የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ዛሬ ከሰአት ወሳኝ የግማሽ ፍፃሜ ቸዋታዎችን አስተናግዶ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ያለፉትን ሁለት ክለቦች ለይቷል፡፡ በ10፡00 በተደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከነማ ጅማ አባ ቡናን 2-0 በማሸነፍ ሆሳእናን ተከትሎ ፕሪሚየር ሊጉ መቀላቀሉን አረጋግጧል፡፡
ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ ስታድየሙ በሰዎች ከመሞላቱ በተጨማሪ የሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች ተመሳሳይ ቀለም ያላቸው ልብሶችን በመጠቀም ስታድየሙን አድምቀውታል፡፡ የድሬዳዋ ከነማ ደጋፊዎችም የተለያዩ የሙዚቃ መሳርዎች በመያዝ ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ታይተዋል፡፡
እንደ ሆሳእና ከነማ እና ሃላባ ከነማ ጨዋታ ሁሉ በጉዞ ላይ በደረሰ አደጋ ህይታቸው ላለፉት የሃላባ ከነማ ደጋፊዎች የህሊና ፀሎት በማድረግ የተጀመረው ጨዋታ በቀይ ካርዶች ፣ በአጨቃጫቂ ግብ ፣ በተሳተ ፍፁም ቅጣት ምት እና በውዝግብ ተጠናቋል፡፡
ከድሬዳዋ ከነማ የድል ግቦች የመጀመርውን አብዱልፈታ ከማል በ12ኛው ደቂቃ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ግቧ ከመስመር አላለፈችም በሚልም አባ ቡናዎች ክስ እስከማስመዝገብ ደረጃ ደርሰዋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ 64ኛው ደቂቃ ደግሞ የቡድኑ ግብ አዳኝ በላይ አባይነህ የድሬን 2ኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ በላይ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ያገኛትን ፍፁም ቅጣት ምት ስቷል፡፡ በላይ ይህንን ግብ ቢያስቆጥር በ7 ግቦች የውድድሩን ኮከብ ግብ አግቢመነት ያጠናክር ነበር፡፡
በጨዋታው ከጅማ አባ ቡና በኩል 2 ተጫዋቾች ከሜዳ በቀይ ካርድ የተወገዱ ሲሆን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከስፖርታዊ ጨዋነት ውጪ የሆነ ግርግር ሲፈጥሩም ተስተውለዋል፡፡
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን ሰጡት የድሬዳዋ ከነማው አሰልጣኝ መሰረት ማኒ የመጀመርያዋ ሴት አሰልጣኝ በመሆን ቡድናቸውን ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማሳለፋቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል ‹‹ ከዞኑ ውድድር ጀምሮ ድክመታችንን እያረምን ለዚህ ደረጃ በቅተናል፡፡ የመጀመርያዋ ሴት አሰልጣኝ በመሆኔም በጣም ደስተኛ ሆኛለው፡፡ በሴትነቴ የደረሱብኝን ፈተናዎች በድል ተወትቻለሁ›› ብለዋል፡፡
የጅማ አባ ቡናው አሰልጣኝ ደረጄ በበኩላቸው ድሬዳዋ በዳኞች ታግዞ አሸንፏል ብለዋል፡፡ ‹‹ ዳኞቹ ለተጫዋቾቼ ቶሎ ቶሎ ካርድ በመምዘዝ በነፃነት እንዳይጫወቱ ሲያደርጉ ነበር፡፡ ግቦቹ የተቆጠሩበት መንድም ፍትሃዊ አልነበሩም፡፡ በዳኛ ከመታገዝ ይልቅ በስራ ቢያልፉ ይረት ነበር፡፡ ካልሆነ በመጡበት አመት መመለሳቸው የማይቀር ነው፡፡›› ሲሉ በምሬት አስተያየታቸውን ሰትተዋል፡፡
ድሬዳዋ ከነማ በ2004 ወደ ተሰናበተው ፕሪሚየር ሊግ መመለሱን ሲያረጋግጥ ሴቷ አሰልጣኝ መሰረት ማኒም የመጀመርያዋ ሴት በመሆን ታሪክ ሰርተዋል፡፡
አንጋፋው የጅማ አባ ቡና አማካይ ቢንያም ኃይሌ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በስፖርት ኮሚሽን እና ወታቶች ቢሮ በጋራ ተመርጧል፡፡