ሶከር ሜዲካል | ዶፒንግ እና እግርኳስ

በስፖርት ህክምና እና ተጓዳኝ ዘርፎች ስር ያሉ እና ከእግርኳሱ ጋር ቁርኝት ያላቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በሶከር ሜዲካል አምዳችን ስናስነብባችሁ ቆይተናል። በዛሬው ፅሁፍ ደግሞ አበረታች መድሃኒቶችን መጠቀም (ዶፒንግ) በእግርኳሱ ላይ ያለውን ተፅዕኖ እንመለከታለን።

ዶፒንግ የሚለው ቃል የተለያዩ በህግ የተከለከሉ መድሃኒቶች እና ንጥረ-ነገሮችን በመውሰድ እንቅስቃሴንና ጊዜያዊ አቅምን ለማሳደግ የሚደረግ ጥረት ይጠቁማል። የሚወሰዱት ንጥረ-ነገሮች ህገወጥ የሚያስብላቸው ሶስት መስፈርቶች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የሚገኙ ከሆነ ከዶፒንግ ተርታ ይፈረጃሉ ማለት ነው፡፡

እነዚህ ባህርያት፡

1) አቅምን ማሳደግ
2) የአትሌቱ ጤንነት ላይ እክል መፍጠር
3) የስፖርቱን አላማ/መንፈስ መፃረር
ናቸው፡፡

የተከለከሉ መድሃኒቶችን በውድድር ወቅት መውሰድ ከጥንታዊ ግሪክ ጀምሮ እንደ ነበረ ይነገራል፡፡ ይሁን እንጂ በአለም አቀፍ ደረጃ ይህንን ለማስቆም ደንብ ማውጣት የተጀመረው በ1920ዎቹ ነው፡፡ በአብዛኛው ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉት ስቴሮይድ የተሰኙት የመድሃኒት አይነት ናቸው፡፡ የስቴሮይዶች ጥቅም ስፖርተኞች ያለድካም ለረጅም ጊዜ እንዲለማመዱ ከማስቻልም በላይ ጡንቻዎች እንዲዳብሩ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የደም ዝውውርን የሚጨምሩ እና የሰውነት ክብደትን ለመቆጣጠር የሚረዱ መድሃኒቶች አሉ፡፡

ከሚሰጡት ጊዜያዊ ጥቅም ባሻገር ግን የተለያዩ አሉታዊ ተጽዕኖም ያሳድራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ ሱሰኝነት ነው፡፡ ለአንድ ጊዜ ተብሎ የተጀመረ ነገር ማቆም እስኪያቅት ድረስ ያስቸግራል፡፡ ጉዳቱ እዚህ ላይ የሚያበቃ አይደለም፡፡ መድሃኒቱ ለአንድ የሰውነት አካል ጥቅም ቢሰጥም በሌላኛው ላይ ደግሞ ጉዳት ሲያስከትል ይስተዋላል፡፡የእግር ኳስ የበላይ አካል ፊፋ የዚህን ችግር አሳሳቢነት በመረዳት በ1966 ዶፒንግን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግን አርቅቆ ነበር፡፡ ይህንንም ለማድረግ ያነሳሳው ስፖርቱ በእንደዚህ አይነቶቹ ህገ-ወጥ ተግባራት እንዳይበላሽ በማሰብ ነው፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ዋናው ስትራቴጂ ደግሞ ስለጉዳዩ ማስተማር እና በተለያዩ ወቅቶች ተጫዋቾችን መመርመር ነው፡፡

ፊፋ ከአለም አቀፉ የዶፒንግ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ World Anti-Doping Agency (WADA) ጋር አንድ ላይ በመሆን በቁጥር እና ምርምር የተደገፉ ጥናቶችን በማድረግ እና ምርመራዎችን በማከናወን ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል፡፡ በየዓመቱም የማጣራት ምርመራዎቹ አካል ከሆኑ ስፖርቶች መካከል እግር ኳስ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስመርመር ላቅ ያለውን ድርሻ ይይዛል፡፡

ዶፒንግ ከእግር ኳስ ይልቅ እንደ አትሌቲክስ እና ብስክሌት ባሉ የግል ስፖርቶች ላይ በተደጋጋሚ ሲከሰት ይስተዋላል፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታትም በአትሌቲክስ በርካታ ውዝግቦችን አስነስቷል፡፡ የእንግሊዙ ጋርዲያን ኢትዮጵያ ላይ አደረኩት ባለው ጥናት መሰረት በግሸን መድሃኒት ቤት ኢሪይትሮፖዬቲን የተሰኘ የቀይ ደም ሴሎችን ቁጥር በመጨመር ኦክስጅን በላቀ ሁኔታ በደም ውስጥ እንዲዘዋዋር የሚያደርግ መድሃኒት ለአትሌቶች ስለመሸጡ ዘግቦ እንደነበረ ይታወሳል፡፡

ያልተፈቀዱ መድሃኒቶችን መጠቀም ለተለያዩ ቅጣቶች የሚዳርግ ሲሆን ፊፋም በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ህግጋትን አዘጋጅታል፡፡ ቅጣቶቹ ተጫዋችንም ሆነ ክለብን ሊመለከቱ የሚችሉ ሆነው ከገንዘብ ቅጣት እስከ ከጨዋታ ሜዳ መታገድ ያሉትን ያካትታሉ፡፡ ስፖርተኞች ማንኛውንም አይነት መድሃኒት ከመውሰዳቸው በፊት ለሃኪሞች መንገር እና የተከለከለ ንጥረ-ነገር በውስጡ መያዝ እና አለመያዙን እንዲያጣሩ የሚመከረውም ለዚህ ነው፡፡

ወደ ሀገራችንም ስንመለስ ምንም እንኳን በእግር ኳሳችን ይህ ነው የሚባል ውዝግብ ባያስነሳም ስለዶፒንግ ግንዛቤን መፍጠር የፌደሬሽኑ እንደዚሁም የክለቦች ኃላፊነት ነው፡፡ ሚዲያውም በተለያዩ ዝግጅቶች ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ የመዳሰስ ግዴታ አለበት፡፡ ተጫዋቾችም በበኩላቸው እንደዚህ ካለው ጎጂ ተግባር እራሳቸውን ሊያርቁ እና ያላቸውን አቅም ብቻ በመጠቀም በርተትው ለተሻለ ውጤት ሊሰሩ ይገባል፡፡