በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ ያተኮረው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቀቀ

በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ላይ ያተኮረውና ለሁለት ቀናት በአዳማ የተካሄደው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደልን አሰመልክቶ የችግሩን መንስዔ እና መፍትሄዎች ላይ ለመወያየት የወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ከኢትዮዽያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ጋር በጋራ በመሆን የተዘጋጀው የምክክር ጉባዔ በትናትና ውሎው የስርአት አልበኝነት መንስኤ አስመልክቶ ዶክተር አያሌው ጥላሁን ጥናታዊ ፅሁፍ በስፋት ያቀረቡ ሲሆን ጉባዔው እስከ ማምሻው ድረስ ቀጥሎ በአራት ቡድን የተከፈለ በጉዳዩ ዙርያ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ትላንት መጠናቀቁ ይታወቃል።

በዛሬ ዕለት የቀጠለው የምክክር መድረክ ትላንት በይደር ባልተቋጩ ጉዳዮች እና በተነሱ ሀሳቦች ዙርያ በየምድቡ በሚገኙ ፀሀፊዎች አማካኝነት የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስኤ ፣ በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያሳደረው አሉታዊ ተፅእኖ እና በአጭር ፣ በመካከለኛ በረጅም እርቀት የችግሩ መፍትሄ መሆን ያለባቸው ሀሳቦች ለተሳታፊው ቀርበዋል።

በዕለቱ የተገኙት የተቋማት አመራሮች የችግሩን ሁኔታ እና በቀጣይ መሰራት ስለሚገባቸው ጉዳዮች በየተራ ለጉባኤተኛው ንግግር ያደረጉ ሲሆን በመቀጠል ጉባዔው ባለ 11 ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል። በዋናነት፡-

– በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ብሔር ፣ ዘር እና ጎሳ ላይ ያተኮሩ ችግሮች ወደ እግርኳሱ መጥተው ከፍተኛ ችግር ሳያደርሱ ከወዲሁ ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድ ችግሩን ለመከላከል ቃል እንገባለን።

– እግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፡- ጎልቶ የሚታይና አፍጥጦ የመጣውን አድሏዊ የሆኑ ብልሹ አሰራሮችን ለአንዴ እና መጨረሻ ጊዜ አስወግደን ከሙስና የፀዳ ፍትህ የሰፈነበት አሠራር እንዲሰፍን ለማድረግ ቃል እንገባለን።

– ዳኞች እና ታዛቢዎች ፡- የእግርኳሱ ህግ ግንዛቤያቸው አድጎ ከሙስና እና ከአድሏዊነት ነፃ እንዲሆኑ ሁኔታዎችን ሁሉ ለማመቻቸት ቃል እንገባለን።

– እግርኳስ ተጨዋቾች አሰልጣኞች ፣ የቡድኑ አመራሮች ፡- የእግርኳስ ሕግ ግንዛቤን ተላብሰው በማንኛውም የውድድር ቦታ ለሕግን ፣ ስነ ምግባር እንዲሁም ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ በመስጠት ውድድር በሠላም እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ቃል እንገባለን የሚሉ ይገኙበታል።

በመጨረሻም የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የወጣቶች ስፖርት ሚኒስቴር አቶ ርስቱ ይርዳው የህንን አንገብጋቢ ችግር ለመቆጣጠር የሚያስችል ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የተወጣጣ ኮሚቴ እንደሚዋቀር በመግለፅ የመዝጊያ መልዕክት አስተላልፈው የመርሀግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።