” ስራው የዘርፉ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ፍፁም ቅንነትን ይልፈጋል ” አቶ ኢሳይያስ ጂራ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዘደንት

ቀጣዮቹን አራት ዓመታት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን በፕሬዘደንትነት ለመምራት የተመረጡት አቶ ኢሳይያስ ጂራ በትናንቱ የሶከር ኢትዮጵያ የሬድዮ ፕሮግራም ላይ በምርጫው ሒደት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ ወደ ፅሁፍ ቀይረን በሚከተለው መልኩ አቅርበንላችኋል።

ከአጠቃላይ የምርጫው ሒደት እንጀምር…

በምርጫው ወቅት በአስፈፃሚ ኮሚቴው በሙሉ ባይሆንም ሰብሳቢው ጋር የህግ ክፍተት ነበር። በፕሬዘደንትነት ምርጫው በመጀመሪያ ዙር አብላጫ ድምፅ ያለውን ነው የምናሳልፈው ብለው ነው ወደ ምርጫ የተገባው። በወቅቱ እጩ ተወዳዳሪ በመሆናችን እና አስተያየት መስጠት የማንችል በመሆኑ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ነግረን እጅ በማውጣት ማስተካከያውን ለመናገር ቢሞክሩም አልተሳካም። በህጉ መሰረት በመጀመሪያው ዙር አብላጫ ድምፅ ያገኘው አካል 50+1 ድምፅ ካላመጣ ወደ ሁለተኛው ዙር ሄዶ በድጋሚ መወዳደር ይኖርበታል። በተለይም ለፕሬዘደንትነት በሚደረገው ምርጫ ላይ ይህ ህግ በግልፅ የተቀመጠ ነው። የተሰራውም ስህተት ይህ ነበር። ከዛም ምርጫው ቀጥሎ በ66 ድምፆች እኔ ማሸነፌን በይፋ ገለፁ። በዚህ ወቅት የፊፋው ተወካይ ሚስተር ኒኮላስ ስህተት እንደተሰራ እና ሁለተኛ ምርጫ መካሄድ እንዳለበት ይናገራሉ። በመቀጠል ወደ ሁለተኛው ምርጫ ለመሄድ የምሳ ዕረፍት ሰጡ። ከምንም በላይ ይህኛው ጉዳይ ነው ያልተመቸን። ሁለቱ ሰዐቶች ሰመራ ውስጥ ከባድ ነበሩ። የተለያዩ ቅስቀሳዎች እየተደረጉ እንደነበርም እንሰማ ነበር። ዕረፍት መወጣት አልነበረበትም። ሁለተኛው ምርጫ መካሄድ ካለበት እዛው ከአዳራሽ ሳንወጣ መጨረስ ነበረብን።

ስለዚህ ከምሳ ዕረፍት መልስ አቋርጠው የወጡት በዚህ ምክንያት ነው ?

በመጀመሪያ ደረጃ ደጋፊዎቼ ከአዳራሹ ሲወጡ እኔ በኃላ ላይ ነው የወጣሁት። ምርጫ አስፈፃሚዎች ፕሬዘደንቱን ካሳወቃችሁ በኃላ በምርጫው ላይ ስልጣን የላችሁም የሚል ሀሳብ አንስቻለው። ምክንያቱም ህግ ጥሰው ነው ያስመረጡት። እናም ደጋፊዎቼ ሲወጡ ተከትዬ ወጥቻለው። እነሱንም ያሳሳታቸው የምርጫ አስፈፃሚ ሰብሳቢ ነው። ከ3-5 ደቂቃ ያህል ወስጄ አነጋግሬያቸዋለው። ‘ ከምንም በላይ ለሀገር ክብር ቅድሚያ መስጠት አለብን። ማንም ያሸንፍ ማን ተመልሰን ገብተን በአግባቡ ድምፅ እንስጥ’ በሚለው ሀሳብ ተስማምተን ተመልሰን ገብተናል። ሆኖም በችኮላ የሚሰጥ ድምዳሜ አለ። እኔ ጉባዓውን አቋርጦ የመውጣት ሀሳብ በፍፁም አልነበረኝም። ነገር ግን እኔን እና ደጋፊዎቼን ለማሸበር ‘ ራሱን ከምርጫው ያገላል ‘ የሚል ወሬ ሲናፈስ ነበር። ይህ እንዲሆን ስለማልፈቅድ እስከመጨረሻው ቆይቼ የሚመጣውን መቀበል ነበረብኝ። ወጥቼም አረጋግቻቸዋለው። ምክንያቱም ይህ የግል ጉዳይ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ለ9 ወራት ሲጠብቀን ቆይቷል። ይህን አቋርጦ መውጣትም ትልቅ ውድቀት ነው የሚሆነው በማለት ተመልሰን ገብተናል። ምርጫው ሲጀመር ፍፁም ስርዐት ነበረው። ትልቁ ክፍተት የነበረው በዝርዝር የተፃፈ ነገር አለመኖሩ ላይ ነው። የፊፋው ተወካይ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ አየተጠየቁ ነበር። ነገሮችን ባሉበት ለማስኬድ በሚል እንጂ ፕሬዘደንት ከተመረጠበት ክልል ስራ አስፈፃሚ አይመረጥም የሚል አንቀፅም አልነበረም። ምርጫ አስፈሚ ኮሚቴው መጀመሪያውኑም ደንብ የማስፈፀም እንጂ የማሻሻል ስልጣን የለውም። እነዚህን ጉዳዮች እኛ ማስተካከል አቅቶን አመቱን ሙሉ እንደተከታታይ የሬድዮ ድራማ ይህን ያህል መቆየታችን አሳፋሪ ነው። በጥቅሉ አንደኛው አባል ሰብሳቢው ስህትተ ሰርተዋል ብሎ በተናገረው መሰረት ስህትቱን እንደ ስህተት ተቀብለን በማስተካከያው መሰረት ሄደናል። ከዛ በኃላ ግን ጉባዔው ሂደቱ ረጅም የነበረ ቢሆንም እጅግ ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ እስከ ምሽቱ 5 ሰዐት ድረስ ስርዐት ባለው መንገድ ቆይቷል። የጊዜው መርዘምም ሂደቱ ራሱ የፈጠረው ነበር።

ምርጫ እንደመሆኑ የመራጮች ድምፅ ምስጢራዊ ነው። ነገር ግን ምርጫውን አቋርጣችሁ ስትወጡ የወጡት የአቶ ኢሳይያስ ጂራ ደጋፊዎች የቀሩት ደግሞ ተቃዋሚዎች ናቸው የሚል አይነት ዕሳቤ እንዲፈጠር አያደርግም ? በቀጣይ አራት አመታት በሚኖረው ስራ ላይስ ችግር አያመጣም ?

ችግር አያመጣም። ምክንያቱም ምርጫው ዲሞክራሲዊው ነበር። የህግ ክፍተቱን ያመጣው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰብሰቢው ነው። ነገር ግን የወጡት በሙሉ መርጠውኛል የቀሩት ደግሞ አልመረጡኝም ማለት አልችልም። በድጋሚ ምርጫ ሲደረግም ተፎካካሪዬ ተጨማሪ 11 ድምፅ ሲያገኙ እኔ 21 አግኝቻለው። ቤቱ ውስጥ ቀርቶ የነበረውም ሰው ከ50+1 በላይ የሚሆን ነበር። እኛ ውጪ ብንቀር ኖሮም ምርጫው ይቀጥል ነበር። ስለዚህ እንደዛ ብሎ ለመምደደም ያስቸግራል። በመጨረሻ ባደረኩት ንግግርም ላለመረጡኝም ለመረጡኝም በአጠቃላይ ለጠቅላላ ጉባዔው ያለኝን ክብር ገልጫለሁ። ተፎካካሪዬን የመረጡት አካላትም ከኢሳይያስ ይሻላል ብለው አምነውበት ስለሆነ ለዚህ ክብር አለኝ። ከአሁን በኃላ ግን ፕሬዘዳንት ሆኜ ተመርጫለሁ። ስለዚህም አንድ ነን። አንድ ሆነንም ለሀገር እግር ኳስ ዕድገት እንተጋለን የሚል መልዕክት አስተላፍያለሁ። ከዚህ ውጪ እኔ የመረጠኝን ካልመረጠኝ ከፋፍዬ ለመስራት የተነሳው ሰው አይደለሁም። ይህን የሚያደርግ ስብዕናም የለየኝም። በጣም የሚቀርቡኝ ሰዎችም እኮ ድምፃቸውን ለተፎካካሪዬ የሚሰጡበት አግባብ ይኖራል ፤ ጓደኝነት እና የውስጥ ዕምነት የተለያየ ነገር ነው። በመሆኑም ማንንም መራጭ በቂም አይን አላይም። ስራው የዘርፉ ዕውቀት ብቻ ሳይሆን ፍፁም ቅንነትን ይልፈጋል። የተቋሙም ምስል በበጎ ጎኑ እየታየ አይደለም። ይህን የመቀየር ግዴታ ይጠበቅብናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ሁሉንም የጠቅላላ ጉባዓ አባላት ባማከለ መልኩ እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት ያስፈልጋል።

በተለያዩ ክለቦች አመራር ላይ ሆነው አሁን በስራ አስፈፃሚነት ከተመረጡ ሰዎች ጋር የስራ ግንኙነት ኖሮት ያውቃል። ከዚህ አንፃር አባሉቱን በምን አይነት መንገድ ይመለከቷቸዋል ?

ትልቅ ችግር ውስጥ ወደሚገኝ ተቋም ሲወጣ መልካምም መጥፎም ጎን አለው። መልካም ነገሩ ለለውጥ ተግተህ ትንሽም ቢሆን ለውጥ ስታሳይ ብዙ በጎ ጎን የሚኖረው በመሆኑ ነው። ስህተትም ስትሰራ ‘የባሰ ነው እንዴ የመጣብን’ የምትባልበት አደጋ ይኖራል። ስለዚህም ቦታው በሳል የሆነ የአመራር ሚናን የሚጠይቅ ነው። ከገቡት ሰዎች መሀከል ከሶስቱ በቀር የማውቃቸው ናቸው። አዲስ ከገቡትም ለእግር ኳሱ መልካም ነገሮችን የሰሩ ሰዎች አሉ። የሴት ተወካይም ገብተዋል። ስለ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አጠቃላይ የግል ስብዕና ማውራት አልፈልግም። ምክንያቱም ከጥቂቶቹ ጋር ነው አብረን ስንሰራ የነበረው። ነገር ግን አሁን ላይ ስራው ከግብ የሚደርሰው አብረን እንደ ቡድን መስራት ስንችል ነው። እንደቡድን ካልሰራን እና አብረን ካልቆምን ከዚህም በላይ ምሁራን የተሰበሰቡበት ቢሆን እንኳን መበላሸቱ አይቀርም። ይህን ለማድረግ ደሞ በቅንነት የተሞላ ቁርጠኛ አመራር መስጠት አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ የአመራርነት ሚና መበላሸት የሚጀምረው ወገናዊነትን ማንፀባረቅ ሲጀምር ነው። እግር ኳሱ ውስጥ የተለያዩ ሙያዎችን የሚጠይቁ ስራዎች እንደመኖራቸው እኔም የምቀመጠው ይህን አመራር እንድሰጥ እንጂ እያንዳንዱን ስራ እንድሰራ አይደለም። ሁሉም ላይ ለባለሙያው ቅድሚያ በመስጠት መስራት እና ማሰራትን ነው የምፈልገው። ሀገራችን የስፖርት ባለሙያ አላጣችም። እንዚህን በየደረጃው ያሉትን ባለሙያዎች ጭንቅላት በበጎ ጎኑ መበዝበዝ (አመሸጦ መጠቀም) ነው የምፈልገው። ያን መጠቀም የግድ ያስፈልገናል። ይህን ካደረግን እና ስራ አስፈፃሚው እንደቡድን ቆሞ ወደ ስራ ከገባ እና ስራዎች እንደ አንድ ቡድን ከተሰሩ የግል ፍላጎት እየሟሟ ነው የሚሄደው። ስለዚህ ከመነሻው እየተራረምን የስነምግባር መመሪያ ደንብ ቀርፀን ፤ የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ደንብ ላይ ያሉትን ነጥቦች በሚመጣው ጉባዔ አጠናክረን እናፀድቃለን። በዛ የህግ አግባብም እንመራለን። ከዚህ ውጪ ግለኝነት ፣ ወገናዊነት ፣ አንደኛውን አቅርቦ ሌላውን ማራቅ መታየት በሚጀምርበት ጊዜ የውስጥ ቡድኖች ስራ መፈጠር ይጀምራል። ይህ ከሆነ ደግሞ ስራ ይበላሻል። ይህንን ለማስወገድም ሁላችንም በተስማማበት አግባብ መመራት ይኖርብናል። ይህንን የአመራርነት ሚና ለመስጠት ቁርጠኛ ነኝ። ከዚህ ውጪ ግን ይህን ያህል ወጣ ያለ አስቸጋሪ ባህሪ ያለው ሰው አለ ብዬ አላስብም። ሁሉም የድርሻውን ለመውጣት ወደዚህ ቦታ እንደመጣም ነው የማስበው።