ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ደደቢት ወደ ድል ሲመለስ አዳማ ፣ መከላከያ እና ሀዋሳም አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ትላንት እና ዛሬ ተካሂደው ደደቢት፣ መከላከያ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ አሸንፈዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-2 አዳማ ከተማ

ቅዳሜ በ08:00 አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የተደረገው ጨዋታ በአዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የበላይነታቸውን ያሳዩት አዳማ ከተማዎች በኤሌክትሪክ የሜዳ አጋማሽ አመዝነው ቢንቀሳቀሱም የግብ ክልል ጋር ሲደርሱ ግን መቀዛቀዝ ሲታይባቸው ተስተውሏል። የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ሰርካዲስ ፣ ሴናፍ እና ይታገሱ በግል የኤሌክትሪክን የተከላካይ መስመርን ሲፈትኑ የዋሉ ሲሆን በጨዋታው ድንቅ የነበረችው ሰርካዲስ ጉታ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ያገኘችውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት አዳማ ከተማን ቀዳሚ አደርጋለች። በ41ኛው ደቂቃ ደግሞ ሴናፍ ዋቁማ ሁለተኛውን አክሎ የመጀመርያው አጋማሽ በአዳማ 2-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ኤሌክትሪኮች ተሻሽለው የቀረቡ ሲሆን ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይ አለምነሽ ገረመው በግሏ የግብ እድል ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት በጉልህ የሚታይ ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይም ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት አለምነሽ አስቆጥራ ልዩነቱን ማጥበብ ችለዋል። ከጎሉ በኋላ ኤሌክትሪኮች አቻ ለመሆን ረጅም ደቂቃዎች ቢቀራቸውም የጠራ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአዳማ በኩል በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ዮዲት መኮንን ከርቀት የሞረችውና የግቡን አግዳሚ ለትሞ የተመለሰው ኳስ የሚጠቀስ ሙከራ ነበር።

ሲዳማ ቡና 0-5 ደደቢት 

(ቴዎድሮስ ታከለ)

ቅዳሜ ረፋድ 4፡00 ይርጋለም ላይ መሪው ደደቢትን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና 5-0 በሆነ ውጤት ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡ ሲዳማ ቡና ያለፈውን አንድ አመት ዋና አሰልጣኝ ከነበረው ፍሬው ኃይለገብርኤል ከሁለት ሳምንት በፊት የተለያየ ሲሆን በምክትሎቹ አሰልጣኞች እየመራም ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሜዳ ገብቷል ፡፡ ፍፁም የደደቢት የጨዋታ ብልጫ በታየበት እና አማካይዋ ሰናይት ቦጋለ በሜዳ ላይ ደምቃ በታየችበት ጨዋታ ገና በጊዜ ነበር ግብ ማስቆጠር የጀመሩት። 7ኛው ደቂቃ ላይ በሲዳማ የግብ ክልል የተሰጠውን የቅጣት ምት ሰናይት ቦጋለ ከመረብ አሳርፋ ደደቢትን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች፡፡ ተጭነው በመጫወት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ደደቢቶች 41ኛው ደቂቃ ላይ በትዕግስት ዘውዴ፣ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ሎዛ አበራ አክርራ በመምታት አስቆጥራ በደደቢት 3-0 መሪነት እረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ ሲዳማ ቡናዎች ግብ ጠባቂዋን በመቀየር ወደ ሜዳ ቢገቡም ተጨማሪ ግበ ከመቆጠር መታደግ አልቻሉም። 50ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ ድንቅ የነበረችሁ ሰናይት ቦጋለ የግል ጥረቷን ተጠቅማ ወደ ሳጥን በመግባት ግብ አስቆጥራ መሪነታቸውን ወደ አራት ስታሳድግ በ86ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከሰናይት ቦጋለ ያገኘችሁን ኳስ ሎዛ አበራ አስቆጥራ ጨዋታው በደደቢት 5-0 ተጠናቋል።

መከላከያ 3-0 ድሬዳዋ ከተማ

ኢትዮጵያ ቡና ከጅማ አባጅፋር ከመጫወታቸው ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ስታድየም 08:00 ላይ በተደረገው ጨዋታ መከላከያ 3-0 ማሸነፍ ችሏል። የመከላከያ የበላይነት በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ያሳየውን ብልጫ ተጠቅሞ ግበ ለማስቆጠር እስከ መጨረሻው ደቂቃ የተጠበቀ ሲሆን በ45ኛው ደቂቃ ብሩክታዊት አየለ ባስቆጠረችው ጎል መከላከያ 1-0 እየመራ እረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስም በተመሳሳይ መከላከያዎች ብልጫ የወሰዱ ሲሆን በተቃራኒው ድሬዳዋ ከተማዎች አመዛኙ ክፍለ ጊዜን በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ ለማሳለፍ ተገደዋል። ከርቀት ወደ ግብ ከሚመቱ ኳሶች በስተቀርም የጠራ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። በ80ኛው ደቂቃ ሔለን ሰይፉ ሁለተኛውን ጎል ስታስቆጥር 90ኛው ደቂቃ ላይ ምህረት ታፈሰ የማሳረጊያውን አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 3-0 አሸናፊነት ተገባዷል።

ሀዋሳ ከተማ 4-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

(ቴዎድሮስ ታከለ)

ዛሬ 9 ሰአት ላይ በሜዳው ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው ሀዋሳ ከተማ በዚህ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሜዳው ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡ ግብ ባልተስተናገደበት የመጀመርያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተሻለ እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን የግብ እድል በመፍጠር ረገድ ደግሞ ሀዋሳዎች የተሻሉ ነበሩ። በ15ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ ሳጥኑ ውስጥ ገብታ ከግብ ጠባቂዋ ጋር ተገናኝታ ያመከነችሁ ኳስ በሀዋሳ በኩል ፣  27ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሄም እና ብዙዓየሁ ታደሰ በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው ለኪፊያ አብዱራህማን የሰጧትን ኳስ ኪፊያ መታ አባይነሽ ያዳነችበት ኳስ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የመጀመርያዎቹ ሙከራዎች ነበሩ። በ38ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳዋ ተከላካይ አረጋሽ ፀጋ በሳጥን ውስጥ በእጅ ነክታለች በማለት ጊዮርጊሶች ፍ/ቅጣት ምት ይገባናል በማለት ዳኛዋ ላይ ተቃውሞን አሰምተዋል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ ቅያሪ ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች ፍፁም ብልጫ የወሰዱበት እና በግብ የተንበሸበሹበት አጋማሽ ሆኖ አልፏል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ የሰጣቻትን ኳስ እታለም አመኑ ከመሀል ሜዳው ከተጠጋ ርቀት አክርራ በመምታት አስደናቂ ግብ አስቆጥራ ሀዋሳን ቀዳሚ አድርጋለች። እታለምም ግቡን ካስቆጠረች በኃላ ተንበርክካ አልቅሳለች። በ61ኛው ደቂቃ ላይ ከቢ ቡድን ያደገችው እና ተቀይራ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ የቻለችሁ ቅድስት ቴቃ ያቀበለቻትን ኳስ ትርሲት መገርሳ ስታስቆጥር 67ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሌላዋ ተቀይራ ወደ ሜዳ የገባችው ነፃነት መና ከምርቃት የተሻገረላትን ኳስ ተጠቅማ ሶስተኛዋን ኳስ ከመረብ አሳርፋለች። ጭማሪ ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከመሀል ሜዳው አጋማሽ ወደ መስመር ባጋደለ መልኩ ልደት ቶሎአ እየገፋች በመሄድ በቀጥታ ወደ ግብ የላከቻት ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብነት ተለውጣ የሀዋሳን የግብ ብዛት ወደ አራት አሰመድጋለች።  ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ትመር ጠንክር የሀዋሳን ተከላካይ መስመር ስህተትን ተጠቅማ ጊዮርጊስን ከሽንፈት ያልታደገች ግብ ከመረብ አሳርፋ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጌዲኦ ዲላ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ዲላ ላይ ዛሬ ሊደረግ የታሰበው የጌዲኦ ዲላ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ሳይጀመር በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ወደ ነገ ጠዋት 3፡00 ዞሯል፡፡