ሶከር ሜዲካል: የጭንቅላት ጉዳት በእግር ኳስ

እግር ኳስ ንኪኪ የበዛበት እና ጉዳቶች የሚስተዋሉበት ስፖርት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሳሳቢ ከሆኑ ጉዳቶች መካከል የጉልበት ጉዳትን ከዚህ በፊት መመልከታችን የሚታወስም ነው፡፡ በዛሬው አምዳችን በቅርብ ጊዜያት ከፍተኛ ትኩረት እየተደረገበት የመጣው እና ብዙ ጥናቶች እየተደረጉበት ያለውን የጭንቅላት ጉዳት እንመለከታለን፡፡

የጭንቅላት ጉዳት በአብዛኛው ተጫዋቾች በአየር ላይ ያለ ኳስን ለማግኘት በሚሞክሩበት ጊዜ የሚከሰት ነው። በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ተጫዋቾች እርስ እርስ በሚላተሙበት እና መሬት ላይ በአደገኛ ሁኔታ በሚወድቁበት ወቅት ይህ ጉዳት ሲፈጠር ይስተዋላል። ራስን መሳት፣ ጊዜያዊ የሆነ የመርሳት ችግር፣ በጭንቅላት ውስጥ የሚፈጠር መድማት ደግሞ ከጉዳቶቹ መካከል ይፈረጃሉ። ቨርጂኒያ ቴክ ዩኒቨርስቲ ባደረገው ጥናት መሰረት እስከ 60% የሚደርሱ እግር ኳስ ተጫዋቾች የጭንቅላት ግጭት ይደርስባቸዋል።

የእንግሊዛዊው የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ራየን ሜሰን ታሪክ የጭንቅላት ጉዳት ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያሳየናል። የቀድሞው የሀል ሲቲ እና ቶተንሃም ሆተስፐር ተጫዋች ገና በ26 ዓመቱ ነበር በጭንቅላት ጉዳት ከሚወደው እግር ኳስ ለመገለል የተገደደው። ተጫዋቹ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ከፍተኛ ግጭት በሀኪሞች ምክር ጨዋታ አቁሟል፡፡ ከጀርመኑ የዜና አውታር ዶይቸ ቬለ ጋር ቆይታ ያደረገው ሜሰን በ2017 ከቼልሲው ተከላካይ ጋሪ ኬሂል ጋር በነበረው የጭንቅላት ግጭት አንጎሉን በሚሸፍነው አጥንቱ (Skull) ላይ የመሰንጠቅ ጉዳት እንዳደረሰበት፣ ሁኔታውንም በደንብ እንደሚያስታውሰው ተናግሮ ነበር:: በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ የጀርመኑ አማካይ ክሪስቶፍ ክራመር ባጋጠመው ግጭት በጊዜ ከሜዳ ለመሰናበት ተገዶ ነበር፡፡ ክራመር በወቅቱ የት እንዳለ እንኳን እስከማያውቅ ድረስ ራሱን ስቶ ነበር፡፡

ከላይ ለአብነት ከተጠቀሱት ሁለት ተጫዋቾች መረዳት እንደምንችለው በጭንቅላት ላይ የሚደርስ ጉዳት እጅጉን አሳሳቢ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ጉዳት አንጎላችን ከመጠነኛ አንስቶ ውስብስብ የሆኑ ተግባራቱን በአግባቡ እንዳያከናውን እክል የሚፈጥር ነው።

ራየን ሜሰን ሲናገር “በጭንቅላት ጉዳት ላይ ያለው አመለካከት ሊለወጥ ያስፈልጋል። ሁለት ተጫዋቾች ሲጋጩም ማን ቅድሚያ ግልጋሎት ማግኘት እንዳለበት ቀድሞ መወሰን የግድ ነው። እኔ ከካሂል ጋር ስጋጭ በጣም የተጎዳሁት እኔ ሆኜ ሳለሁ ቅድሚያ ህክምና የተደረገለት የባለሜዳው ቡድን ተጫዋች ካሂል ነው” ብሎ ነበር።

ምንም እንኳን አንጎላችን በጠንካራ አጥንት የተጠበቀ ቢሆንም ጉዳቶች ሲደርሱ የተለያዩ ደም ስሮች ከመጎዳታቸው የተነሳ Traumatic Brain Injury የተሰኘው በሽታ ይከሰታል። ከዚህም የተነሳ ህይወት እስከ ማለፍ ድረስ ያሉ ችግሮችን ያስከትላል። ይህ ጉዳት CT Scan በማንሳት የሚታወቅ ሲሆን ተጎጂዎቹም ጥብቅ የሆነ ክትትል ይደረግላቸዋል።

አይደለም እንደኛ ባለው ለስፖርት ህክምና በቂ ትኩረት በማይሰጥበት ሀገር ዘመናዊ ህክምናና መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ ባሉበት አውሮፓ እንኳን የጭንቅላት ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ ነው። በቂ ትኩረት፣ አፋጣኝ ህክምና፣ ጥሩ ክትትል በእንደዚህ አይነት ችግር ለሚጠቁ ተጫዋቾች ያስፈልጋል።

የአርሰናሉ ግብ ጠባቂ ፔትር ቼክ በሬዲንጉ አጥቂ ስቴፈን ሃንት ከተረገጠ እና አሰቃቂ ጉዳት ከደረሰበት እነሆ ከ10 አመታት በላይ ሆናል። አሁንም ግን ጭንቅላቱን የሚከላከልበትን ቆብ ሳያደርግ ወደ ሜዳ አይገባም። ከዚህ በላይ ስለጉዳዩ አሳሳቢነት የሚነግረን መረጃ የለም። ተጫዋቾቻችን ከእንደዚህ አይነቱ አስከፊ ጉዳት ከለላ ያስፈልጋቸዋል። በተለይ በጨዋታ እና በልምምድ ወቅት እንደዚህ አይነት ጉዳቶች ከተከሰቱ ከባድ የሆነ ጉዳትን እንዳያስከትሉ በቂ የድንገተኛ ህክምና አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ባለሞያዎችን በየሜዳዎቹ ማዘጋጀት ወሳኝ ነው። የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በእግር ኳስ መሃል የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን በማጤን ሊረባረቡ ይገባል፡፡