ከፍተኛ ሊግ | ሀላባ ከተማ አንደኛውን ዙር በመሪነት አጠናቋል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በ8ኛው ሳምንት ዱራሜ ላይ በሀምበሪቾ እና ሀላባ ከተማ መካከል የተካሄደውና በሀላባ የ 1-0 መሪነት በ51ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጦ የነበረው ጨዋታ ዛሬ ቀሪ 40 ደቂቃ በሀዋሳ ተካሂዶ ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት ተጠናቋል። ሀላባ ከተማም በድሉ ተጠቅሞ የምድብ ለ መሪ በመሆን የውድድር ዘመን አጋማሹን አገባዷል።

በመጀመርያው ጨዋታ ሀላባ ከተማ በ42ኛው ደቂቃ ላይ አምበሉ አዩብ በቀታ ባስቆጠራት ግብ በመምራት ላይ ሳለ 51ኛው ደቂቃ ላይ በደጋፊዎች በተነሳ ሁከት መቋረጡ የሚታወስ ነው። በእለቱ ጨዋታውን በሰላም ለማጠናቀቅ ጥረት ቢደረግም የፀጥታ ኃይሎች ኃላፊነት አንወስድም በማለታቸው በኮሚሽነር ወ/ሚካኤል መስቀሌ አማካኝነት ተቋርጧል፡፡ የጨዋታው ዋና ዳኛ የነበሩት ሄኖክ አክሊሉ እና ኮሚሽነሩ ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት በባለሜዳው ሀምበሪቾ ላይ ቅጣት ተወስኖ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ሳይደረግ ቆይቶ ዛሬ በሀዋሳ ስታድየም ቀሪው 40 ደቂቃ ተካሂዷል።

በዛሬው ጨዋታ ላይ ሀምበሪቾዎች ኳስን ይዞ በመጫወት እና ወደ ግብ በመድረስ የተሻለ አጋጣሚን ሲፈጥሩ ሀላባዎች በመስመር ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ አድርገዋል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ሰይድ ግርማ ከቅጣት ምት ያሻገራትን ኳስ እንዳለ ዮሀንስ በግንባሩ ገጭቶ የወጣችበት አጋጣሚ የሀምበሪቾዎች መልካም አጋጣሚ የነበረች ሲሆን በሀላባ በኩል 67ኛ ደቂቃ ላይ አቦነት ገነቱ በቀኝ መስመር እየገፋ ገብቶ ለስንታየሁ መንግስቱ ሰጥቶት ስንታየሁ በቀጥታ አክርሮ ወደ ግብ መትቶ መክብብ ደገፉን ተክቶ ከመጀመሪያው ጨዋታ ዛሬ ግብ ጠባቂ የሆነው ሄኖክ ወ/አገኘው እንደምንም መልሶበታል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ተመስገን ይልማ በቀኝ በኩል አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ አቦነህ ገነቱ ቢያገኛትም ወደ ግብነት መለወጥ ሳይችል የወጣችበት ኳስም ተጠቃሽ ነበረች።

በመጨረሻዎቹ 5 ደቂቃዎች መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት ሀላባዎች ግቧን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ሲሰምር ሀምበሪቾዎች አቻ ለመሆን ተጭነው መጫወት ቢችሉም ግብ ሳያስቆጥሩ ጨዋታው በሀላባ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎም ሀላባ ከተማ ነጥቡን 28 በማድረስ ዲላ ከተማን በግብ ልዩነቶች በልጦ የከፍተኛ ሊጉን ምድብ ለ መሪ በመሆን የመጀመርያውን ዙር አጠናቋል።