“የሀገሬ ብሔራዊ ቡድንን የማሰልጠን ህልም አለኝ” ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ

በፓለቲካ አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው የመን በጥር 2019 የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ለምታስተናግደው የእስያ ዋንጫ የመጀመሪያ ግዜ ተሳትፎን አሳክታለች፡፡ የመን ይህንን ስኬት ልታገኝ የቻለቸው በኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እየተመራች ነው፡፡ የካፍ የአሰልጣኞች ኢንስትራክተር የሆነው አብርሃም ዛሬ በዱባይ ስለሚደረገው የእስያ ዋንጫ ድልድል፣ ስለየመን ቀጣይ የዝግጅት ፈተናዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

የእስያ ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራት ከጨመሩ በኃላ የሚደረገው የመጀመሪያ ውድድር ነው፡፡ የምድብ ድልድሉ የሚወጣበት ጊዜ በመቃረቡ ስለምድብ ድልድሉ ያለህ ስሜት ምን ይመስላል?

እንግዲህ እንዳልከው የምድብ ድልድል የእጣ አወጣጥ ስነ-ስርዓቱ የፊታችን ዓርብ ሜይ 4 (ዛሬ) ላይ ነው፡፡ ይህንን የምድብ ድልድል ፕሮግራም የምታካሂደው የዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ ነት፤ የውድድሩም አዘጋጅ እሷ ስለሆነች፡፡ የዘንድሮውን የምድብ ድልድል ለየት የሚያደርገው ለመጀመሪያ ግዜ 24 ቡድኖች የሚያሳተፉበት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በተለይ ኤሺያ ውስጥ ያሉ ጠንካራ ቡድኖች ቀደም ሲል 4 ምድብ ውስጥ የነበሩት አሁን ወደ 6 ምድብ ውስጥ ገብተው ፉክክሩን የበለጠ ጠንካራ ያደርጉታል ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡ ስለዚህ ስለምድብ ድልድሉ ያለኝ ስሜት የትኛው ቡድን እንደሚደርሰን ባላውቅም በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ከተሳተፉት ስድስት ሃገሮች እና ካለፉት አምስቱ አንዱ እንደሚገጥመን ግን ተስፋ አደርጋለው፡፡ ምክንያቱም ኢራን አለች፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሳውዲ እና አውስትራሊያ እነዚህ ዓለም ዋንጫው ውስጥ የገቡ ናቸው ስለለሆነም የቡድን አባት ይሆናሉ ብዬ አስባለው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ይገጥመናል፡፡ ከዚህ ውጪ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምናስቀምጣቸው ሃገሮች በኤሺያ ውድድር ላይ በተደጋጋሚ የተሳተፉ በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይም ቀርበው ግን ያልተሳካላቸው ጠንካራ ቡድኖች ናቸው፡፡ ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንግዲህ እኛን (የመን) ጨምሮ ሌሎች ሃገሮች አሉ፡፡ አነሱም ቢሆኑ እዚ ውድድሩ ውስጥ ያየናቸው ጠንካራ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡ የመን እና የመንን መሰል የሆኑ እንደፊሊፒንስ፣ ሊባኖስ ያሉ ሃገሮች የውድድሩ መጀመሪያ እንደመሆኑ ቀላሉ ምድብ ይድረሰን ብለው ዱአ አድርገው (ሳቅ) ነው የሚገቡት ማለት ነው፡፡

ወደ እስያ ዋንጫ ካመራችሁ በኃላ በሳውዲ መዲና ሪያድ ላይ የየመን መንግስት አቀባበል አድርጎላችሁ ነበር፡፡ ይህ አቀባበል ምን ይመስል ነበር ድባቡስ?

ድሉን ተከትሎ የሃገሪቱ ርዕሰ-ብሄር አብድሮቦ ሃዲ ቡድኑን በቤተ-መንግስት ተቀብለው የእራት ግብዣ እና የክብር አቀባበል አድርገዋል፡፡ በውጤቱ እጅግ በጣም ተደስተዋል፡፡ እሳቸው እንዲያውም ያሉት ‘እኔ በህይወት እያለው ቡድኑ ለመጀመሪያ ግዜ ማለፉ በራሱ እደለኛ ያደርገኛል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ስፖርት የሰላም መሳሪያ መሆኑን በሚገባ አይቻለው፡፡ በፊት ሲነገር ነበር የምሰማው በተግባር አይቸዋለው፡፡ ምክንያቱም ሁሉም የመናዊያን በጋራ አንድ አይነት ቋንቋ የተነጋገሩበት ግዜ ነው፡፡ ስለዚህም ከጦርነቱ ወጥተው ስለኳሱ ብቻ ያወሩበት ግዜ በመሆኑ እናመሰግናለን፡፡’ ብለዋል፡፡ እንግዲህ ከድሉ ጋር ተያይዞ የአቅም ጉዳይ እንደምታውቁት ወደ 19 ሚሊየን ህዝብ ተርቧል፤ እርዳታ ጠያቂ ነው፡፡ ዜጎቿ በተለይም የሲቪል ማህበሩ ከ11 ወራት በላይ በትክክል ደሞዙን ያገኘበት ሁኔታ የለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ላይ እናንተ ማለፋችሁ ታሪኩን የበለጠ ያጎላዋል ሽልማታችሁን ግን አያጎላውም ምክንያቱም ሃገሪቷ ተዳክማለች ስለዚህ ወደፊት እየተረጋጋች ስትሄድ ሃገሪቱ እግርኳሱን ለማገዝ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል፡፡ እግረ መንገዳቸውንም ታዳጊ ቡድኑ ማሌዢያ ላይ ለሚካሄደው የኤሺያ ታዳጊዎች ውድድር አልፏል፤ የመን በዚህ ግርግር ውስጥ ብሄራዊ ቡድኖቿ ለኤሺያ ዋንጫ ማለፋቸው ትልቅ ገፅታ ነው ለሃገሪቷ እና ሁሉንም አመስግነዋል፡፡ በተለይም ለዋናው ብሄራዊ ቡድን የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን መንግስት አቅሙ በፈቀ መጠን ትብብር ያደርጋል፡፡ ሃብታም ከሚባሉ የጎረቤት ሃገሮች ጋር በመተባበር ቡድኑ በተሻለ መጠን የሚጠናከርበትን መንገድ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ በግል ደግሞ ኢትዮጵያ እና የመን ያላቸውን የረጅም ግዜ ግንኙነት የበለጠ ያደሰ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛ በካታር ይገኙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት አንድ ዓመት ከስድስት ወር በየውድድሩ እየተገኙ ድጋፍ መስጠታቸው በሌሎች ያልተለመደ ነው ብለዋል፡፡ ይሄ የበለጠ አስደስቷቸዋል፡፡ እኔም እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ደስ የሚል ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል፡፡
የየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞም በየመን ነበርክ፡፡ ግጭቱ እየተባባሰ ሲሄድም እዛው ቆይተሃል፡፡ የቤተሰብ ጫና ቢኖርም የአንተ ምርጫ በየመን መቆየት ነበር፡፡ መልካም ባልነበረው እና የከፋ ሁኔታዎች በሚታዩባት የመን ህይወትህን አደጋ ላይ ጥለህ እንድትቆይ ያደረገህ ምክንያት ምንድነው?

ትልቁ ምክንያት ያው ለእግርኳሹ ያለኝ ጥልቅ ስሜት ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የየመን ህዝብ ከእግርኳስ እና ከተለያዩ ስፖርቶች ጋር ለሚሰሩ ሙያተኞች ትልቅ ክብር እና ድጋፍ ይሰጣል፡፡ በነገራችን ላይ የማጣሪያ ማጣሪያውን ስናደርግ ከማልዲቭስ ጋር ረዳቶቼ ከክሮሺያ እና ቦስኒያ ነበሩ፡፡ የበረኛው አሰልጣኝ ከቦስኒያ ነው፤ የፊትነስ አሰልጣኝ ደግሞ ከክሮሺያ ነው፡፡ በኃላ ግን ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ የሃገራቸው መንግስታት ወደ የመን የምትገቡ ከሆነ ኃላፊነቱን ራሳችሁ ውሰዱ ስላላቸው ፈርተው ነው የቀሩት እንጂ ለእነሱም ቢሆን የየመን ህዝብ ምንም አላላቸውም፡፡ ቢሰሩም ምንም እንዳማይላቸው እርግጠኛ ነኝ፤ ህዝቡ ኳስ ይወዳል፡፡ ይህንን ደግሞ የምለው ሁለቱም ወገኖች ናቸው። ተቃዋሚውም፣ መንግስት እና ህዝብም ስፖርቱን ይደግፋል ይወዳል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ ማረጋገጫው ሁለቱም መንግስታት (በሳውዲ የሚደገፈው እና የሁቲ ተቃዋሚዎች) ቡድኑን መቀበላቸው ነው፡፡ አብዶሮቦ ሃዲ የሃገሪቱ ርዕሰ-ብሄር እና ኦፊሴላዊ የሚታወቁ ናቸው፡፡ እኛም የሃገሪቱ መሪ ነን የሚሉት ተቃዋሚ ፓርቲ ሰንአ ላይ አቀባበል አድርገዋል፡፡ እዛም የተገኘው የየመን ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ የሚል አካል ነው፡፡ እዚህም የተቀበለን ርእሰ ብሄሩ ናቸው፡፡ ሁለቱም ለስፖርቱ ያላቸው ፍቅር ጥሩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የበለጠ እንድቆይ አድርጎኛል፡፡ ሌላው የኦሎምፒክ ብሄራዊ ቡድኑን ሳሰለጥን ከአራት ዓመት በፊት ችግሩ ነበር። ግን በእዛ ችግር ውስጥ ቡድኑን ወደ ኤሺያ ሻምፒዮና እንዲያልፍ ለማድረግ ያረጉት የነበረውን ጥረት በአይኔ ስላየሁ ያንን ተመሳሳይ ድጋፍ ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ያደርጋሉ ብዬ ስላሰብኩ ነው የቆየሁት፡፡ ከዚህ በፊት ደግሞ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኜ ቢሮው ውስጥ እየሰራው ነበር፡፡ ስለዚህ ከሜዳ ውጪ ቢሮው ውስጥ መስራት እና በተለይ ግራስ ሩት ላይ የሚሰሩ ህፃናቶችን በትኖ ወይም ትቶ መሄድ ህሊናዬ አልተቀበለውም፡፡ ፊፋም የሰጠን ማበረታቻ በጦርነቱ መሃል ከየመናዊያን ጋር መስራትህ በአድናቆት የምንመለከተው ነው የሚለው አስተያየት እንድቆይ አድርጎኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን የመናዊያን ለእኔ የነበራቸው ክብር ጥሩ መሆኑ ሁለተኛ ለኳሱ ያላቸው ፍቅር ጥሩ መሆኑ እኔም ደግሞ በአጋጣሚዎች ውስጥ ስሰራ ያገኘኋቸው ትብብሮች እና ስኬቶች የበለጠ እንድቆይ አድርጎኛል፡፡

የምድብ ተጋጣሚዎችህን ካወቅህ በኃላ ምን ምን ነገሮችን ለመስራት አቅደሃል? ትልቅ ውድድር ላይ ለመሳተፍ መዘጋጀት የፋይናንስ አቅምን ይጠይቃል፡፡ የመን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር የእግርኳስ ማህበሩ በቂ የሆነ የፋይናንስ ድጋፍ ለቡድኑ ያደርጋል የሚል ግምት የለም እና ይህንንስ ተግዳሮት ለመወጣት ምን አስበሃል?

በዚህ ጉዳይ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ካለፈው ተሞክሯችን መደገም የሌለባቸው ስህተቶች ምንድን ናቸው ቡድኑ የሚካፈለው ለመጀመሪያ ግዜ ቢሆንም ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ለመውጣት መደረግ ያለባቸው ቅድመ ዝግጅቶች ምን መሆን አለባቸው? የሚለውን ቴክኒካል እና አስተዳደራዊ የሆኑ ጉዳዮችን የተመለከተ ሪፖርታችን ለየመን ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስትር ለፌዴሬሽኑም ጭምር ሰጥተናል፡፡ ነገር ግን ፌዴሬሽኑ ግዜ ወስዷል፡፡ አንድ በጣም የሚገርማችሁ ነገር የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ሪያድ ነው ያለው፤ ዋና ፀሃፊው ካታር ነው ያሉት፡፡ ምክትል ፕሬዝደንቱ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው ካይሮ ነው ያሉት፡፡ ሌሎች የቦርድ አባላት የመን ውስጥ ቀርተዋል፡፡ ስለዚህ ብዙ ስራዎች የሚሰሩት በቴሌ ኮንፍረንስ ነው ፤ ተገናኝተው እንኳን አይሰሩም፡፡ ይሄ ነገሮችን ለማስተካከል ግዜ ይወስዳል፡፡ ትክክል ነው ይህ ውድድር ትልቅ የፋይናንስ አቅም ይጠይቃል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ እንግዲህ ተወዳድሮ የሚመጣውን ውጤት በፀጋ መቀበል ካልሆነ በቀር ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን ትንሽ ያስቸግራል፡፡ እንግዲህ ስራዬ የሚጀምረው የምድብ ድልድሉ ወቅት ነው፡፡ የምድብ ድልድሉን ካወቅኩ በኃላ ከእኔ ምድብ ውጪ ያሉ ሃገሮችን ቢያንስ ወጪ እየቻሉ እነሱ ጋር እየሄድን የወዳጅነት ጨዋታን የምንጫወትበትን መንገድ እዛው የማሳመን እና የማግባባት ስራ መስራት ነው፡፡ ምክንያቱም አቅም የለንም፡፡ አቅም ያላቸው ሃገሮች ሁሉንም ነገር ችለው የሚያስተናግዱን ከሆነ ብንሸነፍም ሄደን ሃገራቸው ላይ እንጫወታለን ። ችግራችን የጨዋታ ልምድ ማነስ ስለሆነ እዛ ላይ ትኩረት አድርጌ እሰራለው፡፡ ከዚህ ውጪ በዚህ ምድብ ድልድሉ ላይ እኔ ብቻ ሳልሆን ፕሬዝደንቶችም ተጋብዘዋል። ስለዚህም ፕሬዝደንቱ ራሱ ከሌሎች ሃገሮች ፕሬዝደንቶች ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሌሎች የፋይናንስ ድጋፍ የምናገኝባቸው መንገዶች ያመቻቻል ብዬ አስባለው፡፡ ስራው የምድብ ድልድሉ ልክ ከተጠናቀቀ በኃላ ሰዉ ሳይበተን እዛው አዳራሽ ውስጥ የሚጀመር ይሆናል፡፡

የእስያ ዋንጫው ወደ 24 ተሳታፊ ሃገራት አድጓል፡፡ በተመሳሳይ በአፍሪካም የተሳታፊ ሃገራት ወደ 24 አድጓል፡፡ የተሳታፊ ሃገራት መብዛት የውድድሩን ጥራት አያደበዝዘውም ብለህ ታስባለህ? ምልከታ ምንድነው በዚህ ጉዳይ ላይ?

ብዙ ሙያተኞች ይህንን አስተያየት ሲሰጡ እሰማለው፡፡ ውድድሩ ሲጀመር ትክክል ነው ይህ ነገር መታየቱ የሚቀር አይደለም፡፡ ነገር ግን ውድድሩ 24 ቡድኖችን እያሳተፈ ዓመታትን እያስቆጠር በሄደ ቁጥር በየኦሎምፒክ ዘመኑ ቡድኖች የተሻለ ጥንካሬ ለኤሺያ ውድድር ተሳትፎ የተሻለ ትኩረት እየሰጡ ወደ ጥራት ይመጣሉ፡፡ የእኔም ግምትም ይሄ ነው፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያው ተሳትፎ ልክ እንደመጀመሪያው ውድድር ጥቂት ትልቅ ቡድኖች እንደተሳተፉበት ጥራቱ እኩል ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ የየመናዊያን ስጋትም ይሄ ነው፡፡ እንዲያውም እንዳንዶቹ ማለፋችን ብቻ በቂ ነው፤ ባንሳተፍስ ብዙ ግብ ሊገባብን ይችላል ይላሉ፡፡ ይሄም እንግዲህ የውድድሩን ውበት እንዳያጎድፈው ከማድረግም አንፃር ነው፡፡ በዚህ የመጀመሪያዎቹ ውድድር ላይ ይሄ ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡ ነገር ግን 24ቶቹ ቡድኖች የመሳተፍ ሁኔታ እየጨመረ ከሄደ ቡድኖች በየኦሎምፒክ ዘመኑ የረጅም ግዜ እቅድ እየያዙ እና እየሰሩ ቡድናቸውንም በኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይም እያሳተፉ ጥሩ ፉክክር ይኖራል ብዬ አስባለው፡፡ ግን መጀመሪያ ላይ እዚህ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም በዓለምም ዓለም ላይ ሊጠራጠር እችላለው 48 ቡድን ማለት ትንሽ ነው ከ210 ሃገራት መካከል፡፡ በአፍሪካ ተመሳሳይ ነገር ሊኖር ይችላል ብዬ አስባለው፡፡ ትልቁ ጠቀሜታ ግን ምንድነው በአህጉራዊ ውድድር ላይ የሃገራት ተሳትፎ በሃገራቸው ውስጥ ያለውን የእግርኳስ እንቅስቃሴ የበለጠ ያነሳሳል፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ተጫዋቾች ፍላጎት በአህጉራዊ ውድድር ላይ መታየት ነው። ስለዚህ ያንን እድል ስለሚጨምረው በሃገር ውስጥ ያለውን የሊግ እንቅስቃሴ ጥሩ ያደርገዋል፤ የወጣቶችን እንቅስቃሴ መልካም ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ በ12 ሃገሮች ወይም በ16 ሃገሮች ውስጥ ብቻ የነበረው የወጣቶች መነሳሳት አሁን ወደ 24 ሃገሮች ይሰፋ እና በአፍሪካ ያሉ ወጣቶች የመንቀሳቀስ ሁኔታ እና የመታየት እድል እጅግ በጣም ይጨምራል፡፡

የየመንን ብሄራዊ ቡድን የተጫዋቾች ስብጥር ስንመለከት ነበር፡፡ በብዛት ወጣት ተጫዋቾች ያወቀሩት ቡድን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በኦሎምፒክ ቡድኑ እንደመስራትህ ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ አንተ የመራኸው የየመን ብሄራዊ ቡድን ከሌሎቹ የየመን ብሄራዊ ቡድኖች ምን የተለየ ነገር ይዟል?

ብዙ የተለየ ነገር አልያዘም የያዘው ነገር ምንድነው ካለፉት 12 ዓመታት ትንሽ ለየት የሚያደርገው 80% በወጣቶች መገንባቱ ነው፡፡ የበፊቱን ግን ብታየው ለ3 የኦሎምፒክ ዘመን ወደ 16 ተጫዋቾች በተከታታይ አብረው የተጓዙበት ነው፡፡ እነሱ በሙሉ አሁን ወጥተው ኦሎምፒክ፣ ታዳጊ እና ወጣት ቡድን የነበሩ ተጫዋቾች ቡድኑን ተረክበው ጥቂት ልምድ ካላቸው ለምሳሌ ግብ ጠባቂው፣ የቡድኑ አምበል እና ሁለተኛው አምበል ውጪ ብዙዎቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ የእኔ ቡድን ውስጥ ለየት የሚያደርገው ይሄ ነው፡፡ ሌላው በዚኛው ቡድን ውስጥ ብዙ ወጣቶች ባሳዩት እንቅስቃሴ ወደ ውጪ ወጥተው የመጫውት እድል ማግኘታቸው ነው፡፡ እኔ ቡድኑን ስይዝ በውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ቁጥር 3 ብቻ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ 14 አድጓል፡፡ ብራዚል ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥም የሚጫወት ልጅ አለ፡፡ ይሄ ትንሽ ሰፍቷል፡፡ የእነዚህ ተጫዋቾች በውጪ ሀገራት መጫወት ግብአቱ ለብሄራዊ ቡድኑ ነው፡፡

የመን ባለመረጋጋት ውስጥ ሆና በኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ እየተመራች በአህጉራዊ ውድድር መድረስ ችላለች፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኗ በውጤት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቆ የኋልዮሽ ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ቁጭት ፈጥሮበኻል?

ከቁጭት ወጥተን በሌላ መልኩ ባየው ማለትም በዓለም ላይ እጅግ ከኢትዮጵያ በተሻለ ሰላም የሰፈነባቸው ምንም ዓይነት ነገር ኮሽ የማይልባቸው ሃገሮች ሆነው ግን በአህጉር አቀፍ ውድድር የማታያቸው ብዙ ሃገሮች አሉ፡፡ ትልቁ መስፈርት ሰላም መኖሩ በጣም ጥሩ ነው፤ ለእኔ ግን ትልቁ መስፈርት ምንድነው ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ረጅም ግዜ ሊያስኬደን የሚችል ስትራቴጂ ነድፈን መንቀሳቀስ አለመቻላችን ነው፡፡ የመን ውስጥ ስንሰራ እንደችግራችን ከዛ ችግር ሊያወጣን የሚችል ነገር ነድፈን ተንቀሳቅሰናል፤ ውጤታማም አድርጎናል፡፡ እኛም ደግሞ እንዳለን አቅም የምንፈልገው ቦታ ሊያደርሰን የሚችል ነገር የለንም፡፡ እንዲሁ በአራዳው ቋንቋ በጨበጣ ነው የምንሰራው፡፡ በደመ-ነፍስ ዓይነት ነገር ነው ስራው፡፡ ይህ ካልቆመ በስተቀር ከዚህ የተሻለ ነገር ኢትዮጵያ ቢኖራትም እግርኳሱን ለብቻው አይቀይረውም፡፡ ስለዚህ እዚህ ነገር ላይ መታሰብ አለበት ብዬ አስባለው፡፡ ከሊጉ ልጀምር የመን ምንም ሊግ የላትም ክለቦችም የሏትም፡፡ ግን ሊግ እንኳን በነበራት ግዜ ሊጓን በየዓመቱ ወይም በዓመት ሁለት ግዜ ትገመግማለች፡፡ የእኛ ሊግ ከተጀመረ በጣም ቆይቷል በተለይ አሁን ያለው ቅርፅ የያዘው እና እየተሰራበት ያለው ሊግ ከተጀመረ ቆይቷል ግን አንድም ዓመት በሙያተኞች ሲገመገም አይቼ አላውቅም፡፡ ምንድነው ጠንካራ ጎኑ ምንድነው ደካማ ጎኑ ፣ የሊጉ ውበት ቀንሷል አልቀነሰም ፤ ጥራቱ ጨምሯል አልጨመረም ፤ ለመጨመር ምን እናድርግ የእኛ ሙያኞች ግብአት ምን መሆን አለበት ፤ ተጫዋቾቹ ምንድነው የሚሰሩት … ምንም ነገር የለም፡፡ በየግዜው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እየባሰ መጥቷል ይባላል፡፡ እየባሰ ለመምጣት የቻለው ስላልተገመገመ ነው፡፡ ቢገመገም ኖሮ ይህ ነገር ከመድረሱ በፊት ይሄ ነገር ሊመጣ ይችላል እና ይሄን ነገር እናድርግ ተብሎ ይቀመጥ ነበር፡፡ ግን አሁን ሲመጣ መደንገጥ ፤ ሲመጣ መደንበር ብቻ ነው የሆነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ዳግም ተምልሶ የማሰልጠንም ይሁን በስፖርቱ ውስጥ የማገልገል እቅድ አለህ?

እንግዲህ የወደፊት እቅዱ ብቻ ሳይሆን አሁንም እየሰራሁ ነው፡፡ ከሃገሬ እግርኳስ ጋር በጣም ግንኙነቱ አለኝ፡፡ ያው እንደምታውቁት በዓመት ሁለት ግዜም ሶስት ግዜም ወደ ሃገር ቤት እየመጣሁ የካፍ የተለያዩ ኮርሶችን ከሲ እስከ ኤ ድረስ ያሉትን ኮርሶች እሰጣለው፡፡ ይህ ማለት ከሙያተኞች ጋር እጅግ በጣም ቅርብ ነኝ፡፡ አሁንም የሙያተኞች ብቃት ለማሳደግ እየሰራው ነው፡፡ ነገር ግን ክለብ እና ብሄራዊ ቡድን ይዞ ከማሰልጠኑ ጋር ትክክል ነው እንደማንኛውም አሰልጣኝ የመጨረሻ ግባችን ብሄራዊ ቡድን ነው፡፡ እንደማንኛውም አሰልጣኝ የሃገሬን ብሄራዊ ቡድን የማሰልጠን ፍላጎቱና ህልሙ አለኝ፡፡ ከዚህ ቀደም አሰልጥኛለው በዋናነት አይደለም እንጂ፡፡