ፌዴሬሽኑ የዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር ባስቀመጣቸው ቅደመ ሁኔታዎች ዙርያ ምላሹን ሰጥቷል

በዛሬው እለት በፌዴሬሽኑ እና በዳኞች ማኅበር መካከል እየተካሄደ የሚገኘው ስብሰባ ላይ ማኅበሩ ላነሳቸው 10 ቅደመ ሁኔታዎች አቶ ጁነይዲ ባሻ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።

1ኛ. የካሳ ጉዳይ የጉዳቱ መጠን እና ማስረጃዎች ታይተው የሚከፈሉ ይሆናል።

2ኛ. ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከ2011 ጀምሮ የዳኞች መድን ዋስትና እንዲኖር ይደረጋል። ይህ ካልተሟላም የቀጣዩ ዓመት ውድድር እንዳይጀመር ይደረጋል። ለጊዜው ግን ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በከፊል ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ የመድን ዋስትናውን የምንገባ ይሆናል።
3ኛ. የሙስጠፋ መኪ ጉዳይ በዲሲፕሊን ቅጣቱ ላይ የተገለፀ ነው። የህክምና ብቻ ሳይሆን ካሳም ወልዲያ የሚከፍል ይሆናል። በሀገር ውስጥ ይሁን በውጭ ሀገር የሚለውን ግን የክክሞና ባለሙያዎች ውሳኔ ነው። ለሙስጠፋ ፌዴሬሽኑ 100,000 ብር ለመስጠት የወሰነ ሲሆን ወልዲያም ወጪውን እንዲሸፍን ደብዳቤ ልከናል።
4ኛ. በክልል ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ለዳኞች ጥበቃ እንዲደረግ የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የፀጥታ አካላት ፣ ወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ተወካዮች እና የዳኞች ማህበር የሚገኙበት የምክክር ለማድረግ በዚህ ሳምንት ደብዴቤ እንበትናለን።

5ኛ. የአየር ትራንስፖርት ለማመቻቸት እስከ ዘንድሮው ውድድር ማብቂያ ድረስ የሚሆን ገንዘብ ክለቦች እንዲሸፍኑ እንሰራለን። ይህ የማይቻል ከሆነ ግን ለ2011 የውድድር ዘመን የሚጀመር ይሆናል።

6ኛ. የእያሱ ፈንቴ እና ሌሎች ፖሊስ ያወቃቸው የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ተገቢው የህግ ፍትህ እንዲያገኙ እየሰራን ነው። የእያሱ ጉዳይ በህግ እየታየ ሲሆን በፍርድ ቤት ቀርቦ የከሳሸነት ቃሉን ሰጥቷል። ምስክሮችም እንዲቀርቡ መጥሪያ ተሰጥቷል። የፌዴሬሽኑ የህግ ክፍል ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው።

7ኛ. የአቅም ግንባታ ስልጠና በተመለከተ በቅርቡ ስልጠና ተሰጥቷል። ወደፊትም የሚሰጥ ይሆናል።

8ኛ. የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባዔ ወጪን እንድንሸፍን የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ማኅበሩ በራሱ ፍቃድ የጠራው በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ወጪውን እንዲሸፍን መጠየቁ አግባብነት የለውም።

9ኛ. የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አሰራር እንዲፈተሽ የቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ኮሚቴው ለተፈጠሩ ችግሮች መነሻ መሆኑን ከክለቦች ጋር ባደረግነው ምክክር መድረክ ላይም ተገልጿል። ስለዚህም ይህ ኮሚቴ ስራውን ከመቀጠሉ በፊት እንዲታገድ ተደርጓል። 

10ኛ. ደህንነታቸው አስተማማኝ ባልሆኑ ሜዳዎች ላይ ውድድር አናደርግም የሚለውን በተመለከተ ክለቦች ይህን ለማስተካከል ጊዜ ስለሚያስፈልጋቸው በደብዳቤ ተገልፆላቸው በቀጣዩ አመት የትኛውም ሜዳ አጥር እንዲኖረው ይደረጋል።