትምህርትን ጠቀሜታ እያስረዳህና በእድሜ እድገት ማወቅ የሚገባቸውን ነገር ሁሉ እያሳወቁ መሄዱ ውጤታማ ስለሚያደርግ ሁልጊዜ መሰረት አድርገን የምንሰራው ስነልቦና ላይ ነው፡፡


በአንተ የአሰልጣኘት ቆይታ ስር ያለፉ ብዙ ተጫዋቾች ስላንተ ሲናገሩሰውነት ተጫዋቾችን በማስተዳደር ችሎታው የተካነ ነው፡፡ይሉሀል፡፡ ከቀድሞው የመምህርነት ሙያህ ጋር የተያያዘ ይሆን? ያው አሰልጣኝነትም አስተማሪነት ነውና

በስፖርት ሳይንሱ ከምትማራቸው ነገሮች አንዱ የስፖርት አስተዳደር (Sport Administration) ነው፡፡ ቡድንን በምን መልኩ ታስተዳድራለህ? እንዴትስ አድርገህ ነው ተጫዋቾችህን የምትመራው? ተጫዋቾቹ እኮ ምናልባትም በሀብት ይበልጡሀል፤ አንተ በእግርህ እነሱ ደግሞ በመኪናቸው የምትሄዱ ሊሆንም ይችላል፡፡ ከዚያ ውጪ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩና የልጆች አባት የሆኑም አሉ፡፡ ተጫዋችህ ሐላፊነቱን እንዲያውቅ ታደርገዋለህ እንጂ አንተ የምታደርገውን ነገር እንዲያደርግ ትፈቅድለታለህ፡፡ እኔ የማደርገው ነገር ያስቀመጥኩትን አላማ በማይጻረር መልኩ ነው የማደርገው፡፡አንተ ሚስትህ ጋር እየሄድክ እነሱ ባለቤቶቻቸው ጋር እንዳይሄዱ አትከለክላቸውም፡፡ ልጆቹ ማንኛውም ሰራተኛ እንደሚዝናና ሁሉ መዝናናት አለባቸው፡፡ ተጫዋቾቹ እኮ እስረኞች አይደሉም፡፡ እኔ ቤቴ መሄድ ካለብኝ እነሱም ይሄዳሉ፤ ከሚስቱ ጋር መተኛት ካለበትም ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ያንን የሚያደርግበትን ቀን ማወቅና መለየት ነው፡፡ ነገ ጨዋታ እያለ ነው ዛሬ የሚሄደው? ቢራ መጠጣት ይፈልግ ይሆናል፡፡ መቼ ነው የሚጠጣው? በማግስቱ ወሳኝ ጨዋታ እያለበት ዛሬ መስከር ነው አላማው? እነዚህ ጥያቄዎች ላይ ከተጫዋቾቹ ጋር ውይይት እናደርጋለን፡፡ በመመካከርና በመስማማት የምንወስናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ይህን ደግሞ ራሱ የእግርኳሱ ሳይንስም ይፈቅዳል፡፡ ያንን ነው እኔ የምተገብረው፡፡


ሰውነትስነ ስርዓትን የሚያስቀድም፤ ሲያስፈልግ ደግሞፈታየሚያስደርግ አሰልጣኝ ነው፡፡ይባላል፡፡ ቀልደኛና ተጫዋች ሆኖ ዲሲፕሊን ላይ ደግሞ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ መሆንን እንዴት ታዛምዳቸዋለህ?

ስራ ላይ ቀልድ የለም፡፡ በህይወትህና በኑሮህ ላይ ለውጥና እድገት ለማምጣት እንዲሁም ደስተኛ ለመሆን ጠንክረህ መስራት ይጠበቅብሀል፡፡ ከስራ ውጪ ደግሞ መሳቅና መዝናናት አለብህ፡፡ የምትዝናናው ደግሞ ሊያዝናናህ በሚችል ነገር ነው፡፡ መጠጥ  አልኮሊክ ባህሪ ስላለውና በሰውነትህ ውስጥ ያለውን ውሃ ስለሚመጥ የሰውነት ድርቀትን ያስከትላል፡፡ ተጫዋቹ የግድ የሚያዝናናው በመጠጥ ከሆነ ሁለት ሁለት እንዲጠጣ ትፈቅድለታለህ፡፡ እኔ የምጣላው የተፈቀደለትን መጠን አልፎ አስራ ሁለት ሲያደርሰው ነው፡፡ ከዛ ውጪ ከተጫዋቾቹ ጋር እየተነጋገርን መጠጥን እንዳይጠጡና ከድል በኋላ አብረን በአንድ ጠረጴዛ ላይ እንደምንዝናና እየተነጋገርን መጠጣት ያቆሙ ልጆች ነበሩ፡፡ አብሮ የመዝናናትና ቀልዶችን እያመጡ ለመጫወት ማሸነፍን እንደ ቅድመ ሁኔታ የምናይበትን ባህል ፈጥረን ተግብረነው ነበር፡፡ ሁሉም ሰው ውጤታማ እንዲሆን ከጎጂ ነገሮች መራቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ “ዛሬ ከሚስቴ ጋር ማደር ይኖርብኛል፡፡” ካለ እና አዕምሮው በጣም ጥሩ የሚሆን ከሆነ፣ ደስተኛነትን ካገኘ እንዲሁም ሐላፊነቱን በአግባቡ ከተወጣ ለምን አልፈቅድለትም? ከከለከልከው ደካማ ይሆናል፤ የመደበትና የመሰላቸት ስሜት ያሳያል፡፡ ከቡድን አጋሮቹም ሆነ ከአሰልጣኙ ጋር ሰላም አይኖረውም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ጓደኞቹም ሳይቀር ይመካከሩብህና ያድሙብሀል፡፡ ስለዚህ ስራህን በማይበድል ሁኔታ ተጫዋቾቹ ቢዝናኑ ምንም ማለት አይደለም፡፡ ከዛ በተረፈ ግን በስራ ላይ ማሾፍ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ እኔ ከተጫዋቾቼ ጋር አባታዊና ወንድማዊ ግንኙነት ነው ያለኝ፡፡ ከዚህ አልፈህ “አንተ አባቴ አትሆንም፤ ወንድሜም አይደለህም፤ ጓደኝነትም አይኖረንም፤ እኔ እንደፈለግኩ ነው የምሆነው፡፡” ካልከኝ በቃ ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡ እኔ ‘ልጄ ነህ፤ ወንድሜ ነህ፡፡’ እያልኩህ፤ አብረን እየበላን፣ አብረን እየኖርን፣ በአንድ ሆቴል ወይም መኖሪያ አብረን እየገባንና እየወጣን እንዲሁም ሰላምታ እየተለዋወጥን መከባበሩ ከሌለ አብረን መቀጠል አንችልም ማለት ነው፡፡ ሁሌም በዚህ መልኩ ስለምንወዳጅ ተጫዋቾች እጅግ በጣም ደስተኞች ናቸው፤ እኔም እንደዚያው ደስተኛ ነኝ፤ ያስቀየምኳቸው ልጆች የሉም፡፡ ብዙዎቹን እንዲያውም ሽማግሌ በመሆን ድሬያቸዋለሁ፡፡ ስቀንሳቸው እንኳ “ኮች መልካም እድል ይግጠምህ!” ብለውኝ ነው የሚሄዱት፡፡ በእርግጥ ከአንዳንዶቹ ጋር የተቀያየምኩበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ አቅማቸውን ስላልተረዱ ነው ችግሮች የተፈጠሩት፡፡ ህዝቡም የተጫዋቾቹን አቅም ስላላወቀ በአንድ ወቅት ከኔ በተቃራኒ ቆሞ ነበር፡፡ ሆኖም ቀስበቀስ ደረጃቸውን እየተረዳ ሲመጣ “አሃ! ሰውነት ለካ ልክ ነበር፡፡” እያሉ ብዙ ሰዎች ይቅርታ ጠይቀውኛል፡፡ ስራ ማህበራዊ ባህሪ አለው፤ ስለዚህ በደንብ ተግባብተህ፣ ተዋደህና እጅለእጅ ተያይዘህ መስራት ይጠበቅብሀል፡፡ አንድ ስራ አስኪያጅ ጠረጴዛውን የምትጠርግለትን ሰራተኛ ማክበር አለበት፡፡ አንድ የወይን ፋብሪካ የወይን ጠጁ ምርት እንዲስፋፋለት የወይን ተክሉን ተኩላ እንዳይበላው የሚጠብቅለትን ዘበኛ ማክበር አለበት፡፡ በየትኛውም የስራ መስክ ብቻህን ምንም አታመጣም፡፡


Biological እውቀትህ እንደነዚህ አይነቶቹን ነገሮች እንድትፈቅድ የሰጠህ ድፍረት አለ?

አይ ተፈጥሮ ነው፡፡ Biology ላይ እኮ ስለ Animal Kingdom እና Plant Kingdom ነው ያጠናሁት፡፡ ጥናቴ እንግዲህ አንድን ቅጠል ወስደህ ብታይ የእያንዳንዷን መስመር ስምና ተግባር ከማወቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እና………..


በምትፈቅዳቸው ነገሮች ላይ ባለህ አቋም የተነሳ ነው ጥያቄውን ያነሳነው፡፡

ገብቶኛል! ዋናው ነገር የሰው ልጅ ርህራሄ እና የመረዳት ፍላጎት ሊኖረው ይገባል፤ Humanitarian መሆን አለብን፡፡ ሰዎች እኮ ምንም አይደለንም፡፡ እንወለዳለን፤ እናድጋለን፤ እንሞታለን፡፡ በቃ! ከእነዚህ የህይወት ኡደት ውጪ ልትሆን አትችልም፡፡ ስለዚህ ሰው መሆናችንን አክብረን መሄድ አለብን፡፡ ለምንድነው አንዳችን ሌላኛችን ላይ ጫና የምንፈጥረው? ሁላችንም እኩል ነን፡፡ በተመሳሳይ የስራ መስክ ላይ የምንገኝ ከሆንን ተስማምተንና ተግባብተን ነው መስራት ያለብን፡፡


የአሰልጣኝነት ኮርሶች በወሰድክባቸው አገሮች የተማርካቸው ትምህርቶች በእግርኳስ ፍልስፍናህ ላይ ያሳደሩት ተጽእኖ አለ?

ፍልስፍና የግል ነው፡፡ እያንዳንዱ አሰልጣኝ የራሱ የሆነ ፍልስፍና አለው፡፡ በእርግጥ የፍልስፍና መንገዶችን ልትማራቸው ትችላለህ፡፡ ያዋጣኛል ብለህ በምትመርጠው መስመር የምትሄደው በራስ ውሳኔ ነው፡፡ ሆኖም የምመራበት ፍልስፍና ውጤታማ የማያደርገኝና የማይጠቅመኝ ከሆነ ‘ፍልስፍናዬ ልክ አይደለም እንዴ?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ በደንብ አስቤበትም ለመቀየር እሞክራለሁ፡፡ ማወቅህና መማርህ ደግሞ የራስህን ፍልስፍና እንድታሰፋውና እንድታሻሽለው ሊጠቅምህ ይችላል፡፡


ከዚህ ቀደም በአሰልጣኞች ገፅ ላይ የወጡ ጽሁፎችን ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ፡፡   LINK


 


በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ አሰልጣኝነትን አስቸጋሪ የሚያደርገው ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

ድህነት! አንዱና ዋነኛው ችግር ድህነት ነው፡፡ በራስህ ሙያ በልበ ሙሉነት እንዳትወስን በርካታ ተጽዕኖዎች አሉብህ፡፡ እንደማንኛውም ሙያ ተቀጣሪ ነህ፤ ቤተሰብ ታስተዳድራለህ፤ ልጆች አሉህ፤ በየወሩ እየከፈልክ ታስተምራለህ፤ መመገብ፣ማልበስና ለህክምና ወጪ ማስቀመጥ አለብህ፡፡ ከባንክ ተበድረህ ቤት ሰርተህም ይሆናል፤ በዚያ ላይ የኮንትራት ሰራተኛ ነህ፡፡ በስራህ ላይ ደግሞ የሚያዝህ ሙያተኛው ሳይሆን ገንዘብ ያለውና ያለቦታው የተቀመጠ እድል ያጋጠመው አመራር  አንተን እንደፈለገ ይመራሀል፡፡ ስለዚህ የሱ ተገዢ ነህ፡፡ ሲፈልግ ያባርሀል፤ ሲያሻው ደግሞ ተጫዋቾችህ እንዲያድሙብህ ያደርጋል፡፡ ስራህን ካጣህ ቤትህ በእዳ ይሸጣል፤ ልጆችህ ትምህርታቸው ይስተጓጎላል፤ ሌሎችም ችግሮች ይመጡብሀል፡፡ ይሄ እንዳይሆን ተለማማጭና እግርኳሱ ሲሞት አብረህ የምትገድል ሰው ትሆናለህ፡፡ ስለዚህም እግርኳሳችን እስከዛሬም ድረስ ያላደገው በድህነታችን ምክንያት ነው፡፡ ሙያተኛው ደሃ ነው፤ ያ የድህነት ተጽእኖ በራስህ እንዳትተማመን ያደርግሀል፡፡ የራሴን ታሪክ ነው እየተናገርኩ ያለሁት፡፡ ካለፍኩበት የህይወት መንገድ  ማስረዳቱ የተሻለ ነው፡፡ እኔ አስተማሪ ነበርኩ፤ ካስተማሪነቴ ከወጣሁ በኋላ እጅግ በጣም ስለምወደውና ስለምፈልገው የስልጠና ሙያ (Coaching) ውስጥ ገባሁ፡፡ ሙያውን ስጀምረው ብቻዬን ነበርኩ ማለት ይቻላል፡፡ በሚዲያ ይህን ብዙ ጊዜ ተናግሬዋለሁ፡፡ ቤቴን ከባንክ ተበድሬ ነበር የሰራሁት፡፡ በወቅቱ ከስራ ወጥቼና 194 ብር በወር መክፈል አቅቶኝ ቤቴን በሀራጅ ሊሸጥብኝ ሞርጌጅ ጥያቄ አቀረበ፡፡ “ቤትህን ልንሸጠው ነው፡፡” አሉኝ፡፡ ስራ የማላገኝ መስሎኝ “እኔን እኮ አትሸጡኝም፤ ቤቱን እንጂ- ስለዚህ ሽጡት፡፡” ብያቸው ነበር፡፡ ኋላ እንደገና የባንኩ ሰዎች የተወሰነ ተጨማሪ የእፎይታ ጊዜ (Grace Period) ሰጡኝ፡፡ ወዲያው ስራ ሳገኝ ያ ቤት የእኔ አለመሆኑን ተረድቼ  በወቅቱ ከሚከፈለኝ 1350 ብር ደመወዝ በወር 1000 ብር እየከፈልኩ በ8 አመት ጊዜ ውስጥ እዳዬን ከፍዬ ጨረስኩ፡፡ እንግዲህ የግድ ለቤተሰብህ ስትል እስረኛና ፈሪ ትሆናለህ፡፡ የምታምንበትን አታሰራም፤ ተጫዋቹ ሊያዝህ ይችላል፤ ተለማማጭ እንድትሆን ትገደዳለህ፡፡ ጠንክረህ በአቋምህ ለመጽናት ስትሞክር ተጫዋቹ ያድምብህና ትወጣለህ፡፡ ይህን የሚረዳ አመራር የለም፡፡ ይሄ ነው እግርኳሳችንን ወደ ኋላ እየጎተተና ዝቅተኛ ደረጃ እንዲኖረው ያደረገው፡፡


አሁን ያሉት አሰልጣኞች አንጋፎች ከሆናችሁት በተለየ የተሻለ የገንዘብ ነጻነት አላቸው፤ ጥሩ ክፍያም ያገኛሉ፡፡ ይህን ማግኘት መቻላቸው የራሳቸውን እግርኳሳዊ እምነት በስልጠናው ላይ እንዲያሳርፉ ያደርጋቸዋል ብለህ ታስባለህ?

አሁን አንድ አሰልጣኝ እስከ መቶ ሺህ ብር ድረስ ያገኛል፡፡ እኔ እግርኳስ ማሰልጠን ስጀምር 150 ብር ነበር የማገኘው፡፡ በክለብ አሰልጣኝነት የመጨረሻው ትልቁ ደመወዜ ዘጠኝ ሺህ ብር ተጠግቷል፡፡ በብሄራዊና ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ጊዜዬ ደግሞ ሀምሳ ሺህ ብር ተብሎ ይጠራል፡፡ 5,000 ብር ለስልክና 5,000 ብር ለቤንዚን ቀረጥ የማይከፈልበት ተደምሮ 10,000 ብሩ ይቀነስና ከቀሪው 40,000 ብር ደመወዝ ላይ ለተለያዩ ክፍያዎች ተቆራርጦ 21,000 ብር ይደርሰኛል፡፡ ከ10,000 ብሩ ጋር ባጠቃላይ 31,000 ሺህ ብር አገኝ ነበር፡፡ የአሁኑ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኞች ስንት እንደሚያገኙ ይታወቃል፡፡ እኔ በአሁኑ ጊዜ ያሉ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ነገሮች የተሻለ ተመቻችተውላቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ቀደም ብዬ ገልጬዋለው ለእግርኳሱ ግብዓት የሚሆኑት ነገሮች አቅርቦት ጠንክሯል፡፡ ገንዘቡ አለ፤ የሰዉ የእግርኳስ ፍላጎት ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወቅት ላይ እያንዳንዱ ሙያተኛ ራሱን ጠይቆ እግርኳሱ ከዚህ በላይ እንዲያድግ ቢያደርግ፣ ሙያተኛውም የበለጠ እንዲያድግ ቢለፋ፣የተሻሉ እግርኳስ ተጫዋቾች የሚፈሩበት መንገድ ቢመቻች፣…ሌሎችም መሻሻሎች መምጣት እንደሚችሉ በማመን ጠንክረው መስራት ያለባቸው አሁን በስራው ላይ ያሉት ሙያተኞች ናቸው ማለት እንችላለን፡፡


በዝቅተኛ ወርሀዊ ደመወዝና በአስቸጋሪ የኑሮ ውጣውረድ ውስጥ ሆናችሁ የምታመጡት ውጤት አሁን የተሻለ በሆነ ክፍያ ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች እየሰሩ ከሚመዘገበው ውጤት አንጻር ተመዛዛኝ ደረጃ ላይ አይገኝም፡፡ ለዚህ ልዩነት መፈጠር ምክንያት የሚሆን ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች ጋር ያለው ችግር ምን ይመስልሀል?

ሙያተኛው ይህንን ዝቅተኛ ውጤት ሲያመጣ የሚጠይቀው አካል ባለመኖሩ ጉዳዩ አያደርገውም፡፡ በየአመቱ በክለቦች ለእግርኳስ በአማካይ እስከ አርባ እና ሀምሳ ሚሊዮን ብር የሚደርስ ከፍተኛ በጀት ይመደባል፡፡ ይሄ ሁሉ ብር እየተመደበ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሚሆን የበቃ ተጫዋች እየወጣ አይደለም፡፡ ውጤታማ ቡድንህም እየሰራን አይደለም፡፡ በወጣትና በዋናው ብሄራዊ ቡድን ደረጃ የሚሰባሰቡት ተጫዋቾች ረዘም ላለ ጊዜ በጥሩ ብቃት ሲያገለግሉ አናይም፡፡ እንደሚመስለኝ ክለቦች ብዙ ገንዘብ ሲበጅቱ ከተቋማዊ እቅዳቸው በተጨማሪ ትልቁ አላማቸው የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ጠንካራ አድርጎ አገሪቷ በስፖርቱ ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ ነው፤ ሌላ ነገር የለውም፡፡  ስለዚህ አመራሩ ይህን ነገር መጠየቅ፣ የሚሰራውን ስራ ማየት እና መገምገም አለበት፡፡ (Coaching is progressive.) የስልጠና ሙያ ዘወትር ለውጦችንና መሻሻሎችን የምታሳይበት እንጂ ዝም ብለህ በየጊዜዉ አንድን ነገር ለመስራት በተመሳሳይ መንገድ የምትደጋግመው ሒደት (routine) አይደለም፡፡ የተጋጣሚዎችህን ያህል የጨዋታዎቹ አይነቶችም ይለያያሉ፡፡ ለእያንዳንዱ ተጋጣሚ ቡድን የምታሰራቸው ስራዎች በሙሉ የተለያዩ ናቸው ፡፡ ተግባራዊ ልምምዱም ሆነ ንድፈ ሐሳባዊው ትምህርት ተጫዋቾቹን ብቁ የሚያደርግ መሆን መቻል አለበት፡፡ ይህንን ማስተካከልና ማረም ደግሞ በየክለቡ ያለ አመራር ሀላፊነት ነው፡፡ አመራሮች በእግርኳሱ ሙያ ያላቸው እውቀት ጠለቅ ያለ ሊሆን ይገባል፡፡ አለበለዚያ በጀት ትመድባለህ፤ ችግሩን ከላይ ከላይ ትጠይቃለህ፤ ምክንያት ይሰጥሀል፤ ከዚያ ትነሳና ክለቡን ታፈርሳለህ፡፡ ልክ እንደ ንግድ ባንክ ቡድን፡፡ ገንዘብ እያለ ሁኔታውን በስነስርዓት ካለማስኬድ የተነሳ ስንትና ስንት ልጅ ሊያድግበት የሚችል የድርጅት ክለብ ይፈርሳል፡፡ ስለዚህ ከሙያተኛው በፊት አመራሩ መጠየቅ መቻል አለበት፡፡ የሙያተኛው ዕለታዊ ተግባርም ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡ ለምሳሌ በታዳጊ- ህጻናት እድገት (Youth Development) አንድ የስምንት አመት ልጅ አንድ አመት ተገቢውን የተግባር ልምምድ ከሰራ በኋላ በአመቱ መጨረሻ ማወቅ የሚጠበቅበትን ነገር የሚወስንና የሚያስቀምጥ አሰራር አለ፡፡ “አውቆታል ወይስ አላወቀውም?” ያንን አሰልጣኙ ይገመግማል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ዘጠኝ አመቱ ሲሄድ ደግሞ ሌላ የሚሰራውን ተግባራዊ ስልጠና እየሰጠኸው ተከታታይነቱን ትቆጣጠራለህ፡፡ የስልጠናውን ጥራትና ደረጃ ሊከታተለውና ሊያርመው የሚችል ሙያተኛ መሪ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ በሌለበት እግርኳሳችን ካሁኑ የበለጠም ወደ ታች ሊሽመደመድ ይችላል፡፡


እግርኳሳችን ታክቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች ወደ ኋላ የቀረበት አሰልጣኞችን የተንተራሰ ምክንያት ይኖራል?

እንዲያው ዝምብዬ እናንተን አልጠይቃችሁም እንጂ በእግርኳስ ታክቲካዊ ልምምዶች የሚጀምሩት መቼ ነው? የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ የእግርኳስ ስልጠና አራት እርከኖች አሉት፡፡ እነዚህም Initial Stage,Basic Stage, Intermediate Stage እና Advanced Stage ናቸው፡፡ በእነዚህ ደረጃዎች ህጻናት ማወቅ ያለባቸውን ነገሮች አውቀው የላይኛው እርከን ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ የማንችስተር ዩናይትዱ የ18 አመት ወጣት ማርከስ ራሽፎርድ የመጨረሻው እርከን ላይ ደርሶ ለብሄራዊ ቡድን እየተጫወተ ነው፡፡ በእኛ አገር እግርኳስ በተመሳሳይ እድሜ ያለ ልጅ ገና ስለ <ድሪብሊንግ> ይማራል፡፡ ይሄ ፈጽሞ የማይሆንና መደረግ የሌለበትም ነው፡፡ አንድን ተጫዋች በ18 አመቱ ስለ ድሪብሊንግ ልታስተምረው አትችልም፡፡ ብሄራዊ ቡድን በመጫወቻ እድሜው ላይ አንተ መሰረታዊ ነገር ልታስተምረው ትሞክራለህ፡፡ በዚያ ሁኔታ ገንዘብና ጊዜ ይባክናል፡፡ ይህንን በፍፁም አለማድረግ ነው፡፡

“ስለዚህ ምንድን ነው መደረግ ያለበት?” ሲባል “ህፃናት ቴክኒካዊ ልምምድን በስንት አመት ይስሩ? መሰረታዊውን ታክቲካዊ ስልጠና ስንት አመታቸው ላይ ይጀምሩ?” የሚሉትን ጥያቄዎች በአለም አቀፋዊው አሰራር መልስ መስጠት አለብን፡፡

ህጻናት በአስራ አንድ አመታቸው መሰረታዊ የታክቲክ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ስለዚህ የታክቲክ ሀሁ የሚጀመረው በአስራ አንድ አመት ነው ማለት ነው፡፡ “የእኛ ልጆች ደካሞችና ደቃቆች ናቸው፡፡” ይባላል፡፡ ተጫዋቾቻችን ከልጅነታቸው ጀምሮ የሰውነት ማጎልመስና ማጠንከር (Body Building) ልምምድ ቢሰሩ ተክለሰውነታቸው ይህን ይመስል ነበር? ጡንቻዎቻችን እንዳያድጉ የተረገሙ ናቸው እንዴ?

“የአካል ግንባታ ልምምድ በየትኛው የእድሜ ክልል ይጀመራል?” ትክክለኛ አሰራሩን ስለማናውቅ  አንሰራውም፡፡ በቴክኒኩም ቢሆን አንድ ህጻን እስከ አስር አመቱ ድረስ የኳስ ቁጥጥር(controlling)፣ ቅብብል (passing)፣ ድሪብሊንግና የመሳሰሉትን ነገሮች ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አንድ ህጻን በትክክለኛው እድሜ ተገቢውን ስልጠና ካገኘ ቅብብሎችን አይሳሳትም፡፡ ለምሳሌ እኔ እያሰራኋቸው ያሉትን ታዳጊዎች ብታዩ ቅብብሎችን የሚሳሳቱ ህጻናት አታገኙም፡፡ ህጻናቱን ሁለት አመት ተኩል ሰርቼባቸዋለሁ፡፡ እነዚህን ልጆች አስራ አንድ አመት ሲሆናቸው መሰረታዊ የታክቲክ ምንነትን እንዲገነዘቡ እናደርጋቸዋለን፡፡ የአካል ብቃትና ፍጥነትን ጠቀሜታም እንዲረዱ እያደረግን እናሳድጋቸዋለን፡፡ በዘመናዊ እግርኳስ መንቀርፈፍና ሮጦ መቅደም አለመቻል ዋጋ ያስከፍላል፤ ምክንያቱም ስፖርቱ የጠንካሮችና የፈጣኖች ውድድር ነውና፡፡  በኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ላይ የተመሰረተ እግርኳስ (Possession Football) ለመጫወት እንኳ ኳሱን በቁጥጥርህ ስር ለማድረግ መጀመሪያ ኳሱ አካባቢ መገኘት መቻል አለብህ፡፡ ሁልጊዜ ኳስን የምታጣ ከሆነ ተከላካይ ነህ፡፡ ኳሱን የያዘው ያጠቃል፤ ኳሱን ያልያዘው ይከላከላል፡፡ በተጨማሪም የPossession Football ለመጫወት በታክቲክ የበቃህ መሆን ይጠበቅብሀል፡፡ ታክቲካዊ ተግባራትን በጥሩ ሁኔታ ለመከወን በተደጋጋሚ በቦታህ ላይ መገኘት አለብህ፡፡ ከታክቲክ መርህ አንዱ በተገቢው ሰዓት ትክክለኛ ቦታ ላይ መገኘት ነው፡፡ ይሄን ሁሉ የምለው ተጫዋቾቻችንን በእድሜ እርከናቸው ማወቅ ያለባቸውን ነገሮች አሳውቀን አናሳድጋቸውም፡፡ ካደጉ በኋላ ኳስ ተጫዋች ይሆናሉ፤ ወደኋላ ተመልሰን በትክክለኛው መንገድ ልንገራቸው የምንችልበት እድሜ ላይ አይደለም የምናገኛቸው፡፡ ይህ ነገሩን የበለጠ ያከብደዋል፡፡የታክቲክ ውህደት የተሰጠህን ሀላፊነት በአግባቡ ከመወጣትም በላይ ከቡድን አጋሮችህ ጋር በጥሩ ሁኔታ ተቀናጅተህ መስራትን ያካትታል፡፡ ታክቲክ፡- የግለሰብ ታክቲክ (Individual Tactic)፣ በሜዳው የተለያዩ መጫወቻ ክፍሎች በሚገኙ ተጫዋቾች ስብስብ የሚተገበር ታክቲክ (Group/Department Tactic) እና በሙሉ ቡድን የሚሰራ ታክቲክ (Team Tactic) ተብሎ በተለያዩ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ በተናጠል ተጫዋቾች በቦታቸውና በሜዳ ላይ በሚወጡት ሀላፊነት ታክቲካዊ እቅዶችን ለማሳካት ይጥራሉ፡፡ ከቡድን አጋሮቻቸው ጋር በተለይም ደግሞ በአንድ አይነት የመጫወቻ ክፍል ከሚሰለፉ ተጫዋቾች ጋር የሚኖረው መግባባትና ውህደትም በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ በቡድኑ አጠቃላይ የአጨዋወት ስርዓት ላይ ያለው ድርሻ በተለይም በሁሉም የጨዋታ ሒደቶች ውስጥ የሚደረገው ብልሀታዊ ተሳትፎ ዋነኛ ግብዓት ነው፡፡ ዳንኤል አልቬዝን እንደ ምሳሌ እናንሳ፡፡ በየጨዋታው በቀኝ መስመሩ ላይ ሲበር ይውላል፤ ወደ ግራ ሄዶ ታይቶ ያውቃል? አይመስለኝም፡፡ እኛ አገር ግን የቀኝ መስመር ተከላካዩ ነቅሎ ሄዶ በግራ መስመር ሲጫወት ታያለህ፡፡ በጨዋታ ወቅት ይህን መሰል የቦታ አጠባበቅ ስርዓት (Positional Discipline) ያለማሳየት ችግር የመጣው ከልጅነታቸው ጀምሮ በአግባቡ መሰረታዊ ነገር ስላላስተማርናቸው ነው፡፡ ተጫዋቾቻችን በታክቲክ ረገድ ከማንም ሰንፈው አይደለም፤ ከመሰረቱ ታክቲካዊ ግንዛቤያቸውን ለማዳበር የሚሆን ነገር ስላልሰጠናቸው እንጂ፡፡


በአንጋፋነት ካንተ ጋር እኩያ የሆኑትና ከፍ ያሉትም አሰልጣኞች የተለያየ የስራ ባህሪ ታሳያላችሁ፡፡ለምሳሌ አንተ ተጫዋቾችን ለአንድ አላማ እንዲቆሙ በማስተዳደሩ (Player Management) በደንብ ትታወቃለህ፡፡ የተቀሩት ደግሞ በዲሲፕሊን፣ በአጨዋወት ዘይቤና በሌሎችም የሚታወቁበት መለያ አላቸው፡፡ በዘመናችሁ ሁላችሁም እንዲህ የሚጠቀስላችሁ ጠንካራ ጎን ህብር እንዲኖረው ቢደረግ እግርኳሱ የበለጠ ያድግ ነበር ተብሎ ይታመናል፡፡ ያን ለውጥ ማምጣት የሚችል ህብረት ለመፍጠር እንድትቀራረቡ፣ እንድትነጋገሩና ሀሳብ እንድትለዋወጡ የሚያደርግ ስርዓት አለመፈጠሩ ከእናንተ ሊገኝ የሚችለውን ትምህርትና ልምድ ወደ ቀጣዩ አካል እንዳታስተላልፉ ምን ያህል አባክኗችኋል?

ትክክል! ተገናኝተን አናውቅም፡፡ በእኛ ጊዜ የነበርነው አሰልጣኞች ሁላችንም ራሳችንን “ትልቅ ነን!” ብለን ነበር የምናስበው፡፡ በየራሳችን ደረጃ የመኮፈስ ነገር ካልሆነ በስተቀር አብረን ተያይዘንና አንድ ላይ ሆነን በአገራችን እግርኳስ ላይ ያለውን ድክመት መርምረን፣ አይተንና ተወያይተን እንዲሻሻል ያደረግነው ጥረት የለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የአሰልጣኞች ማህበር አቋቁመናል፡፡ የመጀመሪያውን አሰልጣኞች ማህበር ያቋቋምነው እኛ ነን፡፡ እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ ያ ማህበር ጠንካራ ነበር፡፡ ከውጪ አገሮች -ከእንግሊዝ፣ ጀርመንና አሜሪካ አሰልጣኞች ማህበሮች ጋር ግንኙነት ፈጥረን ብዙ እየተጻጻፍን ግንኙነቱን ውጤታማ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ትልልቅ ሲምፖዚየሞችን ሁሉ አካሂደናል፤ ጥሩ ጥሩ ብሮሸሮችን አዘጋጅተናል፤ አጫጭር ትምህርቶችን (Refrashment Courses) ወስደናል፡፡ እግርኳሳችን ላይ ባሉት ችግሮች ላይ ሁሉ መነጋገር ጀምረን ነበር፡፡ ነገር ግን በዘላቂነት አልቀጠለም፤ ከጊዜ በኋላም ተበተነ፤ እንዲያውም ጭራሽ ሌላ ስም ተሰጠንና ማህበሩ ፈረሰ፡፡ በእርግጥ ከዚያ ጊዜ በኋላ የአሰልጣኞች ማህበር ተቋቁሟል፤ ነገር ግን ዘወትር የሚሰራ (functional) አይደለም፡፡ አንዳንድ ወቅቶች ላይ እንሰባሰባለን፡፡ ለምሳሌ በስዩም አባተ ህመም ምክንያት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ከመገናኘት ባለፈ በትምህርቱና በእግርኳስ እድገቱ ዙሪያ ከእኛ የበለጠ ተነጋግሮ እና ተወያይቶ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አካል የለም፡፡ እኛ ይህን ተገንዝበን እየተገናኘን መለወጥ የምንችለውን እንዳናበረክት ያደረገንን ነገር እንዲሁም በመሀላችን ውስጥ ያለውን መቃቃር እንድንቀርፍና ዘላቂ ግንኙነት እንዳይኖረን  የሚያራርቀንን ነገር ማወቅ አለብን፡፡ እስካሁን ባለው እውነታ አንደኛው በራሱ መስመር ይሄዳል፡፡ እኔም እንዲሁ በራሴ መንገድ አቀናለሁ፤ ስራዬን እሰራለሁ፤ ኑሮዬን እኖራለሁ፤ ቤተሰቤን አስተዳድራለሁ፡፡ በዚህ ሒደት አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ በሌላው አለም ግን በእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ወይም በአሰልጣኞች ማህበሩ አማካኝነት በመላው አገሪቱ ውስጥ ያሉት አሰልጣኞች ይሰበሰቡና አመቱን ሙሉ ስለሰሩት ስራ ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡ ስለገጠማቸው ችግር፣ ድል ስላገኘኙበት አሰራር፣ መሻሻል ስላለባቸው ነገሮችና ሌሎችም ነገሮች ውይይት ያደረጋሉ፡፡ ለተለያዩ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጡ አካላት የሚሰባሰቡበት ቴክኒካል ዲፓርትመንትም አለ፡፡ “በምን መልኩ ውጤታማነት ታየ? የወረዱት ቡድኖች ችግሮቻቸው የትኞቹ ናቸው?” እዚህንና መሰል እክሎችህን ይወያዩባቸዋለል፡፡ ዲፓርትመንቱ እንደመፍትሄ የሚወሰድ ሐሳብ ያወጣና በመላው አገሪቱ ለሚገኙ አሰልጣኞች ይበትናል፡፡ ይህ የሚሆነው አሰልጣኞች ተገናኝተው ስለሚወያዩ፣ ለአገራቸውና ለሙያቸው ስለሚሰሩም ነው፡፡ የእኔ ሙያ የእኔ ብቻ አይደለም፤ የሁላችንም አሰልጣኞች ሙያ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት የእግርኳስ ሙያችንንም አሳልፈን ለሌላ አካል እንድንሰጥ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሌላ ሰው እኮ ነው በሙያው እንደፈለገ እየሆንበት የሚገኘው፡፡ በተለይ ጥሩ ተናጋሪ ከሆንክ እና ኢንተርኔት ላይ ገብተህ ስለ ፈርጉሰን የሆነች ነገር ካነበብክ ሚዲያ ላይ ወጥተህ ማብራራት ነው እየተለመደ የመጣው፡፡ ይሄ ብቻውን እግርኳሱን አያሳድገውም፡፡ እግርኳስ ተግባራዊ ነው፤ በወሬ ሳይሆን መሬት ላይ ተወርዶ የሚሰራ ስራ ነው፡፡ በተግባር የሰራው ሰውና የተማረው አሰልጣኝ ናቸው ክብደቱን የሚያውቁት፡፡ እነዚህ ችግሮች ላይ ተቀራርቦ መስራት ሲገባን አላደረግነውም፤ ይህ እንግዲህ ለዘመናት አብሮን የኖረ ነው፡፡

ስለዚህ በውስጣችን ያለውን እውቀት በመገናኘት ልንጋራና ልንካፈል ይገባል፡፡ ለእግርኳስ እድገቱ ለውጥ ሲባል በሀሳብ እስከ መፋጨት የሚደርሱ ክርክሮችን እና ውይይቶችን ማድረግ አለብን፡፡

እንግዲህ ቀጣዩ ትውልድ አንድነት ፈጥሮ የሚሰራ ከሆነ አሪፍ ይሆናል፡፡

አሰልጣኞች በውስጣችን ያለውን እውቀት በመገናኘት ልንጋራና ልንካፈል ይገባል፡፡ ለእግርኳስ እድገቱ ለውጥ ሲባል በሀሳብ እስከ መፋጨት የሚደርሱ ክርክሮችን እና ውይይቶችን ማድረግ አለብን፡፡


የህብረት መድረኮች ባይፈጠሩ እንኳ በአጋጣሚ የምትገናኙባቸው ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ 1990ዎቹ አጋማሽ በሴካፋ ዋንጫ ውድድር ከአስራት ሃይሌ ጋር ሰርተሀል ፡፡ ከሌሎች አሰልጣኞች ጋርም በዋናና ምክትልነት በጋራ እንድትሰሩ ስትመደቡ ያሳለፍካቸው የአብሮነት ጊዜያት ነበሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የምታሳዩት የእርስ በርስ መተባበር እና እውቀትን ለመካፈል የምታደርጉት ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

እንግዲህ በሌላው አለም በአሰልጣኞች ቡድን  (Coaching Staff) ውስጥ ዋናው አሰልጣኝ አጠቃላይ የቡድኑን እንቅስቃሴ ይመራል፡፡ በቡድኑ የአካል ብቃት አሰልጣኝ፣ የቴክኒካል ጉዳዮች ተጠሪ፣ የስነልቦናዊ ዝግጅቶች መምህር፣ የስነ ምግብ ባለሙያ፣ የታክቲክ ተንታኝና ሌሎችም ባለሙያዎች ይኖራሉ፡፡ እዚህ ባለሙያዎች ለዋናው አሰልጣኝ እቅድ በእኩል ደረጃ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ እኛ አገር ግን ይሄ አሰራር አልተለመደም፡፡ በነበረው አሰራር በምክትል አሰልጣኝነት ስትቀጠር ታዛዥ ሆነህ እንድትቆም ነው የሚፈለገው፡፡ በታሪክም ቢሆን ከድሮ ጀምሮ ምክትል አሰልጣኝ ዋና ተግባሩ ሲታዘዝ እየሮጠ ሄዶ ኮን ማስደርደርና ኳሶችን ማሰበሰብ ነበር፡፡ ይሄ ፍጹም ስህተት ነው፤ በዚህ አካሄድ ላይ እኔ የበኩሌን አስተያየት ሰጥቻለሁ፡፡ ‘ምክትል የምሆነው ልሰራ እንጂ ልቆም አይደለም፤ በምንም አይነት ለእንደዚህ አይነቱ ስራ አልቆምም፡፡’ ካልኩ በኋላ ነው ዋና አሰልጣኝ የሆንኩት፡፡ በዋና አሰልጣኝነት ብሄራዊ ቡድኑ ተሰጠኝና ሩዋንዳ ሄጄ የሴካፋ ዋንጫ ይዤ መጣሁ፡፡ ከዚያ በኋላ እንደገና “ምክትል ሁን፡፡”ስባል ‘አልሆንም፤ ዋንጫ አምጥቻለሁ፤ በደረጃ ከማንም አላንስም፡፡’ አልኩ፡፡

ዶ/ር አሸብር ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የዋና አሰልጣኝነቱን ሰጠኝ፤ ሊብያን አሸነፍኩና ጫጫታው ሲበዛ ለቀኩ፡፡ ከአምስት አመት በፊትም ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ስመጣ የኮቺንግ ስታፉን አዋቀርኩ፡፡ በመተማመን መስራት ግድ ነው፡፡ ሁሉም የአሰልጣኝ ቡድን አባላት የየራሳቸው ተግባር አላቸው፡፡ ሁሉን ነገር አሟልቶ የያዘ ሰው የለም፡፡ ጉድለቶች ይኖሩብናል፤ በህብረት ስንሰራ እነዛን ክፍተቶች እንደፍናለን፡፡ እኛ አገር የተለመደው ግን ዋና አሰልጣኝ ስትሆን “ያለ እኔ ሰው የለም፡፡” ማለት ትጀምራለህ፡፡ የልምምድ እቅድ ማውጣት ሳይችል ሁሉ የሚኮፈስ አለ፡፡ ልትረዳው ስትፈልግ የሚኮራብህ ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከጥንትም የነበረ ለወደፊቱ መስተካከል ያለበት እንዲህ አይነቱ መለያ ግድግዳ (Barrier) አለ፡፡ የአገሪቱ እግርኳስ በአዋቂዎች መመራት አለበት፡፡ ስልጠናው ላይ ያለን ባለሙያዎች ደግሞ እርስ በርስ በመመቀኘት ስሜት “እሱ እኮ አይችልም፡፡” እየተባባልን ገመናዎቻችንን ለብዙሃን መገናኛዎች ከመስጠት ይልቅ በሚጎድሉን ነገሮች ላይ በግልፅ መወያየትና በትብብር በመስራት ማመን  ይገባናል፡፡ የመጣንበት መንገድ የልዩነት ስለነበረ በጋራ ተባብሮ ለመስራት አልተቻለም፡፡ ይህም የአገሪቱ እግርኳስ ውጤት ላይ እየፈጠረ ያለው ተጽዕኖ እየታየ ነው፡፡


ታዋቂ ተጫዋች ሳትሆን ወደ ስልጠናው ሙያ ገብተህ አንጋፋ አሰልጣኝ መሆን ችለሀል፡፡ ጭራሽ የተጫዋችነት ህይወትን ያላዩና በትልቅ ደረጃ ያልተጫወቱ ሆነው አሰልጣኝ ለመሆን የሚጥሩና የሚመኙ ወጣቶች ምን ምን ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል? በውጪው እግርኳስ ብዙዎች ቢኖሩም በአገራችን እግርኳስ ያንተ ህይወት ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪነት የምታስተላልፈው ምክራዊ ሀሳብ ካለ…..

መጀመሪያ የሚገጥማቸው ችግር አሉባልታ ነው፡፡ “እሱ እኮ በብሄራዊ ቡድን አልተጫወተም፡፡” የሚል ወሬ፡፡ በአለም ላይ ያሉ አሰልጣኞች በሙሉ ብሄራዊ ቡድን ተጫውተው አይደለም የሀገራቸውን ቡድን የሚያሰለጥኑት፡፡ ከተለያዩ ሙያዎች ወደ አሰልጣኝነቱ እየመጡ ስኬታማ የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ዋናው ነገር ያለህ አሰልጣኝ የመሆን ጠንካራ ፍላጎትና ሙያው የሚጠይቀውን ተገቢ እውቀት መያዝህ ነው፡፡ በትምህርት እውቀትህን አዳብር፤ በምታገኘው የሊግ ደረጃ ያወቅከውንና የተማርከውን ነገር ተግባራዊ እያደረክ የበለጠ ልምድህን አሻሽል፤ ተማር፤ እወቅ፡፡ ተራ አሉባልታና ወሬ አንተን ከመስራት ሊያግዱህ እንዳይችሉ ለማድረግ ቦታና ጊዜ አለመስጠት፡፡ በምኞት ደረጃም ቢሆን ከመሬት ተነስተህ ብሄራዊ ቡድን መመኘት የለብህም፡፡ ለምሳሌ እኔ አሰልጣኝነትን በ150 ብር ደመወዝ ከአደይ አበባ ፋብሪካ ነው የጀመርኩት፡፡

ከዚያ ህዝብ ማመላለሻ ኮርፖሬሽን ገባሁ፡፡ በመቀጠል ጀርመን አገር ሄጄ ተምሬ መጣሁና ጭነት ማመላለሻ ኮርፖሬሽን(ጭማድ) ገባሁ፡፡ መብራት ሀይል፣ እህል ንግድ፣ ጉምሩክ እና ሌሎችም አነስተኛ ደረጃ ያላቸው ክለቦች ውስጥ ሰራሁ፡፡ ህይወትን መምራት ስላለብኝም ባገኘሁት ክለብ እሰራ ነበር፡፡ ከፍ ብዬ ተወዳድሬ ጊዮርጊስን ስላላሰለጠንኩ ‘አይ በቃ! እኔ ለአሰልጣኝነት ሙያ ብቁ አልሆንኩም፡፡’ ብዬ ህልሜን አልገታሁም፡፡ ዋናው ጠንክሮ መስራትን መቀጠል ነው፤ ስራው በራሱ የሚታይበት ጊዜ፣ ልፋትህን የሚያዩልህ እና የሚመሰክሩልህ ሰዎች ይመጣሉ፡፡ ክለቦችን የማሰልጠን አጋጣሚዎችሲገኙ ደግሞ ጠንካራ ጎኖችን ለማሳየት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ እኔ በብሔራዊ ቡድን አልተጫወትኩም፤ በተጫወቱት ጓደኞቼ ግን ቀናሁ፡፡ እዚሁ አዲስ አበባ በመምህራን ማሰልጠኛ እያለሁ መብራት ሐይል C ቡድን ተጫውቼያለሁ፡፡ ከጥቂት አመታት በኋላ ለብሄራዊ ቡድኑ የተጫወቱ ተጫዋቾች በመብራት ሐይል C ቡድን ስንመለመል እነሱ አልተመረጡም ነበር፡፡ እኔ ብመረጥም አስተማሪ ሆኜ ወደ ሰቆጣ ሄድኩ፡፡ በኋላ እነሱ ብሄራዊ ቡድን ሲጫወቱ እኔ ወሎ ምርጥ፣ ከዛም ጎጃም ምርጥ ሲቀጥልም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው የተጫወትኩት፡፡ የእግርኳስ ተጫዋችነት ጊዜን በታዋቂ ክለብ አላሳለፍኩም፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ከውስጥ በሆነ ፍቅር አሰልጣኝ መሆንን ከመፈለግ አላስቆመኝም፡፡ ፍላጎቱ ነበረኝ፤ ተማርኩ፤ በሒደት ስለ ሙያው የበለጠ እያወቅኩ መጣሁ፤ ታዲያ ማን ነው የሚያስቆመኝ? በቃ ሄድኩበት፡፡ በመንገድህ የሚመጡብህ ተቀጽላዎች ይኖራሉ፡፡ “እሱ እኮ አይችልም፤ ኳስ ነክቶ አያውቅም፡፡” የሚሉ አሉባልታዎች፡፡ ለወሬዎቹ ቦታ የማትሰጥ ከሆነ ምንም አይነት ጫና አያሳድሩብህም፡፡ እኔም ቀጠልኩበት፤ ይኸው እዚህ ደረጃ ደረስኩ፡፡ ሁሉም የተደሰተበትን ውጤት አመጣን፤ አሁን ፈጣሪህን “እዚህ አድርሰኸኛል፤ የምመኘውን ነገርም ሰጥተኸኛል፤ ለወደፊቱም አንተ ትረዳኛለህ፡፡”  በማለት እያመሰገንክ ስራህን መስራት ነው፡፡ በእርግጥ ከዛ በኋላም ቢሆን < ባጋጣሚ፣ ሳይታሰብ፣ ሳይጠበቅ……………..> እና ሌሎችም ልፋትህን የሚያጣጥሉና አዳካሚ  የሆኑ አስተያየቶች ይነሳሉ፡፡ እንዴት ነው ሳይታሰብ ወይም ሳይጠበቅ የሚባለው? ሳይታሰብ የሚደረግ ነገር አለ እንዴ!!! ስልጠና ሒደት ነው፡፡ አንድ አመት፣ሁለት አመትና ከዚያም በላይ  በተለፋበት ነገር ውጤት ሲገኝ “ባጋጣሚ የተገኘ” እንዴት ይባላል? እንዲህ ያሉ አስተያየቶች ሙያተኛውን የሚያዳክም ነው፡፡ ታስቦበት፣ ታቅዶበት፣ እንቅልፍ አጥተህ፣ ከቤተሰብህ ተለይተህ፣ ተሰድበህ፣ ተተችተህና በነዚህ ሁሉ ተበሳጭተህ የምታገኘው ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ እየታተሩ ያሉት ወጣት አሰልጣኞችም ያላቸው ነገር ላይ እየበረቱና የሚደርስባቸውን አሉባልታና ወሬ ወደ ጎን እየተዉ መቀጠል ነው ያለባቸው፡፡ ምክንያቱም አንድ ቀን የሚፈልጉት ነገር ይሳካልና፡፡ ለኔ ተሳክቶልኛል፤ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ለማግኘት ሃያ አንድ አመታት ያህል ፈጅቶብኛል፡፡ በመድሃኒአለም ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እያስተማርኩ “የአገሪቱን ቡድን ማሰልጠንማ አለብኝ!” ብዬ አሰልጣኝነትን በአደይ አበባ ቡድን ከጀምርኩ በኋላ በዋና አሰልጣኝነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ለመያዝ ሃያ አንድ አመታትን ወስዶብኝ ውጤታማ ሆኛለሁ፡፡


አሰልጣኞች ሊወጡት ከሚገባቸው ሐላፊነት ባሻገር የእግርኳስ ህብረተሰቡ፣ጋዜጠኞችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት አመለካከት እንዲቀየር ምን መሰራት አለበት ትላለህ? አንዳንድ ጊዜ በይፋእሱ ኳስ ነክቶ ሳያውቅ እንዴት አሰልጣኝ ይሆናል?” የሚሉ ጥያቄዎች ሲደጋገሙ የእግርኳስ አሰልጣኝ ለመሆን የግድ ኳስን በትልቅ ደረጃ መጫወት በመርህ የተቀመጠ ሳይንሳዊ ግኝት የሆነ እየመሰለ መጥቷል፡፡ እንደነዚህ ያሉት የህብረተሰቡ እግርኳሳዊ አስተሳሰቦች እንዲለወጡ ምን ይሰራ?

ህብረተሰቡን በተደጋጋሚ ማስተማር! ለምሳሌ እግርኳስን ተጫውቶ የማያውቅ ሰው ቴክኒክን ማስተማር ይችላል፡፡ በምን መልኩ? በቪዲዮ! በጣም አሪፍ የሆኑ አብዶኛዎችን እንቅስቃሴ በቪዲዮ እያሳየህ “ይህን አይነት ስራ እንሰራለን፡፡” ብሎ በደንብ አስረድቶ ማሰራት ይችላል፡፡ እኔ አሁን ድሪብሊንግ ለማሰራት ሜዳ ላይ ድሪብል ማድረግ አይጠበቅብኝም፤ አልችልምም፤ ቅልጥፍና ይፈልጋልና፡፡ ስለዚህ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማስመልከት ማስተማር ይቻላል፡፡ በሒደት ደግሞ ከምታለማምዳቸው ተጫዋቾች መሀል ጥሩውን ትመርጥና አንተ በምትፈልገው ተገቢ የፍጥነት መጠን እሱ እንዲያሳያቸው ማድረግም ይቻላል፡፡ በዚህም አንዱን የቴክኒክ ማስተማሪያ መንገድ ተጠቀምክ ማለት ነው፡፡ አሰልጣኙ ግዴታ በትልቅ እድሜው እየተገለባበጠ የመቀስ ምት እንዲመታ አይጠበቅበትም፡፡ ቲዎሪውን ያውቃል፤ ወደ ተግባር ለመለወጥና ለተጫዋቾች ለማስተማር በተመረጠ ተጫዋች ማሳየትና የነቃ ክትትል ማድረግ ነው፡፡ እውቀትን የምታሸጋግረው ራስህ ተግባራዊ አድርገኸው ብቻ አይደለም፤ በሌሎች መንገዶችም በማስተማር ጭምር እንጂ፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር በእያንዳንዱ ስራ ላይ ያለህ ጠለቅ ያለ እውቀትና በሒደት የተገኘ ተግባራዊ ልምድ ነው፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡን ማሳወቅና በደንብ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ሚዲያው ደግሞ ባለሙዎችን እያቀረበ መሻሻል ስላለባቸው ነገሮች መጠየቅ አለበት፡፡ እኛ ይህን በቁጥራዊ መረጃዎች  በተደገፉ ማስተማሪያ ዘዴዎች በደንብ መናገር እንችላለን፡፡ ለምሳሌ Advanced Level ላይ የደረሰ አንድ ተጫዋች በምርጥ ብቃቱ ላይ ለመገኘት 10,500 የልምምድ ሰዓት ላይ መድረስ አለበት፡፡ በBasic Level ደግሞ አንድ ከ12 አመት በታች የሆነ ታዳጊ በአመት ከ150-320 የሚደርስ የመለማመጃ ሰዓት ማግኘት አለበት፡፡ እኛ እየሰራን ያለነው እስከ 90 ሰዓት ብቻ ነው፡፡ Advanced Level ላይ ለመድረስና ምርጥ የብቃት ደረጃ (Best Performance) ላይ ለመገኘት ስንት አመት እንደሚፈጅብን ተመልከቱ፡፡ በዚህ አናሳ የልምምድ ሰዓት ተወዳዳሪነታችን አቁሟል ማለት ነው፡፡ ይሄ የሆነው ለምንድን ነው?  የራሳችን ሜዳ የለንም፤ ዘመናዊ የልምምድ መሳሪያዎች አልተሟሉም፤ ሰልጣኞቹን ልጆች ከሰኞ እስከ አርብ ድረስ ባሉት የትምህርት ቀናት አላገኛቸውም፤ ….. የሚሰሩት ቅዳሜ እና እሁድ ብቻ በመሆኑ ተፈላጊውና መደበኛ ተብሎ የተቀመጠውን ሰዓቱ ማሟላት አልተቻለም፡፡ በሌላው አለም ህጻናቶቹ ከትምህርት በኋላ በፓውዛ (Flood Light) እየሰለጠኑ ሰዓቱ የሚሞላበት ሁኔታ ይመቻቻል፡፡ በልምምዶች አማካኝነት ክፍተቶቻቸውን እየሸፈኑና ድክመቶቻቸውን እያሻሻሉ ወደ ላቀ ደረጃ ይሸጋገራሉ፡፡ ስለዚህ ከእኛ ጋር ሲገናኙ በቀላሉ ያሸንፉናል፡፡ በስልጠና አሰጣጥ ላይ ለልምምድ በምንጠቀመው የሰዓት ብዛት እንኳ አንገናኝም፡፡ እነዚህና ሌሎችም ነገሮች መሟላት እንዳለባቸው ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ Football is measurable. በተለያዩ የግምገማ ዘዴዎች በመጠቀም ተጫዋቾች ልምምድ በሰሩበት የጊዜ መጠን ተመስርተህ የመጡትን መሻሻሎች ትመዝናለህ፡፡ ተጫዋቾቻችንን በአመት ስንት ጊዜ ስራቸውና እድገታቸው ላይ ምዘና እናደርጋለን? ለአስር አመት የሚሆን ጊዜ የብቃታቸውን እድገት ለክተንላቸው ወይም ገምግመንላቸው አናውቅም፡፡ ምን እንደሚመዘንም ላንረዳ እንችላለን፡፡ ከመሰረቱ በእንደነዚህ አይነቱ አሰራር ውስጥ ካልገባን እግርኳሱን ልናሳድገው አንችልም፡፡ ይህን ግንዛቤ ለመፍጠር ደግሞ ባለሙያዎችን ማነጋገር፣ እውቀታቸውን እንዲያካፍሉ መጋበዝ፣ውይይት ማድረግና ተገቢ ክርክሮችንም ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ በቃ በአጭሩ ለመግለጽ ከተቀመጠው ወጪና ሌላው አለም ከሚሰራው በተዛነፈ መልኩ ነው እኛ እየሰራን ያለነው፡፡ ሆኖም በመጠኑ ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለመስራት ስትሞክርም “ይሄ ደግሞ ከየት ያመጣው አሰራር ነው!” ተብለህ ትተቻለህ፡፡ ይህን ለማስቀረት ሳይደክሙ መስራትን ይጠይቃል፡፡