ድሬዳዋ ከነማ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት ለብሄራዊ ሊግ ፍፃሜ ደርሷል፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መመለሱንም አረጋግጧል፡፡ ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸውን የሰጡት አሰልጣኝ መሰረት ማኒ የተሰማቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ በእያንዳንዱ ጨዋታ ድክመቶቻችንን እያረምን ለፕሪሚየር ሊጉ በቅተናል፡፡ በዚህም ደስታ ተሰምቶኛል፡፡ የመጀመርያዋ ሴት በመሆን ታሪክ በመስራቴም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በሴትነቴ ምክንያት ይህንን ስራ መስራት ብዙ ፈተናዎች ነበሩት፡፡ እነዛን ሁሉ ፈተናዎች ተወጥቼ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ይህ ስኬት ሴቶች ምንም ነገር መስራት እንደማያቅታቸው ማሳያ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡
መሰረት በቀጣዩ አመት ለሚጠብቃቸው የፕሪሚየር ሊግ ፈተና እደሚዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ የፕሪሚር ሊጉ ከባቢ ከብሄራዊ ሊጉ የተለየ ነው፡፡ በደረጃውም የሃገሪቱ ትልቅ ሊግ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን የያዝነውን ቡድን ሙሉ ለሙሉ ይዘን መቅረብ ይቸግረናል፡፡ በቀጣይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን ለፕሪሚየር ሊጉ የሚመጥኑ ተጫዋቾችን ለማምጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማለፋችን አያዘናጋንም ፡፡ ወደመጣንበት ላለመመለስ ጠንክረን እንሰራለን፡፡ ›› ሲሉ ሃሳባቸው አጠቃለዋል፡፡
ድሬዳዋን በ2004 ወደተሰናበተበት ፕሪሚየር ለግ የመለሱት አሰልጣኝ መሰረት ማኒ በቀጣዩ የውድድር ዘመን የፕሪሚር ሊግ ቡድን በአሰልጣኝነት የሚመሩ በታሪክ የመጀመርያዋ ሴት አሰልጣኝ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡