ኢትዮጵያ ቡና የዳሽን ቢራውን ተከላካይ ኤፍሬም ወንድወሰንን ማስፈሙን በይፋዊ የክለቡ የፌስ ቡክ አስታውቋል፡፡
የመሃል ተከላካይ ተጫዋች የሆነው ኤፍሬም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ድንቅ አቋም ካሳዩ ተከላካዮች ግንባር ቀደሙ ነበር፡፡ በተለይም ከአይናለም ኃይሉ ጋር የፈጠሩት ጥምረት ዳሽን ቢራን በ2006 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት ክለብ አድርጎታል፡፡
በ1990ዎቹ አጋማሽ የጀመረው የኤፍሬም የእግርኳስ ህይወት በመከላከያ ፣ ሙገር ሲሚንቶ ፣ ሰበታ ከነማ ፣ ንግድ ባንክ እና ዳሽን ቢራ አድርጎ አደገኞቹ ቤት ደርሷል፡፡ ባለፈው አመት ክረምት ከንግድ ባንክ ዳሽንን የተቀላቀለው ኤፍሬም ከዳሽን ጋር የ1 አመት ውል ቢቀረውም እንደ ቡድን ጓደኛው ደረጄ ኃይሉ ሁሉ ውሉን አቋርጦ ለኢትዮጵያ ቡና የ2 አመት ኮንትራት ተፈራርሟል፡፡
በቁመቱ ረዘም ያለው ኤፍሬም ከቡድኑ ቁልፍ ተከላካይ ቶክ ጄምስ ጋር የሚፈጥረው ጥምረት ኢትዮጵያ ቡና ከቆሙ ኳሶች የሚቆጠርበት ግቦች ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡