ዜና እረፍት | የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

የደደቢቱ ዋና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ትላንት ምሽት በገጠማቸው ድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ምሽት 06:00 ገደማ ከጓደኞቸቻው ጋር በነበሩበት ሰአት በተሰማቸው የህመም ስሜት ወደ ጎፋ ጤና ጣብያ ተጉዘው ህክምና ካደረጉ በኋላ የህመም ስሜቱ ሲባባስ ለድጋሚ ህክምና ሀሌሉያ ሆስፒታል ሲደርሱ ህይወታቸው ማለፉን ከክለቡ የቅርብ ሰዎች ሰምተናል። የአሰልጣኙ አስከሬን ለምርመራ ምኒልክ ሆስፒታል የሚገኝ ሲሆን ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላም ለስርዓተ ቀብር ወደ ማይጨው ይሸኛል ተብሏል።

የቀድሞ የምድር ጦር ተጫዋች የነበሩት አሰልጣኝ ንጉሴ በመከላከያ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ደደቢት እና ወልዲያ አሰልጣኝነት የሰሩ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በድጋሚ በተመለሱት ደደቢት ከ2010 ጀምሮ በመስራት ላይ ይገኙ ነበር። 

ክለቡ ዛሬ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የ25ኛ ሳምንት ጨዋታውን የሚያደርግ ቢሆንም በአስደንጋጩ ዜና ምክንያት ወደ ሌላ ጊዜ እንደሚሸጋገር ታውቋል።

ሶከር ኢትዮጵያ በደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ድንገተኛ ህልፈት ሀዘኗን እየገለፀች ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለደደቢት ስፖርት ክለብ አባላት እና የስፖርት ቤተሰብ መፅናናትን ትመኛለች።