ቢኒያም በላይ ከስከንደርቡ ጋር ሁለተኛ ዋንጫ አሸነፈ

ስከንደርቡ የአልባኒያ ዋንጫን ኬኤፍ ላሲን 1-0 በማሸነፍ ሲያሳካ ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ የመጀመሪያ ዓመት የአውሮፓ ቆይታውን በሁለት የዋንጫ ድሎች ደምድሟል፡፡

የኮርሲው ክለብ የሱፐር ሊጋውን ዋንጫ ከሳምንታት በፊት ማሸነፉን ካረጋገጠ በኃላ ሙሉ ትኩረቱን ለዚህ የፍፃሜ ጨዋታ ሰጥቶ ነበር፡፡ ቢኒያም በተጠባባቂ ወንበር ላይ ሆኖ የጀመረ ሲሆን በ88ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት በጨዋታው ላይ መሳተፍ ችሏል፡፡ የስከንደርቡን የድል ግብ ሳቢን ሊላ በ67ኛው ደቂቃ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ከመረብ አዋህዷል፡፡

የ8 ጊዜ የሱፐር ሊጋው አሸናፊ ስከንደርቡ የአልባኒያ ዋንጫን ሲያሸንፍ በታሪኩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም 5 ጊዜ ለፍፃሜ ደርሶ በሁሉም ተሸንፎ ነበር፡፡ ክለቡ በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ የሁለትዮሽ ዋንጫ ባለቤት ሲሆን የቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋች ቢኒያምም የዚህ ታሪካዊ ቡድን አካል ሆኗል፡፡

ቢኒያም በዓመቱ መጀመሪያ ወደ አልባኒያ ካመራ በኃላ በውስጥ ሊግ ጨዋታዎች እና በዩሮፓ ሊግ የምድብ ጨዋታ ላይ መሰለፍ ችሏል፡፡ በአልባኒያ ዋንጫ ላይ ደግሞ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡