ዶ/ር አሸብር ራሳቸውን ከምርጫው ያገለሉበትን ምክንያት በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አድርገዋል

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝደንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ደቡብ ክልል የሰጣቸውን ድጋፍ ተጠቅመው በፕሬዝደንት ሆነው ወደ ሰሩበት የእግርኳስ ፌድሬሽኑ ለመመለስ ተፎካካሪ ሆነው ከቀረቡ ግለሰቦች መካከል የሚጠቀሱ ቢሆንም አርብ ዕለት በምርጫው እንደማይካፈሉ ታውቋል፡፡

ዛሬ በኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ፅህፈት ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ዶክተር አሸብር በምርጫው አስቀድሞ የመወዳደር ፍላጎት እንዳልነበራቸው ጠቁመውዋል፡፡ “ደቡብ ክልል ወክሎኝ ተወዳዳሪ ነበርኩ፡፡ ከጅምሩም እውነቱን ለመናገር ብዙም ፍቃደኛ አልነበርኩም፡፡ ግን በተደጋጋሚ በቀረበው ጥሪ ገባሁ፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ በጠበቁት መልኩ ለዴሞክራቲክ ምርጫ ዝግጁ አልነበረም፡፡ ብዙ ያልጠበኳቸው ከስፖርቱም ወጣ ያለ ለሃገሪቱ ስፖርት የማይበጅ ብዙ ነገሮች ተከስተዋል፡፡ በዚህ መሃልም አቆርጬ መውጣት ከወሰንኩ እጅግ በጣም ቆይቻለው፡፡ የወከለኝ አካል ሌላ ሰው መተካት የማይችበት ነገር ነበር፡፡ ጥሩ አጋጣሚ የተፈጠረው እጩዎች እንደገና ማቅረብ እንደሚቻል በተጠየቀው መሰረት እኔም ለደቡብ ክልል እጩ ሆኜ መቅረብ እንደማልችል አስታውቂያለው፡፡”

ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዶክተር አሸብር መፍትሄ ከመሆን አንፃር ራሳቸውን ከምርጫው እንዳገለሉ አስረድተዋል፡፡ “ምናልባት እኔ እዛ ብቀጥል በዕለቱም ላይካሄድ ይችላል የሚል ስጋትም ስላለኝ እንዲሁም የሃገራችን ገፅታም በእንደዚህ ዓይነት መልኩ እየጠፋ መሄዱ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ስለሚሰማኝ ስለሚቆረቁረኝ ከዚህ ውድድር ራሴን ማግለል ችያለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይቅርታ መጠየቅ የምፈልገው የመረጠኝን የወከለኝን ደቡብ ክልል እስካሁንም ሰዓት እየጠየቀኝ ያለው የደቡብ ክልልን በጣም አጥብቄ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለው፡፡ የደገፉኝን ለእኔ ሲሉ ፕሬዝደንት ሁላ ያላቀረቡ ክልሎችን፣ በእኔ ያመኑትን ክለቦችን እና ማህበራትን ለወሰንኩት ውሳኔ በእጅጉ አድርጌ ይቅርታ እጠይቃለው፡፡ በእርግጥም ይረዱኛል ብዬ አስባለው፡፡ ኢትዮጵያ ከእኔ በላይ ናት፡፡ ማንም ሰው የራሱን ክብር እና ፍላጎት ከሃገር ክብር እና ፍላጎት በታች አድርጎ ማየት አለበት፡፡”

ዶክተር አሸብር በምርጫው ላይ ድምፅ ስለማይኖራቸው እንደማይሳተፉ ታውቋል፡፡ ሆኖም ዳግም ከሌሎች ክልሎች ድጋፍ የማግኘት እድላቸው የጠበበ ነው የሚሉ ሃሳቦችን እንደማያምኑበት እና በእርሳቸው ላይ ከተወዳዳሪዎች ይሰነዘሩ የነበሩ ነቀፌታዎችን አጣጥለዋል፡፡ “ውክልና በአሁኑ ደቂቃ እንኳን ማግኘት እችላለው አይደለም እስካሁን ባለው ግዜ፡፡ እኔ ብፈልግ በአሁኑ ሰዓት አገኛለው፡፡ የደቡብ ክልልም የትኛውም ክልል ለእኔ ይሰጠኛል የሚከለክለኝ የለም፡፡ ነቀፌታውን በተመለከተ ይህ የጨዋታው አንዱ አካል ነው፡፡ በፖለቲካውም በስፖርቱም በሌላውም አለ፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ቢደርስብህ አንተም ማድረስ ትችላለህ፡፡ አንተን ከምርጫ ለማውጣት የግለሰቦች ሊያውም ከእኔ በላይ መንቀፍ እና ሃራስ ማድረግ የማይችሉ ሰዎች የተናገሩት ንግግር እኔ ብዙም በእዛ ደረጃ አላስብም፡፡ ለእኔ ከውድድሩ መውጣት የእነሱ አስተዋፅዖ የለውም፡፡”

ዶክተር አሸብር አዲስ ከሚመረጠው ፕሬዝደነት ጋር ተባብሮ ለመስራት ቃል የገቡ ሲሆን መጪው ፕሬዝደነት በእግርኳሱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት መስራት ያለበትን አንዳንድ ሃሳቦች ሰንዝረዋል፡፡ “በቀጣይ የሚመረጠው ፕሬዝደንት የሃገሪቱን እግርኳስ አሁን ከገባንበት የማይሆን ነገር እግርኳስ መሆኑ ቀርቶ የጦር አውድማ ሰው የሚገዳደልበት ቦታ ሆኗል፡፡ ክብር እና ፍቅር የጠፋበት ቦታ ሆኗል፡፡ ጭራሽ መቃቃር ብቻ የነገሰበት ቦታ ሆኗል፡፡ ይህንን ስፖርታዊ ጨዋታነት ማምጣት የግድ የሚለው ይመስለኛል፡፡ በእኔ እምነት በሃገሪቱ ላይ የጠፋውን ፕሮጀክት እንደገና ማስቀጠል እና በድህነት እንኳን ወቅት እያለን የነበረን ውጤት እና ክብር ተመልሶ የሚመጣበት ደረጃ ላይ መስራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ክቡር አቶ ይድነቃቸውን የመሰለ ታላቅ መሪ አፍሪካ ለ20 ዓመት በመራበት ሃገር መሆኑን ይታወቃል፡፡ ይህንን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ የውጪ ግንኙነታችንን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ትርምሱን እያባባሰ እና ሃገሪቱ ላይ አለመረጋጋትን እያመጣ ያለው የውድድር ስርዓት ውድድሩ የግድ በክለቦች እንዲመራ ማስቻል እንዳለበት አስባለው፡፡”