በቅሬታዎች የታጀበው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ተካሂደውበታል

የኢትዮጽያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሊከናወኑ መርሐ ግብር ቢወጣላቸውም የተከናወኑት ግን 2 ጨዋታዎች ብቻ ናቸው። የሊጉ የዛሬ ውሎ እና የክለቦችን ቅሬታ ያስከተሉ ክስተቶችን እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

በአምሀ ተሰፋዬ እና ቴዎድሮስ ታከለ

ኤሌክትሪክ ከ ጌዴኦ ዲላ እንዲሁም መከላከያ ከ ደደቢት በአዲስ አበባ ስታድየም እንዲጫወቱ መርመ ግብር ቢወጣም ጨዋታዎቹ ወደ አካዳሚ ሜዳ መሸጋገራቸውን ፌዴሬሽኑ ባለፈው ሳምንት ገልጾ ነበር። በዚህም መሰረት ሁለቱ ጨዋታዎች በአካዳሚ ሜዳ ዛሬ ይካሄዳሉ ተብሎ ቢጠበቅም በቦታው የተገኙት አራቱ ቡድኖች ወደ ሜዳ እንዳይገቡ በአካዳሚው በመከልከላቸው ረጅም ደቂቃዎችን በር ላይ በመጠበቅ አሳልፈው በመጨረሻም ወደመጡበት ተመልሰዋል።

የአራቱም የቡድን አባላት በተፈጠረው ክስተት ማዘናቸውን ገልፀው በሴቶች ሊግ የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ መሆን ላለመሰጠቱ እንዲህ ያለው ክስተት ግልፅ ማሳያ ነው ብለዋል። ጌዴኦ ዲላዎች በበኩላቸው አዲስ አበባ ድረሰ መጥተው ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልፀው ” ይህ ሁኔታ ሊያጋጥም እንደሚችል ከጠዋት ጀምሮ በማውቃችን ፌደረሽኑንን ለማነገር ጥረን ነበር። ነገር ግን ጨዋታው እንደሚካሄድ ነበር የገልፁልን። ” ሲሉ የተሰማቸውን ቅሬታ ለሶከር ኢትዮጽያ ገልፀዋል።

ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታም ሳይካሄድ ቀርቷል። ሀዋሳ ከተማዎች አስቀድመው በከተማዋ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለፌድሬሽኑ ደብዳቤን ልከው ጨዋታው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍላቸው በመጠየቅ ተቀባይነት ማግኘታቸውን ሲገልፁ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተቃራኒው ጨዋታው እንደሚካሄድ ፌዴሬሽኑ በመግለፁ ወደ ለጨዋታው ሀዋሳ ተገኝተው ዛሬ ፌድሬሽኑ በመደባቸው ዳኞች እና ኮሚሽነሮች አማካይነት የቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ካደረጉና ወደ ሜዳ ሄደው የተጫዋቾችን ስም ከመዘገቡ በኃላ በዛው ሜዳ ላይ ፌድሬሽን ጋር በመደወል የሀዋሳ ቡድን አልተገኘም በማለት የእለቱ ኮሚሽነር ጥቆማ ቢያደርጉም ” ጨዋታው አይካሄድም። ሀዋሳዎች ጥያቄ አቅርበው ለሌላ ጊዜ ተላልፏል። ” በሚል ሜዳ ላይ መነገሩ ቅሬታን እንደፈጠራቸው የንግድ ባንኩ  አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

“ጨዋታው አሁን አይካሄድም ተባልን። እኛ ህጉን ተግባራዊ ለማድረግ ጠብቀን ከፕሪማች ጀምሮ ተገኝተናል። ዳኞችም በእለቱ ነበሩ፤ ምክንያቱን አላወቅንም። እኛ ሜዳ ላይ ተገኝተን ነበር ዳኞቹም የነበረውን ሁኔታ መዝግበው ወስደዋል። በቀጣይ ውሳኔያቸውን እንጠብቃለን። ይሄ ነገር መኖሩ ታውቆ ቢነገረን ጥሩ ነበር። ለሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል ሲባል ሰምቻለሁ፤ ውሳኔያቸውን ግን እንጠብቃለን” ብለዋል።

የሀዋሳ ከተማ ቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ አለም ባንተ ማሞ የሀዋሳ ያልተገኘበትን ምክንያት ሲያስረዱ “ሲጀመር እኛጋ ችግሮች ነበሩ። እንኳን የሴቶቹ የወንዶቹ ቡድን ልምምድ አቁሟል። ይህን ደግሞ ለፌድሬሽኑ አሳውቀናል። በተጨማሪነትም የሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ በፊፋ አማካይነት እድሳት እየተደረገለት በመሆኑ ሜዳ ለጨዋታ ብቁም አይደለም።” ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ እና ሀዋሳ የተከሰቱትን ጉዳዮች አስመልክቶ ከፌዴሬሽኑ ባገኘነው ምላሽ ፌዴሬሽኑ ጨዋታዎቹን ለማድረግ ከአካዳሚው ፍቃድ ቢያገኝም በቦታው ሲደርሱ ፈቃጁ ግለሰብ ስልክ ባለማንሳቱ እንደተስተጓጎለ ተገልጿል። በተጨማሪም ሁለቱ ጨዋታዎች ነገ ረፋድ ላይ በባንክ ሜዳ እንደሚደረጉ ተነግሮናል። ከሀዋሳ እና ባንክ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ደግሞ ሀዋሳ ለፌዴሬሽኑ የላከው የይራዘምልኝ ደብዳቤ የወንዶቹን ቡድን የሚመለከት እንደሆነና የኮሚሽነሩ ሪፖርት እንደሚጠበቅ ተገልጾልናል።

በእለቱ በተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ቅዱስ ጊዮርጊስን 4-0 በሜዳው ሲረታ አዳማ ከተማ ወደ ይርጋለም ተጉዞ ሲዳማ ቡናን 1-0 አሸንፏል።

ድሬዳዋ ላይ ባለፈው ሳምንት በደደቢት የተረታው ድሬዳዋ ከተማ ቅ/ጊዮርጊስን ገጥሞ 4-0 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል። ገና በ2ኛው ደቂቃ ሊና መሀመድ ባስቆጠረችው ግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት ድሬዎች በ20ኛው ደቂቃ ላይ ትዝታ ፈጠነ ሁለተኛ ግብ አስቆጥራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ከዕረፍት መልስ አምበሏ ብዙሀን እንዳለ በ57ኛው ደቂቃ የተገኘውን ቅጣት ምት ወደ ግብነት ስትለውጥ 77ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተገኘችሁ አጥቂዋ ነቢያት ሀጎስ የማሴያውን ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ይርጋለም ላይ በ13ኛው ሳምንት በሜዳው በሀዋሳ አስደንጋጭ ሽንፈት ያስተናገደው አዳማ ከተማ ከሜዳው ውጭ ተጉዞ 1-0 በማሸነፍ ሶስት ነጥብን ማሳካት ችሏል። 19ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂዋ አይዳ ዑስማን በቀድሞ ክለቧ ላይ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥራለች።