የእግርኳሳችንን ህልውና እንታደግ !

የኢትዮጵያ እግርኳስ በእጅግ ጥቂት ከፍታዎች እና እጅግ ውስብስብ ችግሮች እየተገመደ ያለንበት የዝቅጠት ደረጃ ላይ ደርሰናል። እግርኳሳችን ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩም በአስተዳደራዊ፣ በሜዳ ላይ እና በአጠቃላይ ስርዓቱ ላይነሳ በሚመስል መልኩ እየተቀበረ ያለ ይመስላል። ባለፉት አምስት አመታት ለእግርኳሱ ቅርብ ለሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ እግርኳሳችን አሁን ያለበት ደረጃ “አሳሳቢ” ከሚባለው መጠርያ እጅግ በራቀ መልኩ ወደ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ማባባሻነት እየተሸጋገረ ነው ብላ ታምናለች።

የዚህ ፅሁፍ አላማ ለሚመለከታቸው አካላት በአጠቃላይ እግርኳሳዊ ስነ-ስርዓት እንዲከበር ለማሳሰብ ነው። በዚህ አመት ብቻ ከእግርኳስ መሰረታዊ ስርዓቶች ያፈነገጡ በርካታ አንገት አስደፊ እና የእግርኳስን ህልውና የሚፈታተኑ ስርዓት አልበኝነቶች ፣ ቅሌቶች እና ድራማዎችን አስተናግደናል። በሜዳ ላይ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና የቡድን አመራሮች ዋንኛ ስራቸውን ረስተው የስርዓት አልበኝነት አስጀማሪ እና መሪ ተዋናይ ሆነዋል ፤ ደጋፊዎች ከመሰረታዊ የክለብ ደጋፊነት ባህርያት ተቃራኒ የሆነና ለቁጥጥር አስቸጋሪ የሆነ የፅንፈኛ ብሔርተኛ ተኮር አደጋገፍን እያሳዩ በሚድያም “ደግ አደረጋችሁ” እየተባሉ እዚህ ደርሰዋል ፤ እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመበት ዋንኛ አላማ አፈንግጦ በስልጣን ሽኩቻ 8 ወራትን አስቆጥሯል ፤ መገናኛ ብዙሀኑ እግርኳሳዊ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮችን ማራገብ ስራው ሆኗል ፤ ሙሉ ለሙሉ ለማለት በሚቻል ሁኔታ እግርኳሱን በፋይናንስ የሚደጉመው መንግስት በዝምታ ነገሮችን እየተመለከተ ይገኛል። እነዚህና መሰል ችግሮች ወቅታዊ መነጋገርያ ርዕስ ከመሆን ሳያልፉ ተድበስብሰው ሲቀሩ እና ምንም አይነት የእርምት እርምጃ ሳይወሰድባቸው ሲቀር መመልከት እንደ ሶከር ኢትዮጵያ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ወደ ዛሬው ዋናው የፅሁፋችን ሀሳብ ስናመራ በዚህ ወር በፕሪምየር ሊጉ ብቻ በሁለት አጋጣሚዎች (ወልዲያ እና ወልዋሎ) የተከሰቱት ዳኛን የመደብደብ አሳፋሪ ትዕይንቶች ከላይ እንደተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ ከጊዜያዊ መነጋገርያነት ማለፍ ካልቻሉ እና እንደከዚህ ቀደሙ በቸልተኝነት ከተውነው በየሜዳው ወደሚታይ ተቀባይነት ያለው ህጋዊ ተግባርነት መሸጋገሩ እንደማይቀር ሶከር ኢትዮጵያ አጥብቃ ለማሳሰብ ትወዳለች። 

በእግርኳስ እጅግ ወሳኙ አካል የሆነው ዳኛ የማይከበርበት ስፖርት “እግርኳስ” የሚል መጠርያ ሊያገኝ አይገባውም። ዳኛን መደብደብ ተራ እግርኳሳዊ ክስተት ሳይሆን የእግርኳስን ህልውና በእጅጉ የሚፈታተን ተግባር ነው። ተግባሩን ማንም ፈፀመው ማንም የሚወገዝ ብቻ ሳይሆን የማያዳግም እርምጃ የሚያስወስድ እጅግ ከባድ ጥፋት ነው። ዳኞችን መደብደብ ቀርቶ ውሳኔው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ማዋከቦች ፣ ዘለፋዎች እና ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶች በቸልታ ሊታለፉ የሚገባቸው አይደሉም። ነገር ግን ከመደብደብ በታች ያሉ ተግባራት በተደጋጋሚ በእግርኳሳችን ሲከሰቱ እንደትክክለኛ ተግባር ስናስተናግደው በመኖራችን አሁን እየተደጋገመ የሚገኘው ዳኛን የመደብደብ ድርጊት እንደ በጎ ልማድ ከመቆጠሩ በፊት እልባት እንዲበጅለት ሶከር ኢትዮጵያ በፅኑ ታሳስባለች።

የእግርኳሳችን አስተዳዳሪ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እየተከሰቱ ያሉ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ ጥሰቶችን የሚቆጣጠርበት ወጥ ፣ አሻሚ ያልሆነ ፣ በዝርዝር ተብራርቶ የተቀመጠ ህግ እና ደንብ በማዘጋጀት ኮስታራ በሆነ መልኩ መተግበር ይጠበቅበታል። የዳኞች ኮሚቴ የሀገራችንን እግርኳስ ያገናዘበ ተጨማሪ ህግ እና ደንቦች እንዲወጡ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። ተግባሩ ” በዲሲፕሊን ኮሚቴ የተወሰነን ቅጣት መሻር ” እየሆነ የመጣው የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አወቃቀር ለሙስና እና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍት በመሆኑ በአግባቡ ሊፈተሽ ይገባዋል። የዳኞች እና ኮሚሽነሮች ማህበርም ዳኞች እንደ ሰብዓዊ ፍጡር፣ ህጋዊ ዜጋ እና ባለሙያ ሊሰጣቸው የሚገባቸው ክብር እና መብት ሳይሸራረፍ እንዲሰጣቸው እስከመጨረሻው መታገል እና ከላላ የሚሰጡ ተጨማሪ ህጎች እንዲወጡ በፌዴሬሽኑ ላይ ጫና ማሳደር ይኖርበታል ብለን እናምናለን።

እንደ ሶከር ኢትዮጵያ እምነት ዳኛን መደብደብ ጨምሮ እየተከሰቱ የሚገኙ ውንብድናዎች መንስዔ ክለቦቻችን፣ ፌዴሬሽኑ፣ ደጋፊው ፣ መገናኛ ብዙሀኑ እና አጠቃላይ እግርኳሱ የሚመራበት መንገድ “እግርኳሳዊ” አለመሆን ነው። የእግርኳስ ህልውና ጠፍቶ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ብሔር ተኮር ችግር ህይወት አግኝቶ (ነፍስ ዘርቶ) እየተመለከትን በቀላሉ መፍትሔ መጠበቅ ከባድ ነው።

ከ95% በላይ የሚሆኑ ክለቦች የተመሰረቱበት አላማ በግልፅ የማይታወቅ ፣ መንግስታዊ አወቃቀር እና የብሔር ማንነትን ብቻ ተከትለው የተቋቋሙ በመሆናቸው ” እግርኳሳዊ መንፈስን የተላበሱ ” ፣ ትክክለኛ የክለብ ቁመናን የያዙ ናቸው ብለን አናምንም። በዚህም ምክንያት እያንዳንዱ እግርኳሳዊ ክስተት እና ውሳኔ “በብሔሩ ፣ በአኗኗሩ እና በፖለቲካዊ አመለካከቱ ምክንያት የተሰነዘረበት ቡጢ ” አድርጎ የመመልከት ልማድ በክለቦቻችን ላይ ተንሰራፍቷል። ይህ ዝንባሌ ደግሞ ዳኞች ጨዋታውን በአግባቡ ተቆጣጥረው ፣ ትክክለኛ ውሳኔዎችን በወሰኑ ቅፅበት ድብደባ ሽልማታቸው እንዲሆን አድርጓል። ከክስተቱ በኋላ ደግሞ ክለቦች በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ ችግሩ እንዳይባባስ ከመስራት ይልቅ “ክለባችንን የማይወክሉ ግለሰቦች ያደረጉት ተግባር ነው” በሚል ተልካሻ ምክንያት ተድበስብሶ ሲያልፍ እያስተዋልን እንገኛለን። የክለብ አመራሮች ከተቻለ በራሳቸው ስህተት የሚፈጠሩ ችግሮችን ወደ ሌሎች አካላት በመቀሰር ክለባቸው የጥቃት ኢላማ እንደተደረገ አስመስሎ ህዝብን ከማነሳሳት ተግባር ቢታቀቡ ፤ ካልቻሉ ደግሞ በእግርኳሳዊ መንገድ ክለቡን ሊያስተዳድሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን ወደ ቦታው በማምጣት ከቦታቸው እንዲነሱ እንመክራለን። ክለቦቻችን በጤናማ እግርኳሳዊ አስተሳሰብ ካልተመሩ ስራውን የሚያከብር ባለሙያ ፣ አሰልጣኝ እና ተጫዋች ሊኖር አይችልም ፤ ስፖርታዊ መንፈስ ያልሰረፀበት ክለብም ተቃራኒ ደጋፊን ፣ የእግርኳስ ስርዓትን እና እግርኳሱን የሚያከብር ደጋፊ ሊኖረው ከቶ አይቻለውም። የእነዚህ ሁሉ ድምር ደግሞ እግርኳሱን የውንብድና ማዕከል ከማድረግ የዘለለ አንዳች አዎንታዊ እድገት ሊያመጣ አይችልም።

ከላይ ከተጠቀሱት በባሰ መልኩ ፌዴሬሽኑ ከገባበት አዘቅት ካልወጣ የእግርኳሳችን ህልውና ወደ ማክተሙ መሸጋገሩ አይቀሬ ነው። ለእግርኳሱ ውድቀት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ የሆኑና በመሪነት መጥተው ከመቼውም ጊዜ በላይ ቅሌት ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደረጉ ግለሰቦች በድጋሚ ለስልጣን ሲራኮቱ መመልከት የተወዳዳሪዎቹን ሰዋዊ ክብር የሚያጠራጥር ነው ብለን እናምናለን። ያለ ሀፍረት መወዳደራቸው ሳያንስ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍ አንገብጋቢ በሆነ ወቅት ላይ ተገኝተን እንኳ ያለ አንዳች ውጤት የጊዜ ፣ የሀብት እና የሞራል ኪሳራ በማስከተል በእግርኳሱ ላይ ሌላ በሽታ ሲሆኑ መመልከታችን ያንገበግበናል። እንደ ሶከር ኢትዮጵያ የምንጠይቀውም ፌዴሬሽኑ ቢያንስ ራሱን ከሰጠመበት ጥልቅ ባህር አውጥቶ ለሌሎች ምሳሌ እና አርዓያ የሚሆንበትን መንገድ እንዲጀምር ነው።

መገናኛ ብዙሀን ጉዳዩን የእግርኳሳችንን ህልውና የመታደግ ጉዳይ አድርገን እንድንሰራ ጥሪ እናስተላልፋለን። የእግርኳስ ሚድያ ዋንኛ ኃላፊነት “እግርኳስን ማገልገል” ነውና። አደገኛ በሆነ መንገድ የሚሸጥ ዜና ፍለጋ ከመሯሯጥ ፣ አንዱን አካል ተጠቃሚ ፣ ሌላኛውን ተጎጂ ለማድረግ ከሚከወኑ ተግባራት መቆጠብ ፤ ህዝብን ወደ ትክክለኛው መንገድ መምራት እና “ህዝብ የሚፈልገውን” የማቅረብ ዝንባሌ ከአዕምሮ በማውጣት ለእግርኳስ ዘብ መቆም ያስፈልጋል። በተደጋጋሚ በራዲዮ ውይይቶቻችን እንደገለፅነውም ሚድያዎቻችን ስለ ሜዳ ላይ እንቅሴቃሴ ድክመት እና ጥንካሬ ከማንሳት ይልቅ ስለ ደጋፊዎች የእለት ከእለት ክንውን መዘገብ ፣ የፌዴሬሽኑን አሰራር ከመተቸት ይልቅ ቡድናዊነትን የሚያንፀባርቁ የሴራ ንድፈ ሀሳቦች ላይ ማተኮር ፣ የእግርኳሳችን ችግሮች የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ ” ሁለት ጊዜ መቀባበል የማይችሉ ተጫዋቾች ለሞሉበት እግርኳስ ፣ ለዚህ የሞተ እግርኳስ … ” የሚሉ ገዳይ ሀሳቦች በርካታ ህዝብ የሚከተተለው ሚድያ ላይ ማቅረብ ትርፉ መነሻ እና መድረሻ ወደሌለው “ክብ መከራ” የሚያመራን በመሆኑ ከዚህ ልማድ ልንታቀብ ይገባል። 

በሌላ በኩል ደግሞ በገሀድ የታየ እውነታን በምንዘግብ ሚድያዎች ላይ የሚከፈተው ዘመቻ ፣ ማስፈራርያ እና ጫና እንዲቆም አበክረን እንጠይቃለን። አንዱ ሚድያ የዘገበውን ዜና በተሳሳተ መንገድ ህዝቡ እንዲረዳው ፣ ወገንተናዊነት የተንፀባረቀበት መሆኑን ለማሳየት የሚያሴሩ የሚድያ ሰዎችም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ አጋጣሚ ትገልፃለች።

በአጠቃላይ መነሻ ጉዳያችን በወቅታዊው የዳኞች ድብደባ ላይ ቢሆንም ችግራችን ተያያዥ እና ስር የሰደደ በመሆኑ ከላይ የተጠቀሱ ጉዳዮችን ልናነሳ ወደናል። ውስብስብ እና አንዱ ከሌላኛው ችግር ጋር የአካል እና ነፍስ ያህል የተዋሀደ በመሆኑ አንዱን ችግር ብቻ ቆርጦ ከመጣል እና ከመጠገን አልፈን በሕብረት መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መንገዱን እንድንጀምር በድጋሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ክብር ለዳኞቻችን !

ክብር ለእግርኳስ !