አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ስለ ፌዴሬሽኑ ምርጫ ይናገራሉ

ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ፣ ደራሲና የስፖርት አመራር አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በመጀመሪያ የኦሎምፒክ ጨዋታ የተሰኘች የመጀመሪያ የስፖርት መጽሓፍ እንዲሁም የፒያሳ ልጆች መጽሃፍ ደራሲ ናቸው፡፡ የኢትዮጲያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ሲቋቋም ከክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ጋር በዋና ጸሃፊነት አገልግለዋል፡፡ በዓለም ዓቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴም የፕሬዝዳንቱ ካቢኔ ዳይሬክተር፣ የዓለም ዓቀፍ ትብብር ዳይሬክተርና የኦሊምፒክ ሪቪው ዋና አዘጋጅ ለረዥም ጊዜ አገለግለዋል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኝነትን ሀ ብለው በዛሬይቱ ኢትዮጵያና በ l’Ethiopie d’aujourd’hui በአማርኛና በፈረንሳኛ ቋንቋ በመጻፍ የጀመሩት አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ሲመሰረትም የመጀመሪያ የስፖርት የሬዲዮ ጋዜጠኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡ አቶ ፍቅሩ ለአሜሪካ ድምጽ  ሬዲዮም በስፖርት ጋዜጠኝነት በማገልገል አሳልፈዋል፡፡


በወቅታዊ የሀገራችን እግርኳሳዊ ጉዳዮች ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን የሚሰጡት አቶ ፍቅሩ ለሶከር ኢትዮጵያ የፈረንሳይኛ ዜና አዘጋጅ ተሾመ ፋንታሁን ላቀረበላቸው ጥያቄዎች በኢሜይል ያደረሱትን ምላሽ እነሆ፡፡ 


በተደጋጋሚ የተራዘመውና በፊፋ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የፌዴሬሽን ምርጫ በመጨረሻ ሊደረግ ነው፤ ፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርታችሁ በአስቸኳይ አስመራጭ ኮሚቴ ምረጡ ባለው መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ አስመራጭ ኮሚቴ ተመስርቷል፤ በዚህ አለቅጥ በተንዛዛ ምርጫ ዙርያ የእርስዎ ትዝብት ምንድን ነው ?


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሪዎች መተዳደሪያ ደንባቸው የተለየ ነው፡፡ ካፍም ሆነ ፊፋ አያውቀውም፡፡ በዚህም የተነሳ ፊፋ ልክ እንደአዲስ ጀማሪ ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ አርቅቆ ልኮላቸዋል፡፡ ወደ አማርኛ ማስተርጎም ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ ከእንግሊዝኛው የአማርኛው የተሻለ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ ጠቅላላ ጉባኤ የተጠራው የአስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ ነበር። አስመራጭ ኮሚቴው ተመርጧል ነገር ግን አሁንም ነጻ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የሚመረጡት አስመራጭ ኮሚቴዎች ከተፎካካሪዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሊኖራቸው አይገባም፡፡ 


ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ ያቃተን በምን ምክንያት ይመስልዎታል ?


የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቅሌት ውስጥ ከከተተን በጣም ቆይቷል፡፡ ለሌሎች ሃገራት ምሳሌ የነበረው ፌዴሬሽን አሁን የማንም መቀለጃ ሆኗል፡፡ ተራ ጠቅላላ ጉባኤ ማዘጋጀት ያቃተው ችሎታ በሌላቸው ሰዎች የመመራቱ ውጤት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ?  የራስ፣ የዘር እና የክልልን ጥቅም ብቻ በሚያስቀድሙ ነገር ግን ለእግር ኳስ እና ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሁም ህግ አክባሪነት ደንታ በሌላቸው ሰዎች ተሞልቷል፡፡


የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት እውነት አማተርነት ነው? ወይስ ህዝብ የማያውቀው ልዩ ጥቅም አለው?


በመላው ዓለም በክለብ፣ በማህበርና በፌዴሬሽን ውስጥ የሚያገለግሉ ሁሉ አማተሮችና በጎ ፍቃደኞች ናቸው፡፡ እኔ ዕድሜ ልኬን ያገለገልኩት የራሴን ወጪ ራሴ እየሸፈንኩ በበጎ ፍቃደኝነት ብቻ ነው፡፡ ክለቦችና ፌዴሬሽኖች ቋሚ ሰራተኞች አሏቸው። ነገር ግን የሥራ አስኪያጁና ንዑስ ኮሚቴዎች በሙሉ በበጎ ፍቃደኞች የሚመሩ ናቸው፡፡ አሁን ያለው ጥቅም ለካፍና ለፊፋ ስብሰባዎች የሚሄዱበትን ሙሉ ወጪ የሚችሉት ድርጅቶቹ ናቸው፡፡ በቀን ሁለት መቶ ሃምሳ ዶላር የቀን አበል ይከፍሏቸዋል፡፡ በዚህ ላይ አዲስ አበባ ላይ በቴሌቪዥን መታየት፣ ፎቶግራፍን በጋዜጣ ገጽ ላይ ለማሳተም ይጠቅማል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ የጋዜጦች የፊት ገጽ ለፕሬዝዳንትና ለሚኒስትሮች፣ ሁለተኛ ገጽ ክስ ለቀረበባቸውና ለወንጀለኞች ሲሆኑ አራተኛው ገጽ ለስፖርት መሪዎች የተሰጠ ነው፡፡ ለሁሉም ቀላሉ የፌዴሬሽን መሪ መሆን ነው፡፡ አሁን ሁሉም የሚሻኮተው ለኢትዮጵያ በመቆርቆር ሳይሆን ወደ ሩሲያ የዓለም ዋንጫ ለመሄድ ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉት ፊፋ እምቢ ብሎ እንጂ ምርጫው አሁንም ቢተላለፍ ደስ ይላቸዋል፡፡ ተፎካካሪዎቹ ደግሞ ውድድሩ ሳይቀርብ ተመርጦ ለመሄድ በየክትፎ ቤቱ ዘመቻ ላይ ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የነበሩት አቶ ተሾመ ቶጋ ለካፍና ለፊፋ በጻፉት ደብዳቤ (ኮፒው በእጄ ይገኛል)  ኢትዮጵያ የማንም መቀለጃ አይደለችም ብለው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት እንደዚው በምርጫ አተካራ የተነሳ በፊፋ ልትቀጣ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር ጣልቃ ገብቶ ነው ከቅጣትና ከውርደት ተርፋ መብቷን ማስከበር የቻለችው፡፡  


የእግር ኳሱ ውጤት እየጠፋ ነው፣ የእግር ኳስ ሜዳዎች ከጊዜ ወዲህ ወደ ስርዓት አልበኞች አውድማነት እየተቀየሩ ነው፣ ዳኞች አሰልጣኞችና ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ በይፋ ይደበደባሉ፣ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ቅጥ ያጣባት ሃገር እየሆነች ነው፣ እንደዚህ አይነት ችግሮች ምክንያታቸው ምን ይሆናል ? ምንስ መደረግ አለበት ?


ዘር፣ ሃይማኖትና ፖለቲካ በስፖርት ውስጥ መጠቀስ የለበትም፡፡ ለምሳሌ ከቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የኤርትራ ክለቦች ሃማሴንና አካለጉዛይ ስማቸውን እንዲቀይሩ አድርገዋል፡፡ አልፎ ተርፎም ጦር ሰራዊት፣ ክቡር ዘበኛ፣ ፖሊስና አየር ኃይል የሚባሉትም ቡድኖች ወደ መቻል፣ መኩሪያ፣ ኦሜድላ እና ንብ እንዲቀይሩ ሆነው ነበር፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰፈር (አካባቢ) ቡድን ነው እንጂ የክርስቲያን ቡድን አልነበረም፡፡ የቡድኑ አምበል አዋድ መሐመድ ሙስሊም ነበር፡፡ ሌሎቹም ቢሆኑ ለቀብርና ለሰርግ ቤተክርስቲያን የሚሄዱ እንጂ ኃይማኖተኞች አልነበሩም፡፡ አሁን ግን በዘርና በጎሳ የተከፋፈልን ስለሆንን ቡድኖቹም መሪዎቹም የዚሁ ሰለባ ስለሆኑ እንደልባቸው ይደባደባሉ፤ አሁን አሁንማ በመሪዎቹ ብሷል፡፡ የጨዋታው ውጤት የዘር ግጭት መጥሪያ ሆኗል፡፡ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሌላ ዘር አላውቅም፡፡ በኔ ዘመን አሁን እንዳለው ድብድብና ብልግና አይታይም ነበር፡፡ ሕዝቡ ጨዋና ህግ አክባሪ ነበር፡፡ ያሁኑ ትውልድ ጸብ የጠማው ይመስላል፡፡ ስታዲየም ስትገባ ስድቡም ያንኑ ያህል ነው፡፡ በዘር መከፋፈላችን ደግሞ ከሁሉም የከፋው ስቃይ ነው፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከዚህ ሁሉ ይገለግለናል ብዬ ተስፋ አለኝ፡፡ 


እግር ኳስን በመምራት ቀደምት፣ ለሌሎች ሃገራት ምሳሌ የሆነች፣ ከራሷ አልፋ አህጉራዊውን ተቋም ለመምራት የበቃች ሃገር፣ አሁን የራሷን ሃገር ለመምራት ያልቻለች ሌላው ቀርቶ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ የፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት መምረጥ አቅቶን ፕሬዚዳንቱ ወቅቱን (Mandate) ከጨረሱ 8 ወራት አልፏቸዋል፡፡ ችግሩ ምን ይሆን ?


ሃገራችን ውስጥ የተማረ ሞልቷል። ነገር ግን እግር ኳሱ አካባቢ ካሉት ሰዎች ጋር መነታረክ ስለማይፈልግ እንደሮታሪ አይነት ነጻ ተቋም ፈልጎ ያገለግላል እንጂ መቅረብም ሆነ መጠጋት አይፈልጉም፡፡ ብዙዎቹ የፕሪምየር ሊግ ክለብ መሪዎች የታወቁ የፖለቲካ ድርጅት አባላትና መሪዎች ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚ ሰዎች እያሉ እንዴት ቀርበህ መስራት ትችላለህ ? በግል ስፖርቱን ልትወድና ልትደግፍ ትችል ይሆናል። ከፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ጋር ተወዳድረህ ኳስን ልትመራ ግን አትችልም፡፡ ለራሳቸው ጥቅም የሚሯሯጡ የክልልና የድርጅት ካድሬዎች ስለሞሉትም እኮ ነው የፊፋን መተዳደሪያ ደንብ እንኳ አንብቦ መረዳት የማይችሉ ሰዎች ፌዴሬሽኑን ያጣበቡት፡፡
ፊፋ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ይከለክላል፤ ግን ደግሞ ይህ ህግ በስፖርቱ ዙሪያ ላሉ ሰዎች ከለላ ሆኗቸው እያየን ነው፡፡ መንግስት በርግጥም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ጣልቃ መግባት ካልቻለ ሰዎቹ በተገቢው መስመር መጓዝ የሚችሉ አይመስልም፤ የክለብ ቤለቤቶች የመንግስት ተቋማት በሆኑበት ሁኔታ የዚህ ህግ ትርጓሜ ምን ማለት ይሆን ?


መንግስት ጣልቃ መግባቱን ፊፋ ያወቀው ዘግይቶ ነው፡፡ ዕጩ የሚያቀርቡት ክልሎች ናቸው፡፡ ተፎካካሪዎችም የክለብ ተጠሪዎች አይደሉም፡፡ ለመወዳደር የሚፈልግ ሁሉ ብሔሩን መሰረት አድርጎ ነው፡፡ በኢትዮጵዊነት መወዳደር አይቻልም፡፡ የሚያቀርበው የለም፡፡ በመሰረቱ ጠቅላላ ጉባኤው መካሄድ ያለበት በክለብ ወኪሎች ተሳታፊነት ነው፡፡ ዕጩ የሚያቀርቡትም ክለቦች ናቸው፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ በቀር በየትኛውም ዓለም የሚሰራበት ነው፡፡ በኛ ዘመን ክለቦች የሚመርጧቸው የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት ብዙዎቹ ሚኒስትሮች በሃገሪቱ የታወቁ ባለስልጣናትና ሚኒስትሮች ነበሩ። ዓላማው እግር ኳስ እንዲዳብር በመንግስትም ደረጃ ሆነ በሌላ መልኩ እግር ኳስን መርዳት የሚችሉ ሰዎች መኖራቸውን በመረዳት ነው፡፡ ለምሳሌ አማተር ተጫዋቾች የስራ ፍቃድ አያገኙም ነበር፡፡ በዓመት ውስጥ ብዙ የኢንተርናሽናል ውድድሮች ሲኖሩ አሰሪዎቻቸው ፍቃድ አልሰጥም ሲሉ አማላጅ ሆነው የሚሄዱት እነዚው ባለስልጣናት ነበሩ፡፡  አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳስ ውስጥ ዘር ቆጠራ እስካልቀረ ድረስ የኢትዮጵያ እግር ኳስ መሪዎችንም መመሪያዎችንም አያከብርም፡፡ አለመከበር ደግሞ ትልቅ ውርደት ነው፤ ለኛም ለሃገርም ትልቅ ውርደት ነው፡፡ መንግስት በስፖርቱ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚለው አባባል ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ስፖርት እንዲስፋፋ ዋናው ባለድርሻ መንግስት ነው፡፡ ያለመንግስት ዕርዳታ የአፍሪካ ሃገራት ምንም ማድረግ አይችሉም፡፡ ፌዴሬሽኖች ሲቋቋሙ ዕውቅና የሚሰጠው መንግስት ነው፡፡ በፌዴሬሽን ምርጫ መንግስት ጣልቃ አይግባ የሚባለው ክለቦች የራሳቸውን መሪዎች እንዲመርጡ ከዛም የተመረጡበትን ጊዜ እንዲጨርሱ መነሳት ካለባቸው በጠቅላላ ጉባዔ ብቻ የመነሳት መብታቸው እንዲከበር ነው፡፡ 


በአጠቃላይ ከርስዎ ልምድ ትምህርትና አመለካከት የተነሳ የእግር ኳስ አመራር ምን መሆን አለበት ብለው ያስባሉ ?


የኢትዮጵያ ስፖርት ከእግርኳስና አትሌቲክስ በቀር ገደል ውስጥ ከገባ ቆይቷል፡፡ አፍሪካ ውስጥ ከሃያ በላይ ዓመታዊ ስፖርታዊ ውድድሮች በክለብም በብሄራዊ ደረጃም ይካሄዳሉ ኢትዮጵያ ግን የለችም፡፡ ፌዴሬሽኖቹ አሉ ያሉት ግን ወረቀት ላይ ብቻ ነው፡፡ የባስኬት ቦል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አለው ነገር ግን ውድድር የለውም፡፡ ሃገራችን የተማረ ሰው ችግር የለባትም ለማገልገል ግን የሚጋብዝ ሁኔታ የለም፡፡ ስፖርቱን የከበበው የራሱን ጥቅም የሚያሳድድ ብቻ ነው፡፡ የስፖርት ምሁራን ተሰደዋል፡፡ ዘር ቆጠራው ሁሉንም አባሯቸዋል፡፡ ዘር ቆጠራ ቀርቶ አንድ ኢትዮጵያ የሚባልበት ቀን እሰኪመጣ መደማመጥ ከባድ ነው። 


እንደማጠቃለያ …


ከላይ እንደነገርኩህ ሲስተሙ ለውጥ ይፈልጋል፡፡ ተወዳዳሪዎቹ እስከአሁንም ፌዴሬሽኑን በዚው በተበላሸ መንገድ እየመሩ የነበሩ ወይም ከዚህ በፊት የመሩ ናቸው፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ይመጣል ብዬ አላስብም። ነገር ግን አሁን አዳዲስ ሁለት ሶስት ሰዎች አሉበት። እድል አግኝተው ይመረጣሉ ወይ እኔንጃ ። ከተመረጡ ግን ምናልባት …። በባለፈው አስመራጭ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ የፊፋን ህግ ሳይቀር ለማረም የሞከሩ ደፋሮች አሁን የሉም፤ የሚሆነውን ማየት ነው፡፡