ኢትዮጵያ ዋንጫ | የተሳካ የግብ ጠባቂ ቅያሪ አፄዎቹን ለድል አብቅቷቸዋል

ጎንደር ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ጨዋታ ፋሲል ከተማ ከ አዳማ ከተማ መደበኛውን ክፍለ ጊዜ አቻ ተያይተው በመለያ ምቶች ፋሲል 6-5 በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴ ቢሳዩም ፋሲል ከተማ በተሻለ ወደግብ መድረስ ችለው ነበር። በ9ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ ወደ ግብ  የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እና በ45ኛው ደቂቃ ላይ የግብ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ በፋሲል በኩል የሚጠቀስ ሲሆን በአዳማ በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ሳያደርጉ ነበር የመጀመሪያው አጋማሽ የተጠናቀቀው።

በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከተማ የተሻለ በመጫን ቢጀምርም አብዛኛው የተፈጠሩት እድሎች ከጨዋታ ውጪ ነበሩ። በ54ኛው እና 55ኛው ደቂቃ ኤርምያስ ኃይሉ ከሰዒድ ሁሴን የተሻገረለትን ኳስ ሳይጠቀምባቸው የቀሩት እንዲሁም ኤፍሬም አለሙ በ75 እና 78ኛው ደቂቃ ላይ ያመከነው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ የሚጠቀሱ ናቸው። በአዳማ በኩል ደግሞ በ57ኛው በረከት ደስታ እንዲሁም በ87ኛው ደቂቃ ሚካኤል ጆርጅ በጭንቅላት ገጭቶ የሞከረው ኳስ የሚጠቀስ ነው። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ቴዎድሮስ ጌትነት ሚኬል ሳሚኬን ተክቶ የገባ ሲሆን ለፋሲል ድልም አስተዋፅኦ አድርጓል።

ጨዋታው ያለ ግብ በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አሸናፊውን ለመለየት በተሰጡ የመለያ ምቶች ፋሲል 6-5 ማሽነፍ ችሏል። ግብ ጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነትም ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ለቡድኑ ድል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

አስተያየቶች

ቴዎድሮስ ጌትነት 

ቅያሪው ታስቦበት የተደረገ ከመሆኑ አንፃር በጥሩ ስሜት ነው የገባሁት። ፍፁም ቅጣት ምት ማዳን ቢከብድም ደጋፊው የሚፈልገውን ነገር አሳክተን መውጣት ችለናል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ 

ጨዋታው ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው በጥንቃቄ የተሞላ ነበር። ከጥንቃቄው ውጭ ግን ብዙ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለን ነበር። ከዛም ወደ መለያምት ደርሰናል። በተለመደው መልኩ ፈጣሪ ረድቶን አሸንፈን ወጥተናል። የቴዲ ቅያሪ ታስቦበት የተደረገ ከመሆኑ አንፃር ስኬታማ ነበርን። ቴዲም ተስፋ በቆረጥንበት ስአት ተአምር ሰርቶ እንድናሸንፍ ረድቶናል።