በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እያከናወነ ይሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ለቡድኑ አይመጥኑም ያላቸውን 3 ተጫዋቾች ከቡድኑ ቀንሷል፡፡ ከተቀነሱት ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው ቤኒናዊው አጥቂ አቢኮዬ ሻኪሩ ከክለቡ መልቀቅያውን ወስዶ መለያየቱንና ሌሎቹ ተጫዋቾች በመጪዎቹ ቀናት መልቀቅያ እንደሚሰጣቸው የክለቡ የሰው ኃይል አስተዳደር አቶ ተክለ ወይን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ጠቁመዋል፡፡
‹‹ አቢኮዬ ሻኪሩ የ2 አመት ኮንትራት ይቀረው ነበር፡፡ ክለባችን እሱ ላይ ግፍላጎት ባለማሳደሩ በስምምነት ውሉን አፍርሰነዋል፡፡ እሱም ካልፈለጋችሁኝ መልቀቅ እችላለሁ ስላለ ትላንት መጥቶ መልቀቅያውን ወስዷል፡፡ ጌቱ ተስፋዬ እና ደረጄ ኃይሉ ከቡድኑ የተቀነሱ ሲሆን መልቀቅያቸውን እስካሁን አልወሰዱም፡፡ ሁለቱ ተጫዋቾች ከከልቡ ጋር በመነጋገር ላይ ናቸው፡፡›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቡና አቢኮዬ ሻኪሩን ያስፈረመው ባለፈው የክረምት የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሲሆን በአአ ከተማ ዋንጫ ላይ ግቦች በማስቆጠር ጥሩ አጀማመር አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን በፕሪሚየር ሊጉ እና ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የሚጠበቅበትን ግልጋሎት ማበርከት ሳይችል ቀርቷል፡፡ እንደ ሻኪሩ ሁሉ ደረጄም ዳሽን ቢራን ለቆ ክለቡን የተቀላቀለው ባለፈው ክረምት ሲሆን በተከላካይ አማካይነት እና ተከላካይነት የውድድር አመቱን አሳልፏል፡፡ ደረጄ ቡናን ሲቀላቀል ከዳሽን ጋር ቀሪ የአንድ አመት ኮንትራት እየቀረው ሲሆን አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቀሪ 1 አመት ኮንትራት እየቀረው ሊሰናበት ተቃርቧል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አመዛኙን ጨዋታ የተሰለፈው ግብ ጠባቂ ጌቱ ተስፋዬም ቀሪ የአንድ አመት ኮንትራት ይቀረዋል፡፡
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ ቡና ከዳዊት እስጢፋኖስ ጋር የገባው ውዝግብ በቅርቡ እልባት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ተጫዋቹ ከክለቡ የስንብት ደብዳቤ ከደረሳቸው ተጫዋቾች አንዱ የነበረ ሲሆን ሲሰናበት በነበረው ቀሪ ኮንትራት ምክንያት ዳዊት ክለቡን ለፌዴሬሽኑ ከሷል፡፡
ዳዊት ከኢትዮጵያ ቡና መልቀቅያ ባለመውሰዱ ወደ ሌሎች ለክለቦች መፈረም ባለመቻሉ ቡና መልቀቅያውን እንዲሰጠው ለፌዴሬሽን ጥያቄ ሲያቀርብ ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው ተጫዋቹ ባለፈው ክረምት ለውል ማደሻ ከተቀበለው ገንዘብ የቀሪ ኮንትራቱን ገንዘብ ካልመለሰ መልቀቅያውን እንደማይሰጥ ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡ ተጫዋቹ ደግሞ ከክለቡ ተጨማሪ ገንዘብ አለመቀበሉን ገልጧል፡፡
የክለቡ የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ አቶ ተክለወይኒ እንደሚሉት ለዳዊት ገንዘብ መክለፈላቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ለፌዴሬሽኑ ማስገባታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ ፌዴሬሽኑ ለዳዊት የከፈላችሁበትን ሰነድ በ3 ቀናት ውስጥ አቅርቡ በተባልነው መሰረት ተጫዋቹ የፈረመበት ቼክ እና ሌሎች የውል ሰነዶች አያይዘን አስገብተናል፡፡ ፌዴሬሽኑ ሁኔታውን መርምሮ በ5 ቀናት ውስጥ ለጉዳዩ እልባት ይሰጠናል ብለን እንጠብቃለን፡፡›› ብለዋል፡፡
በ2002 ክረምት ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ዳዊት እስጢፋኖስ ያለፉትን 2 የውድድር ዘመናት ክለቡን በአምበልነት መርቷል፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በዲሲፕሊን ግድፈት ምክንያት ከቡድኑ የታገደ ሲሆን ኋላ ላይ ከክለቡ መሰናበቱ የሚታወስ ነው፡፡