የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 20ኛ ሳምንት (ምድብ ሀ)

20ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ትላንት እና ዛሬ በአዲስ አባባ እና በክልል ከተሞች ተደርገዋል። ባህርዳር እየመራ የነበረው ጨዋታ ሲቋረጥ ተከታዮቹ ነጥብ ጥለዋል።

ደሴ ላይ ደሴ ከተማ ከ ባህርዳር ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ባህርዳር ከተማ በ42ኛው ደቂቃ ፍቃዱ ወርቁ ባስቆጠረው ጎል እየመራ ወደ እረፍት ቢያመሩም በፀጥታ ችግር ምክንያት ጨዋታው ሳይቀጥል ቀርቷል። በጨዋታው ላይ የተፈጠሩት ጉዳዮች ላይ የኮሚሽነሩ ሪፖርት ይጠበቃል።

መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድንን የገጠመው አዲስ አበባ ከተማ በአቻ ውጤት ጨዋታውን አጠናቋል። በፈጣን እንቅሳቃሴ የተጀመረው የሁለቱ ጨዋታ የመጀመሪያው የኳስ ንክኪ እንደተደረገ በማስቆም በሁለቱም በኩል የተጫዋች ተገቢነት ላይ ክስ አስመዝግበው ጨዋታው ቀጥሏል። በመጀመሪያው 20 ደቂቃ ውስጥ ኢትዮጽያ መድኖች በግብ ሙከራ ሆነ በእንቅስቃሴ የተሻሉ ነበሩ። በተለይም በ18ኛው ደቂቃ ሀብታሙ መንገሻ በመድን በኩል መሪ የምታደርግ እድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአዲስ አበባ በኩል የተወሰደባቸውን የበላይነት ቀስ በቀስ በማስመለስ የግብ እድሎችን የፈጠሩ ሲሆን በ34ኛው ደቂቃ ፍቃዱ የሞከረው ኳስ የግቡን የላይኛውን አግዳሚ መልሳ የወጣችበት ፣ ላኪ ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት እንዲሁም ሚሊዮን ሰለሞን ከግራ በኩል የሞከረው በመጀመሪያው አጋማሽ የታዩ አጋጣሚዎች ናቸው።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ መድን ፍፁም በእንቅስቃሴ ቢበለጥም በግብ ግን ቀዳሚ መሆን ችሏል። በግማሽ አመቱ ከየካ ወደ መድን ያመራው ታምሩ ባልቻ የግቡ ባለቤት ነው። ከግቡ በኋላ መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት መድኖች በ76ኛው ደቂቃ ታምሩ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ያባከናት እድል ውጭ ምንም አይነት የጎል እድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። በተቃራኒው ላኪ ሳኒን ተክቶ የገባው ድንቅነህ ከበደ በርካታ የግብ ሙከራዎችን ያደረገ ሲሆን በተለይም 80ኛው ደቂቃ የተሻማን ኳስ በግንባሩ ቢገጨውም ከግብ ጠባቂው ጀርባ የነበረው ማሀመድ ሻፊ ሲያድንበት የተመለሰውን ኳስ ፍቃዱ በድጋሚ ቢገጨውም የግቡን አግዳሚ ገጭታ ወጥታበታለች። በ84ኛው ደቂቃ ድንቅነህ ከበደ ለአዲስ አበባ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወደ አክሱም የተጎዘው ሽረ እንዳስላሴ አቻ ተለያይቷል። በዋና ዳኛ የተመደበው ዳኛ በበረራ ምክንያት ወደ ቦታው ባለማምራቱ ተተኪ ዳኛ ከዓዲግራት በቀጥታ በመነሳት የዕለቱን ጨዋታ የመራው ሲሆን አክሱም ከተማ በፍፁም ቅጣት ምት ሽመክት ግርማ አስቆጥሮ መሪ መሆን ቢችሉም በ69ኛው ደቂቃ ልደቱ ለማ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሯል።

ለገጣፎ ላይ ለገጣፎ ለገዳዲ የካ ክፍለ ከተማን አስተናግዶ 5-0 አሸንፏል። በ2ኛው ደቂቃ በሱፍቃድ ነጋሽ እንዲሁም በ4ኛው ደቂቃ በሀብታሙ ፍቃዱ ጎሎች ገና በጊዜ መምራት የጀመሩት ለገጣፎዎች በ35ኛው ደቂቃ ፋሲል አስማማው ባስቆጠረው ጎል ወደ እረፍት ያመሩ ሲሆን በ63ኛው ደቂቃ አስናቀ ተስፋዬ እና በ79ኛው ደቂቃ ፋሲል አስማማው ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል።

ሰበታ ከተማ ከኢኮስኮ አቻ ተለያይቷል። በ4ኛው ደቂቃ ጌቱ ኃይለማርያም ሰበታን ቀዳሚ ሲያደርግ አበባየው ፋኖ ኢኮስኮን አቻ አድርጓል። ወሎ ኮምቦልቻ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትንቅንቅ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል። አውስኮድን 1-0 ባሸነፉበት ጨዋታ የብቸኛው ጎል ባለቤት ሰለሞን ሐብታሙ ነው። ፌደራል ፖሊስ ከነቀምት ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ግብ ሳይቆጠርበት የተጠናቀቀ የ20ኛው ሳምንት ብቸኛ የምድቡ ጨዋታም ሆኗል።

በዝናብ ምክንያት ገና በ3ኛው ደቂቃ ተቆርጦ የነበረው የቡራዩ ከተማ እና የሱልልታ ጨዋታ ዛሬ ቀጥሎ ቡራዩ በሚሊዮን ደምሴ እና በኢሳይያስ ታደሰ ግብ ታግዞ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። ለሱልልታ ከተማ እንዳለ ዘውገ ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል።