አዲሱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት የመጀመሪያ የውጪ ጉዟቸውን ዛሬ ያደርጋሉ

ባሳለፍነው እሁድ ሰመራ አፋር ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ሆነው የተመረጡት አቶ ኢሳያስ ጂራ ዛሬ ምሽት ወደ ሞሰኮ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል፡፡ በ68ኛው የፊፋ ኮንግረስ ላይ ለመሳተፍ አቶ ኢሳይያስን ጨምሮ አዲሱ የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝደንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም እና ዋና ፀሃፊው ሰለሞን ገብረስላሴ ወደ ሞስኮ ይጓዛሉ፡፡

ከ2018 ዓለም ዋንጫ መጀመር አስቀድሞ በመጪው ረቡዕ በሚደረገው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ የ2017 የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት፣ የኦዲት ሪፖርት እና 2019-2022 የሚኖረውን የፊፋ በጀት እንደሚያፀድቅ ይጠበቃል፡፡ የፍልስጤም እግርኳስ ማህበር በፊፋ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 3 እንዲሻሻል እና የብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ፔሩ፣ ቦሊቪያ፣ ቺሊ፣ ኮሎምቢያ፣ ኤኳዶር፣ ፓራጓይ፣ ዩራጓይ እንዲሁም የቬንዙዌላ እግርኳስ ማህበራት የካታር 2022 የዓለም ዋንጫ ተሳታፈ ሃገራት ቁጥር ማደግ ላይ የሚያተኩር የአዋጭነት ጥናት እንዲሰራ ያቀረቡት ጥያቄን ኮንግረሱ እንደሚወያይበትም ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ሁሉ ግን የሁሉንም ቀልብ የሳበው የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ መምረጥ ነው፡፡ ውድድሩን ለማስተናገድ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ እንዲሁም ሞሮኮ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለየትኛው ጥያቄ ድጋፏን እንድምሰጥ አሁን ላይ ግልፅ ባይሆንም በቅርግ ግዜያት ላይ ሞሮኮ በእግርኳሱ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ መስራት መጀመሯ ሃገራችን ድምጿን ለሰሜን አፍሪዊቷ ሃገር እንደምትሰጥ እንድንገምት ያደርገናል፡፡

አዲሱ የፌደሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ይህ ጉዞ የመጀመሪያው የውጪ ጉዟቸው ሲሆን ከፊፋው ኮንግረስ ቀደም ብሎ እሁድ እና ሰኞ በዛው በሞስኮ በሚካሄደው የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስብሰባ እንደሚታደሙ ተገልጿል።