የተሾመ ታደሰ እና የአርባምንጭ ከተማ ጉዳይ እልባት አላገኘም

በ2009 በአርባምንጭ ከተማ ለተጨማሪ ሁለት አመታት ለመጫወት ኮንትራቱን ያራዘመው ተሾመ ታደሰ በዛው አመት ግንቦት ወር ላይ ጉዳት ከገጠመው በኃላ ከሜዳ የራቀ ሲሆን በህክምና ወጪው እና የደሞዝ ክፍያው ዙሪያ ያነሳው ጥያቄ አሁንም በክለቡ መፍትሄ ስላለማግኘቱ ይናገራል።

የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ተሾመ ታደሰ ከአንድ አመት በፊት በደረሰበት ጉዳት ከሜዳ ርቆ ሲቆይ የደሞዝ እና የህክምና ወጪ ክፍያዎችን አስመልክቶ ያለበትን ቅሬታ ከአራት ወራት በፊት ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፆ ክለቡም በስራ አስኪያጁ በኩል መሟላት ያለባቸውን መረጃዎች ከተሰበሰቡ በኃላ ክፍያዎቹን እንደሚፈፅምለት መግለፁ ይታወሳል። ሆኖም ውሉ ዘንድሮ የሚጠናቀቀው ተሾመ ክለቡን አሳውቆ በተለያዩ ሆሲፒታሎች በራሱ ወጪ ህክምናውን ሲከታተል ከቆየ በኃላ በተባለው መሰረት የህክምና ማስረጃውን አቅርቦ የደሞዝም ሆነ የህክምና ውጪውን የሚሸፍን ክፍያ ቢጠብቅም እስካሁን ምንም እንዳልደረሰው ይገልፃል።

ተጨዋቹ አሁን ላይ ስላለበት ሁኔታ ሲናገርም “ወደ ክለቡ ተመልሰህ ዘንድሮ እያገለገልክ ሁሉንም እናደርግልሀለን ቢሉኝም አሁን ከህመሜ ባለማገገሜ መጫወት አልችልም የሚል ምላሽን ሰጥቻቸዋለሁ። እነሱም ይህን አውቀው ጠብቅ እያሉኝ ቆይቻለሁ። አሁን ግን ለከፋ ችግር በመዳረጌ እና ገንዘብ የሚያስፈልገኝ በመሆኑ በውሌ መሠረት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና ለክለቡ የክስ  ደብዳቤ አስገብቻለሁ።” ይላል።

ከአራት ወራት በፊት ቅሬታው ተገቢ እንደሆነ አምነው በአፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡት ገልፀው የነበሩት የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጨመሳ የገቡት ቃል በተግባር ሳይቀየር እስካሁን ለምን እንደዘገየ ጠይቀናቸው “እንደ መፍትሄ ያሰብነው ተጨዋቹን በሁለተኛው ዙር ወደ ክለቡ ለመመለስ እና በሂደት የጠየቀውን ለመፈፀም ነበር ፤ ልምምድም ጀምሮ ነበር። ሆኖም ዳግም በመጎዳቱ ሊጫወት እንደማይችል ነግሮናል። አሁን ላይ ልጁ ባለመብት ነው። ደሞዙንም ሆነ የህክምና ወጪውን ስጡኝ ማለቱ ተገቢ ነው። በጥያቄው መሠረት ክፍያዎቹን ለመፈፀም በቀጣይ ጉዳዩን ለቦርድ አቀርባለሁ። በዛ ላይ ተወያይተን ለተጉላላበት ጊዜ በሙሉ ክለቡ ወጪውን የሚሸፍን ይሆናል።” በማለት ምላሻቸውን ሰጥተዋል።