“ካለፈው ተምሬ የበለጠ ለመስራት በጣም ዝግጁ ነኝ” ጂነይዲ ባሻ 

ከመስከረም 2006 ጀምሮ ከአራት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በፕሬዝደንትነት የመሩት አቶ ጁነይዲ ባሻ ዳግም ለመመረጥ እየተወዳደሩ ይገኛሉ፡፡ ፕሬዝደንት ጁነይዲ ምርጫውን በተመለከተ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ያለፉትን አራት ዓመታት በመሪነት ላይ ቆይተዋል፡፡ በዚህ ዓመታትም ለእግርኳስ ጥሩ የማይባሉ ጊዜያት ነበሩ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ዳግም ለመወዳደር ለምን ፈለጉ?


ለምን ብትል በመጀመሪያ ፉትቦል በኢትዮጵያ ውስጥ በሰፊው ተዘርግቶ ነበር ወይ ብትል አልተዘረጋም ብዬ ነው ማስበው፡፡ ለምን ታዳጊ ክልሎች ትልቅ ብሄራዊ ክልሎችም የምትላቸው እነ አማራ፣ እነ ኦሮሚያ ምንድነው የነበረው ክለብ ብትል በአማራ አንድ ዳሽን ብቻ ነው የነበረው አሁን ክለብ ፈልቶ በየከተማው ይታያል፡፡ ሰው የሚያየው መጣላቱን አንዳንድ የስፖርታዊ ጨዋነትን መጉደሉን ነው፡፡ ሲኖሩ እኮ ነው ስለዛ የሚነገረው፡፡ እዛ ላይ ቆሞ ግን ይስተካከላል፡፡ በወጣት ደረጃ ከ20 ዓመት በታች እና ከ17 ዓመት በታች አሁን ነው የመጣው፡፡ ብሔራዊ ቡድን በሰፊው የውጤት ጉዳይ አይደለም ጫፍ ላይ ደርሶ የሚመለሰው፡፡ ቻን በዚህ ሃገር እየመጣ ነው፤ ሴካፋ አዘጋጅተናል፡፡ አሁን ለአፍሪካ ዋንጫ 2025 አምጣ ተብያለው፡፡ የካፍ እና የፊፋ ግንኙነታችን ተጠናክሯል፡፡ ህንፃ ለመግዛት በ3 ሚሊየን ዶላር ተፈራርሚያለው፡፡ ይሄን ሁሉ ስራ ላይ ለማዋል በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብዬ ነው ማስበው፡፡ ሌላው ደግሞ እንደሊግ ዓይነት ምስረታ፣ በወጣት ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት ላይ ለመግባት በጣም በከፍተኛ ጉጉት ላይ ነን ከፊፋ እና ካፍ ጋር ኳሶችን አምጥቼ፡፡ ከ15 ዓመት በታች ካመጣሁ ለምን ከዚህ በኃላ ከ12 ዓመት በታች አይሆንም? ይሄ ደግሞ የሚገኘው ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሰሜን ጎንደር ሄደህ ትጀምራለህ ፤ ምዕራብ ትግራይ ሄደህ ትጀምራለህ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ነገር መሰራት ስላለበት መግባት አለብን እስከኦሞ እስከታዳጊ ክለብ መስራት አለብን፡፡ ይሄን ለማድረግ አሁን እንቅስቃሴ ላይ ነኝ፡፡ ሰው ድክመት ብቻ ስለሚናገር እንጂ ለምርጫ ሲባል ብዙ ችግሮችን እየደጋገመ የሚናገረው የነበረውን ፌደሬሽን ክሬዲቱን ለማሳጣት እንጂ ብዙ ስራ ተሰርቷል፡፡ እስኪ እስከዛሬ ህንፃ አለን? ለምን አልነበረንም? ህንፃ ለመግዛት ጫፍ በተደረሰበት ይህ ምን ማለት ነው? ለምን ቢሮ አይኖረውም 50 ዓመት የቆየ ፌደሬሽን? ለምንድነው ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ያልነበረው? ለምንድነው ለምሳሌ ኦሮሚያን ብትወስድ ከአዳማ እና ሙገር ውጪ ሞቅ ያለ ያልነበረው? አሁን በአንድ ጅማ ሁለት አለ፡፡ አማራ አንድ ዳሽን ብቻ ነው የነበረው፡፡ ትግራይም ፕሪምየር ሊግ የገባ አንድም ክለብ አልነበረውም አሁን ሁለት አለው፡፡ እነሶማሌ እና ጋምቤላ ክለብ አልነበራቸውም፡፡ ይሄን ለምን እንደቀላል እናየዋለን? ስለብሄራዊ ቡድን ብቻ ስለምናወራ ነው፡፡ ብሃራዊ ቡድን ግን የምናመጣው የት ተሰርቶ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ደግሞ የተጫዋቾች ዝውውር አልተሰራም? አዲስ ዝውውር ይሄ ሁሉ ዘመን ነበር፡፡ በዘፈቀደ በዘልማድ ነበር የምናዛውረው፡፡ ዛሬ እስከፊፋ ሪከርድ አድርገን ፊፋ እንዲያውም እዚህ ስልጠና ማድረግ ጀምሯል፡፡ ፌደሬሽኑም እንግዲህ ሰው እንደሚያወራው አይደለም፡፡ ካፍ በቅርቡ ባወጣው ዘ ቶፕ ፌደሬሽን 10 ብሎ ኢትዮጵያ 10ኛ ናት፡፡ ብዙ ፌደሬሽኖች አሉ በምዝበራዎች ከፊፋ የመጣን ገንዘብ ወደ ተለያዩ ቦታ የሚሄዱበት እስቲ እኛ ሃገር የወጣ ነገር ይነገር፡፡ በጣም ንፅህና ያለው ፌደሬሽን ብዬ ነው ማስበው፡፡ እኔ ምንም 5 ሳንቲም አልጠፋም ብዬ መከራከር ባልፈልግም ሁሉን  ቦታ መቆጣጠር ስለማልችል፡፡ ውድድሮች በሰፊው የምንመራበት፣ ሊግ ለመመስረት ከፊፋ ስልጠና፣ ኢንተርናሽናል ዳኞች ከ7 ወደ 22 ያደጉበት ብዙ ነገሮች እየሰራን ነው፡፡ ክልል እያየን ነው፡፡ ኢንተርናሽናል ጨዋታ በባህርዳር በሀዋሳ በሁሉ ቦታ እያመጣን አይደለም ወይ? እድሜ ከ17 ዓመት በታች ኤምአርአይ እያመጣን ከድሮ በተሻለ ህክምና አቋቁመን እየሰራን ነው፡፡ እስቲ አንድ የሚናገር አለ ይሄን ሁሉ? አይኔን ግንባር ያድርገው ነው? ስለዚህ መምረጥ ካርድ ዝምብሎ መስጠት አይደለም፡፡ ዝምብሎ አቶ እገሌ እገሌ ከክልል መላክ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ ታስቦ ከማንነት ከብሄረሰብ ውጪ ከተለያዩ የእምነት ጉዳይ ውጪ ወጥተን የኢትዮጵያ እግርኳስ የሚመቸውን የተረጋጋ አማካይ ስራ ሁሉን ስራ ክልል ማቀፍ የሚችል ወገን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ 

እርሶ ወደስልጣን ከመጡ በኃላ የተቀረፀ ስትራቴጂ ነበር፡፡ አራት ግቦችን ለማሳካት ያቀደው ይሄ ስትራቴጂ አንዱም አልተሳካም፡፡ ለምሳሌ በማርኪቲንግ በኩል አስከ 900 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ እና በአፍሪካም ደግሞ ተወዳዳሪ የሆነ እና ተከታታይነት ያለው ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን የመፍጠር የሚሉትን ግቦች አልተሳኩም፡፡ አፈፃፀሙ ላይ…


ልክ ነው አፈፃፀሙ ላይ፡፡ ብሄራዊ ቡድን ላይ ባለፈው ግዜ ሲሸልስ ላይ ነጥብ ባንጥል 11 ነጥብ ነበረን፡፡ ቶጎ የገባው በ11 ነው፡፡ መቼም ሩብ ጉዳይ አንድ ጉዳይ ተብሎ መነገር ብዙም ስለማይመች እንጂ እኮ ሴቶቹም ከጋና ጋር ጫፍ ደርሰው ነው፡፡ አሁን ዘንድሮ ለምሳሌ ሴቶች ጥሩ መጥተዋል፡፡ ያልፋሉ ብዬ እገምታለው ከአልጄሪያ ጋር፡፡ እየቀረብን ነው በእውነቱ ለመናገር ከሆነ፡፡ በፊትም እንደምታውቁት ከ31 ዓመት በኃላ ነው እንጂ ያመጣነው የብዙ ዘመን ክፍተትም አለ፡፡ የተረጋጋ እግርኳስ መምጣት አለበት፡፡ ስትራቴጂ ደግሞ ለምሳሌ ፉትቦል ክልል ላይ እንዲስፋፋ አላደረግም? አድርገናል፡፡ ስልጠናዎችን አላደረግንም? አድርገናል፡፡ ገንዘብም ቢሆን ከ50 ሚሊየን 112 ሚሊየን ማድረስ እጥፍ ነው፡፡ በፊት ተመኝተን ትልቅ ነገር እናድርግ ብለን ነበር፡፡ ይሄ ሁሉ ይሰበሰባል ወይ? 

አቶ ጁነይዲ የተለያዩ ሴራዎች በመስራት አይታማም ፣ አይታወቅም ነገር ግን የአመራርነት ብቃቱ ዝቅተኝነት አለ በስሩ ያሉትን ሃላፊዎች የመምራት ብቃትን ጨምሮ፡፡ ይሄ ባለበት ሁኔታ መወዳደሩ አግባብ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ…


ማነው ዝቅተኛ የሚለው? ይሄ አሁን አንተ ነው የምትለው፡፡

ለምሳሌ ውሳኔዎች ይሻራሉ…

አንድ ነገር ላይ ብቻ ናት እሷም የምትነሳው፡፡ ሌላው እስኪ ያልተመራ ነገር ንግረኝ ? ሁሉን ነገር ፕሬዝደንት ይስራ እንዴ? እያንዳንዱ የቢሮ ሰራተኛ፣ ክለብ፣ የክልል እግርኳስ ፌደሬሽን ድርሻ አላቸው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ እሱ እሱስ አልተስተካከለም?

ግን እዛ ላይ ውሳኔ የመስጠት እና እርምጃ የመውሰድ ለምሳሌ ሴካፋ ላይ ከ17 ዓመት በታች ቡድናችን በፓስፖርት ስህተት ነጥብ ሲቀነስ…እንደዚህ ዓይነት ስህተቶች አሉ፡፡


እየተወሰደ ነው፡፡ እውነት ለመናገር እስቲ ሜዳ ላይ ያልተወሰነ ነገር ይሄ ነው ብለህ ንግረኝ? ከ17 ዓመት በታቹም ውሳኔ እየተወሰደ ነው ያለው፡፡ ተጣርቶ መጥቶ በእዛ ላይ እየሰጠን ነው ያለነው፡፡ ውሳኔ መቀየርም 300 ምናምን ከተሰጠ የቀተየረው 10 እና 12 ናት፡፡ እሷንም ቢሆን እንዳትደረግ ብዬ ውሳኔ ሰጥቼ አልፊያለው፡፡ አሁን ደግሞ ከዚህ ተምሮ የበለጠ ለመስራት በጣም ዝግጁ ነኝ፡፡