ወላይታ ድቻ በአዲሱ የውድድር አመት አዲስ መልክ ይኖረዋል

በክረምቱ በርካታ ወሳኝ ተጫዋቾችን በሌሎች ክለቦች የተነጠቀው ወላይታ ድቻ ሌሎች 10 ተጫዋቾች በማስፈረም የቅድመ ውድድር ዘግጅቱን እያደረገ ይገኛል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመንም በርካታ አዳዲስ ፊቶች በቡድኑ ውስጥ ይታያሉ፡፡

ክለቡ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል በብሄራዊ ሊጉ መልካም አቋም ያሳዩት የሆሳዕና ከነማው ቴዎድሮስ መንገሻ ፣ የአዲስ አበባ ከነማው አማኑኤል እሸቱ ፣ የሱሉልታው ቶማስ ስምረቱ ፣ የባቱ ከነማው ዳግም እና የሃላባ ከነማው ከሪም ጀማል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በደደቢት የግራ መስመር ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው ሰለሞን ሐብቴ ወላይታ ድቻን ከተቀላቀሉ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን እንዳለ መለዮም ወደ ክለቡ ተመልሷል፡፡

ድቻ ተጫዋቾችን ከማስፈረም በተጨማሪ የበርካታ ተጫዋቾቹን ውል አድሷል፡፡ ግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ ፣ ተከላካዮቹ አናጋው ባደግ እና ተክሉ ታፈሰ ፣ አማካዩ ዮሴፍ ዴንጊቶ እና አጥቂው አላዛር ፋሲካ ውላቸውን ያደሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ክለቡ በርካታ ለውጦችን ማስተናገዱ በቡድኑ የቀጣይ አመት እጣፈንታ ላይ በርካቶች ጥያቄ እንዲያነሱበት አድርጓል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ (ወደ መከላከያ) ፣ አዲሱ ተስፋዬ (ወደ መከላከያ) ፣ አሸናፊ ሽብሩ(ወደ ኤሌክትሪክ) ፣ ተስፋዬ መላኩ(ወደ ኤሌክትሪክ) ፣ እሸቱ መና (ወደ አዳማ ከነማ) እና ዘላለም ታደለን (ወደ ሲዳማ ቡና) የመሳሰሉ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾችን ማጣቱ በእርግጥም ብዙዎች በቀጣይ አመት የቡድኑ ጉዞ ላይ ጥያቄ እንደሚፈጥር አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

‹‹ በእርግጥ ወሳኝ ተጫዋቾቻችንን አጥተናል፡፡ ነገር ግን ለሌሎች ተጫዋቾች እድል መስጠትም ወሳኝ ነው፡፡ በትቅ ደረጃ የመጫወት አቅም እያላቸው እድል ያላገኙ ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ሰብስበን ጠንካራ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በአጠቃላይ 32 ተጫዋቾችን ይዘን ዝግጅት እያደረግን ሲሆን ከተስፋ ቡድናችን ያሳደግናቸው ተጫዋቾች እና በክልል ሻምፒዮና የተመለከትኳቸውን ተጫዋቾች የሙከራ እድል አግኝተናል፡፡ እስካሁን በቡድኔ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እየተመለከትኩ ነው፡፡ ያም ሆኖ የውድድር ዘመኑ እስኪጀመር ብዙ ጥያቄዎች መነሳታቸው የማይቀር ነው፡፡ ስለ ቡድኔ የቀጣይ አመት አቋም ከማወራው በዘለለ አዲሱ የውድድር ዘመን ሲጀምር ሁላችሁም የምትመለከቱት ይሆናል፡፡ ›› ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወላይታ ድቻ በሶዶ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እያደረገ ሲሆን ከ2007 በይደር ወደ 2008 በተላለፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) መስከረም 11 ቀን 2008 ከሀዋሳ ከነማ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *