ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመግባት ተቃርቦ የነበረው ሃላባ ከነማ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾቹን በሌሎች ክለቦች እየተነጠቀ ነው፡፡
ከክለቡ ባገኘነው መረጃ መሰረት ሃላባ እስካሁን 7 ተጫዋቾች ለቀውበታል፡፡ እያሱ ታምሩ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ከሪም ጀማል ወደ ወላይታ ድቻ ፣ ፈቱዲን ወደ መከላከያ ፣ ኄኖክ አዱኛ ወደ ድሬዳዋ ከነማ ፣ የብሄራዊ ሊጉ ኮብ ግብ ጠባቂ ተክለማርያም ሻንቆ ወደ አዲስ አበባ ከነማ እና አካሉ አበራ ወደ ሰበታ ከነማ ያመሩ ተጫዋቾች ናቸው፡፡
የክለቡ አሰልጣኝ አላምረው በክለቡ እጣፈንታ ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት የለቀቁባቸውን ተጫዋቾች በፍጥነት ለመተካት እንደሚጥሩ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ 7ቱ ተጫዋቾች ክለባችን ለቀዋል፡፡ ተጫዋቾቹ ከዞኑ ውድድር ጀምሮ እስከ ግማሽ ፍፃሜ ባደረግነው ጉዞ ወሳኝ ሚና የተወጡ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ በሄዱበት ክለብ መልካም ጊዜ እንዲገጥማቸው እመኛለሁ፡፡ የሄዱት ከኛ ወደተሻሉ ክለቦች በመሆኑ እድገታቸውን እናበረታታለን፡፡ ባጣናቸው ተጫዋቾች ምትክ ከብሄራዊ ሊጉ እና በሃላባ ከሚጀኙ ቡድኖች በመመልመል በቀጣዩ አመት በከፍተኛ ሊግ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆንና ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለማደግ እንሰራለን፡፡›› ብለዋል፡፡