” ኢትዮጵያ ለታገለችላቸው የስፖርት መርሆች ተገዢ መሆን አለባት ” አብርሀም መብራቱ

በእግርኳሳችን ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያያየረ የሚገኘው የስርአት አልበኝነት ጉዳይ አሳሳቢነት ከመቼውም ጊዜ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። እየተፈጠረ ባለው ችግር ዙርያ የተለያዩ የስፖርቱ ባለ ድርሻ አካላትን ካላቸው ልምድ በመነሳት መደረግ ስለሚገባቸው የመፍትሄ ኃሳቦች በማናገር እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። ለዛሬ የየመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እየተፈጠሩ በሚገኙ ችግሮች ዙርያ እና በቀጣይ መስተካከል ስለሚገባቸው ነገሮች ለሶከር ኢትዮዽያ የግል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ማህበርን ለ16 አመት በፕሬዝደንት እና በም/ፕሬዝደንት ሆነው ሲመሩ በየመድረኩ አጥብቀው ሲናገሯቸው የነበሩት መልዕክቶቻቸው ቅድሚያ ለስፖርታዊ ጨዋነት ትልቅ ክብር መስጠት አለብን በማለት ነበር ። ፊፋ በሚያስተዳድራቸው ውድድሮች ሁሉ የፊፋ መርሆቹን መከተል አለበት ይሉ ነበር ። ለምሳሌ እግርኳሱ ከዘር መድልኦ ፣ ፖለቲካ ፣ ኃይማኖት ፣ የቀለም እና የጎሳ ልዩነቶች ነፃ መሆን አለበት እያሉ አጥብቀው ይታገሉ ነበር ። ከዚህ በተጨማሪ ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚያስቧቸው አደንዛዥ እፅ ፣ መጠጦች ፣ የሲጋራ ማስታወቂያዎች በጭራሽ በስታዲየም አካባቢ እንዳይደርሱ ተሟግተው ያሳምኑ ነበር ። ይህ ማለት ኢትዮዽያ በስፖርታዊ ጨዋነት በዓለም እና በአህጉራችን ዘንድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች ማለት ነው ። ይህንን ትልቅ ሚና የተጫወተች በስፖርታዊ ጨዋነት ዓለምን ያሳመነች ሀገር በተለይ በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድልኦን በመቃወም ትልቁን ስራ የሰራች ሀገር እንዴት ነው ታዲያ ስፖርታዊ ጨዋነትን መጠበቅ ያቃታት በጣም ያሳዝናል ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ራሷ የታገለችላቸው የፊፋን የስፖርት መርሆችን መቀበል መቻል አለባት። ይህ ማለት የፊፋ መርህ የሚለው እግርኳስ ከዘር ፣ ከኃይማኖት ፣ ከቀለም እና ጎሳ ልዩነት ነፃ መሆኑ ነው። ይህን መቀበል ከተቻለ ስፖርቱን በሁሉም ዘርፍ በሰላም ማንቀሳቀስ  መምራት ይቻላል ብዬ አስባለው ።

ሌላው ለትምህርት ዘግይተናል። በኢሺያ ሊግ ውድድሮች ከመጀመራቸው አስቀድሞ በተሻሻሉ አዳዲስ ህጎች ዳኞቻቸውን ብቻ ሳይሆን ህጉ የሚፈፅምባቸውም አካላት ጭምር የተሻሻለውን ህግ እንዲያውቁ ይደረጋል ። ለምሳሌ እኔ መኪና አሽከርካሪ ነኝ። መንጃ ፍቃድ ከማግኘቴ በፊት በትራፊክ ደንብ መሰረት ትራፊኩ እንዳይቀጣኝ የሚያስቀጡ ህጎችን በሚገባ ተምሬ ነው የምዘጋጀው ። እዚህም የፊፋ ዳኞች ወይም የሀገራችን ዳኞች ተጨዋቾችን የሚቀጡበት ደንብ አለ ። ሆኖም አሰልጣኞቹም ተጨዋቾቹም ምን እንደሚያስቀጣ ህጉን በሚገባ አያውቁትም። የሚመራበትን ህግ አለማወቁ ነው ችግሮች እያስከተለ የሚገኘው ። ስለዚህ ለትምህርት የሰጠነው ትኩረት በጣም አነስተኛ ነው ። ለስፖርታዊ ጨዋነት የሰጠነው ቅስቀሳ እና ትምህርት እጅግ በጣም አናሳ ነው ። የእኛ አሰልጣኞች ፣ ቡድን መሪዎች እና ተጨዋቾች ህጉን ካስተማርካቸው ህጉን ካወቁ ውጤትን በፃጋ ይቀበላሉ ፣ ደጋፊዎቻቸው እነሱን አይተው ውጤቱን በፀጋ ይቀበላሉ ብዬ አስባለው  ። የእኛ ሀገር ደጋፊ ደግሞ የታወቀ ነው ሜዳ ውስጥ ምንም ይፈፀም የሚደግፈው ተጨዋች የሚያደርገውን ነገር  ይደግፋል ። የሚያደርገው ነገር ሁሉ እውነት ይመስለዋል። ዳኛ ሲቃወሙ አብሮ ይቃወማል ። የሚቃወሙት ልጁ ሜዳ ውስጥ ስለተቃወመ ልጁን ለመደገፍ ነው ። ግን ልጁ የተቃወመበት መንገድ ዳኛን የከበበት ፣ ዳኞችን የመታበት ምክንያት እውነት ስለሚመስለው ይቀበለዋል ። ስለዚህ ህጎች ላይ እውቅት ማዳበር ላይ ብዙ ነገር ይቀረናል።

በአለም ላይ  የግብ መስመር ማለፍ ፣ በእጅ ጎል ማስቆጠር ታይቷል። ግን ሰው አልተደበደበም ፣ ህይወት አልጠፋም ፣ ውድድር አልተቋረጠም። ስለዚህ ከእኛ የለያቸው አስተሳሰቡ ፣ አመለካከቱ ላይ ነው ። ስለዚህ እኛም መስራት ያለብን አስተሳሰብ እና አመለካከት መሆን አለበት ። ህጉ እንደሆነ ያው ተመሳሳይ ነው ። ሌላው ማለት የምፈልገው ግልፅ እና የማያሻማ ህጎች መቀመጥ አለበት ። ማን ምን ሲያጠፋ መቀጣት እንዳለበት መታወቅ አለበት። እንጂ ጥፋቱ ሲጠፋ ምን ብንቀጣው ይሻላል ብለህ የምትመክረበት መሆን ያለበት አይመስለኝም ። ስለዚህ ህጉ ላይ ጠበቅ ያለ ስራ መሰራት አለበት ።

ሌላው ቅጣት ማስተማርያ መሆን አለበት። ማስተማርያ ከሆነ ደግሞ ትምህርቱ ሳያልቅ አንተ የምታነሳው ከሆነ ይፃረራል ። ስለዚህ መጀመርያውን የቀጣኸው ቅጣት እሳት ማጥፊያ ነበር ማለት ነው ። ማስተማርያ ነው ካልክ እስኪማሩ ድረስ መጠበቅ ነው ያለበት። በትክክል ማስተማርያ መሆኑ ሳይታወቅ ቅጣት የምትሽር ከሆነ ነገም ሌላው አካል ስድስት ወር ቢቀጣው ወደ አንድ ወር ይቀይረዋል በሚል ስህተቶች እየተደጋገሙ ይሄዳሉ ። ስለዚህ ቅጣቶች በተገቢው መልኩ መተርጎም አለባቸው። በዚህም አንዱ ከአንዱ እየተማረ መምጣት ይቻላል ።