የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እንቆቅልሽ

የኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በቡሩንዲ እየተከሄደ በሚገኘው የሴካፋ ዋንጫ ከምድቡ ማለፍ ተስኖት በጊዜ ከውድድሩ ውጭ በመሆን ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል። በተለይ በመጀመርያ የምድብ ጨዋታው ሶማልያን 3-1 በመርታት አጀማመሩን መልካም ቢያደርግም የቡድኑ የፓስፖርት ጉዳይ ሲያስፈፅሙ በነበሩ ግለሰቦች ስህተት ምክንያት የሴካፋ ዲሲፒሊን ኮሚቴ በጨዋታው ሐት-ትሪክ የሰራው መስፍን ታፈሰን ጨምሮ ሦስት ተጨዋቾች ውድድሩ ከሚፈቅደው የእድሜ ገደብ በላይ ተጫውተዋል በሚል በወሰነው ውሳኔ መሰረት የ3-0 ፎርፌ ተሸናፊ ሆነዋል። በቀጣይ ባደረጋቸው ጨዋታዎችም ከኬንያ ቻ ተለያይቶ ፣ በቡሩንዲ ተሸንፎ ከውድድር ውጪ ሆኗል።

ብሔራዊ ቡድኑ ከውድድሩ በጊዜ ለመሰናበቱ ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም የሦስቱ ተጨዋቾች ከቡድኑ ውጭ መሆን ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርጓል። ከእድሜ ገደባቸው በላይ ተጫውተዋል ከተባሉት ተጫዋቾች መካከል ሙሴ ከበላ እና መስፍን ታፈሰ ዕድሜያቸው ለጨዋታው ብቁ ቢያደርጋቸውም በአሰራር ስህተት ምክንያት  አለመጫወታቸው የፈጠረባቸውን ጉዳት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

” ነገሩን ስሰማ በጣም ደንግጫለሁ። በጥሩ ሁኔታ አሸንፈን በጥሩ ስሜት ላይ ሆነን በነጋታው ይሄንን ሰማን ፣ መጫወት እየቻልን በሰህተት ይህ መሆኑ በጣም ያሳዝናል። በጣትም ትልቅ ነው ቁጭት የፈጠረብኝ። አሁን ለሀገሬ የመጫወት እድል ብነፈግም በቀጣይ ዳግመኛ የብሔራዊ ቡድን ማልያ እንደምለብስ እርግጠኛ ነኝ” ያለው አማካዩ ሙሴ ሲሆን ” መጫወት እየቻልን በቡድኑ አመራሮች ስህተት ምክንያት እንዲህ በመሆኑ አዝኛለው። በተለይ እኔ በአንድ ጨዋታ ሦስት ጎል አስቆጥሬ በከፍተኛ ተነሳሽነት የውድድሩ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ለማጠናቀቀ እያሰብኩ ባለሁበት ሰዓት እንዲህ ያለ ነገር ሲሰማ በጣም ነው የተጓዳሁት። በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት ከ20 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን በመጫወት ዳግመኛ የሀገሬን ማልያ እንደምለብስ ሙሉ እምነት አለኝ” ያለው ደግሞ ሶማልያ ላይ ሐት-ትሪክ የሰራው መስፍን ታፈሰ ነው።

ከተጫዋቾቹ የተሰማውን ቅሬታ ይዘን በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸውን የፌዴሬሽን አካላትን ሀሳብ ለመስማት ባደረግነው ጥረት የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አባል እና ህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ ነስረዲን አብዱራሂም (ዶ/ር) የሚከተለውን ማብራርያ ሰጥተውናል።

” ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን አስመልክቶ ተጫዋቾቹ በሜዳ ላይ ተመርጠው ወደ ህክምና ኮሚቴው ከመጡ በኋላ አብዛኛዎቹ  የ17 አመት በታች የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የተመረጡ ስለሆነ ከ6 ወር በፊት የነበረውን MRI ምርመራ ይዘን ሌሎች አዲስ የመጡትን በማካተት በድጋሚ 25 ተጫዋቾችን በመያዝ በህክምና ቡድኑ አማካኝነት MRI ምርመራ ተደርጓለ። ለፌዴሬሽኑም ውጤቱን በዝርዝር ከደብዳቤ ጋር አባሪ አድርገን ሰተናል። እንግዲህ የህክምናው ምርመራ እዚህ ላይ የሚያበቃ ይሆናል። ቀጥሎ ያለው ኃላፊነት ፓስፖርቱን የሚያወጡት የፕሮቶኮል ፣ የቴክኒክ ክፍል እና በአጠቃላይ የፅህፈት ቤቱ ሰራተኞች ነው። 

” የሁሉም እድሜ በMRI 16 ሆኖ ነው የወጣው። ይህ ማለት ደግሞ እስከ 2019 መጨረሻ ድረስ መጫወት የሚችሉበትን ዕድሜ ነው መርምረን ያሳለፍነው። ታዲያ ፓስፖርት ሲወጣ 2002 (እኤአ) ሆኖ መውጣት ሲገባው የሦስቱ ተጨዋቾች ብቻ 2001 (እኤአ) ሆኖ ወጣ። በዚህ ምክንያት ተጫዋቾቹ ከውድድሩ ውጭ ሆኑ። ሀገሪቱም እንድትቀጣ ያደረገው ምክንያት የተፈጠረው በዚህ ሁኔታ ነው።
ስለዚህ ስህተቱን የሚወስደው በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት አካባቢ ያሉ ናቸው። ምክንያቱም ችግሩ የፓስፖርት አወጣጥ ላይ ነው። መቼም ፓስፖርት ማውጣት የሀኪሞች ስራ አይደለም። እኛ የተሰጠንን እድሜ መሰረት አድርገን የህክምናውን ምርመራ ልከናል ። የተላከውን አይተው ፓስፖርቱን በጥንቃቄ ማውጣት የነበረባቸው ኃላፊነቱ የተሰጣቸው ናቸው። 17ቱን ተጨዋቾች 2002 ብሎ አውጥቶ 3 ብቻ 2001 ብሎ ማውጣት ስህተቱ ይሄ ነው። ”

ይህን አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ አድርጎ በአስቸኳይ ችግሩን አጣርቶ አስፈላጊዉን እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ተሰቷል ።
በህክምና ኮሚቴው ጣት የተቀሰረበት የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ በበኩላቸው ” የተፈጠረው ስህተት በየትኛው ወገን እንደሆነ እያጣራን ነው። ችግሩ ውስብስብ ስለሆነ አጣርተን ችግሩን የፈጠረውን አካል ለይተን አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን።” ብለዋል ።