ወልዋሎ ሮቤል ግርማን ሲያሰናብት ከሙሉዓለም ጋር ሊለያይ ተቃርቧል

ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በክረምቱ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ሮቤል ግርማን ሲያሰናብት እስካሁን ወደገቡድኑ ካልተመለሰው ሙሉዓለም ጥላሁን ጋር የመለያየቱ ነገር እየቀረበ መጥቷል። የክለቡ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ሮቤል ግርማ ሁለት ጊዜ የዲሲፕሊን ችግሩን እንዲቀርፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ማሻሻል ባለመቻሉ ለማሰናበት መወሰናቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። በክለቡ የሚታዩ የዲሲፕሊን ችግሮች ላይም በቀጣይ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልፀዋል።

በተያያዘ ወደ ወልዋሎ ሳይመለስ ከሳምንት በላይ ያስቆጠረው ሙሉዓለም ጥላሁን በሳምንቱ መጨረሻ የክለቡ አመራሮች እንደሚያናግሩት መግለፁን መዘገባችን የሚታወስ ነው። ሆኖም ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው እስካሁን ከአመራሮቹ መጥቶ ያናገረው እንደሌለ የገለፀ ሲሆን ከክለቡ አካባቢ ባገኘነው መረጃ ተጫዋቹ ከወልዋሎ ጋር ሊለያይ መቃረቡ ተነግሯል።