ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተጀምሯል

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ ረፋድ በባቱ ከተማ ተጀምሯል። አራት ጨዋታዎች ዛሬ ሲከናወኑ አፍሮ ጽዮን፣ ወጣቶች አካዳሚ፣ ማራቶን እና አዳማ ከተማ አሸንፈዋል።

በምድብ ሀ 03:00 ላይ በባቱ ስታድየም በተደረገው የአፍሮ ጽዮን እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ በአፍሮ ጽዮን የበላይነት እና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ግብ ባልተቀጠረበት የመጀመርያ አጋማሽ አፍሮ ጽዮኖች ከፍተኛ የበላይነት ቢኖራቸውም ድንቅ ሆኖ የዋለው የወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ አብነት ይስሀቅ ብርታት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በ10ኛው ደቂቃ አሸናፊ አክመል የሞከረውና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራም የሚጠቀሰ ነበር። 

 

በሁለተኛው አጋማሸም የተሻሉ የነበሩት አፍሮዎች በጨዋታው ኮከብ በየነ ባንጃ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ጥረታቸውን በግቦች ማጀብ ችለዋል። በ52ኛው ደቂቃ ኄኖክ አወቀ የመጀመርያውን ጎል ሲያስቆጥር ከጎራ መስመር እየተነሳ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የዋለው በየነ ባንጃ በ81ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሏል። ተጫዋቹ በ67ኛው እና 78ኛው ደቂቃ የሞከራቸውን ለግብ የቀረቡ ኳሶችም በግብ ጠባቂው አብነት ጥረት ከሽፈዋል። በዚሁ አጋማሽ በአፍሮ ፅዮኖች በኩል ጎል ሊሆን የሚችል ኳስ በድቻ ተከላካይ በእጅ ተነክቶ ወጥቶ ከዳኛ እይታ ውጪ መሆኑ የሚጠቀስ ክስተት ነበር።

በተመሳሳይ 03:00 ላይ በሼር ሜዳ በተደረገ የምድብ ለ ጨዋታ ማራቶን ሀዋሳ ከተማን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
05:00 ላይ በምድብ ሀ ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ከብልጫ ጋር 3-1 አሸንፏል። ገና የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ላይ አካዳሚዎች አከታትለው ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ጨዋታውን በቁጥጥራቸው ስር ማድረግ ችለዋል። አደም አባስ በ4ኛው ደቂቃ ቀዳሚውን ሲያስቆጥር ዳዊት ቴዎድሮስ በ6ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አስከትሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ አከዳሚዎች በመልሶ ማጥቃት ፈተና ሆነው ውለዋል። በ49ኛው ደቂቃም ከቅጣት ምት የተሞከረ ኳስ አግዳሚውን ለትሞ ሲመለስ አምበሉ ፀጋ ደርቤ አስቆጥሮ የአካዳሚን መሪነት ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል። በ63ኛው ደቂቃ ተመስገን ቢያዝን ጎል ሊሆን የሚችል ኳስ በእጁ በማስቀረቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወጣ እዮብ መርሻ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ወደግብነት ለውጦ የጊዮርጊስን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል። በ68ኛው ደቂቃ አሸናፊ ሞሼ ለጊዮርጊስ ተጨማሪ ጎል የሚያስቆጥርበትን እድል ሲያመክን በድንቅ የመልሶ ማጥቃት ሀቢብ ዛኪር ሞክሮ ግብ ጠባቂው ያወጣበት በአካዳሚ በኩለ የሚጠቀስ ነበር። 

በተመሳሳይ 05:00 ሼር ሜዳ ላይ አዳማ ከተማን ከመከላከያ ያገናኘው የምድብ ለ ጨዋታ በአዳማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

የ17 ዓመት በታች ውድድር ነገ እረፍት ሲሆን የ20 ዓመት በታች ሁለተኛ የምድብ ጨዋታዎች ረፋድ ላይ ይካሄዳሉ።

ምድብ ሀ
03:00 ደደቢት ከ ሀዋሳ ከተማ (ባቱ)

05:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ (ባቱ)

ምድብ ለ

03:00 ድሬዳዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (ሼር)

05:00 ኢትዮጵያ መድን ከ ኢትዮጵያ ቡና (ሼር)