” ውጣ ውረዱን ተቋቁመው ለዚህ ድል ላበቁን ተጫዋቾች ምስጋና አቀርባለሁ” ገብረመድህን ኃይሌ

የዛሬ አመት ከጅማ አባ ቡና ጋር ነበርክ። ወደ ጅማ አባ ጅፋር ስትመጣ የነበረው ስሜት እንዴት ነበር ?

ጅማ አባ ቡና እያለው የነበረው ቡድን ጥሩ ነበር። በሰዓቱ ጅማ ላይ የተሰራው ነገር ጥሩ አልነበረም። ያን ማንሳት አልፈልግም። ነገር ግን በሰዓቱ በጅማ እና በአከባቢዋ ያለው ህብረተሰብ ለእግር ኳሱ ትልቅ ፍቅር ነበረው። በተለይም ለኔ የነበረው ፍቅር ልዩ ነበር። ያ ቡድን በመውረዱ በውስጤ ቁጭት ነበር። ይህን ዕድል ከጅማ አባ ጅፋር ሲመጣ ደግሞ በደስታ ነው የተቀበልኩት። ድሬዳዋ ላይ እናተም ነበራችሁ። የዛሬ አመት ያልኩት የነበረው የጅማ ህዝብ የዋህ እና ኳስ አፍቃሪ ነው። ይህን ህዝብ ማስደሰት እና መካስ አለብኝ ብዬ ስላመንኩ ነው እዛው ጅማ ላይ መስራት የፈለኩት። ጅማ ላይ አንድ ጠንካራ ቡድን መስራት እፈልጋለው ብዬ ነበር በሰዐቱ። እግዚያብሔር ብሎ ይህን በማሳካቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ስለ ተጫዋች ስብስቡ ምን ትላለህ ?

በተጫዋች ስብስቤ ውስጥ ከከፍተኛ ሊግ ፣ ከፕሪምየር ሊግ እንዲሁም ደሞ ከውጭ የመጡ  ተጫዋቹች አሉ። በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ከባድ ያደረግብን አንዱ እና ዋንኛው ምክንያት ይህ ነበር። ቡድናችን በስኳድ ጥራት ላይ ቆንጆ ነው ብለህ የምትለው አይደለም። ነገር ግን ከተጨዋቾቼ ጋር በመሆን ምን ምን ስራ ላይ መስራት እንዳለብን ተመካክረናል በቡድኑ እና በልጆቹ ላይ ቀን በጨመረ ቁጥር ለውጥ ይታይ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ስራ ነው። አንድን ስራ ደጋግመው ነው የሚሰሩት። በአጠቃላይ ተጨዋቾቼ ራሳቸውን ለኔ ሰጥተዋል።

የውውድር አመቱን እንዴት ታያዋለህ ?

ውድድር አመቱ ሁለት ገፅታዎች ነበሩት። አስቸጋሪ እና መልካም ጊዜያት። ከአስቸጋሪዎቹ ጌዜያት በመጀመሪያውቹ አራቱ ጨዋታዎች አንዱን አሸንፈን ሶስት ጨዋታ የተሸነፍንበት ይጠቀሳል። በሰዓቱ ብንሸነፍም ቡድኑ ቅርፅ ነበረው። ነገር ግን በምንሰራቸው አንዳንድ ስህተቶች ሽንፈቶቹ ገጥመውናል። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ሜዳችን ቅጣት ስላስተናገደ በሜዳችን መጫወት የሚገባንን ጨዋታ አዳማ ላይ አካሂደን አቻ ነበር የወጣነው። እንዲህ አይነቱ ነገር ሲደራረብ አመቱን ከባድ ያደርገዋል። ሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ግን ጥሩ ገፅታ ነበረው።

በቡድኑ ጠንካራ እና ደከማ ጎን ምን ነበር ?

ቡድኑ ሽንፈቶች ባገጠመው ወቅት የወሰድነውን እርምጃ እንደጠንካራ ጎን ነው የማየው። ቡድኑ ጎል ይገባበታል። ይህን እንዴት እንቅረፈው በሚል በጠረጼዛ ዙሪያ በጣም ግልፅነት በተሞላው መንፈስ ነበር የተወያየነው። ከውይይቱ መልስ ኢትዮጽያ ቡናን አሸንፈን ማንሰራራት ጀመርን። ከዛ በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሰናል። ከዚያም ቡድኑ በስነልቦናም ሆና በጨዋታ እንቅስቃሴ በጣም መሻሻል ታይቷል። በሁለተኛው የውድር አጋማሽ 14 ጨዋታ ባለመሸነፍ ነው የተጓዘው። እዚህ ላይ የአቻ ውጤቶችም አሉ። ቡድኑ ሲያሸንፍ በዛ ያለ ጎልና በጨዋታ እንቅስቃሴም በልጦ ነው።

ጅማ በዘንድሮ ውድድር አመት ከአጥቂው ክፍል ተጨማሪ ግብ ጠባቂው ላይ ያለው ጥንካሬ እንዳለ ሆኖ ዳንኤል አጃዬ በማይኖርበት ጊዜ የነበረው ክፍተት ግን እንዴት ይታያል ?

እውነት ነው። በዘንድሮ አመት የግብ ጠባቂው ዳንኤል አጃዬ ሚና ትልቅ ነበር። እሱ ያሳየው አቋም ጥሩ ነበር። እሱ በማይኖርበት ወቅት ተሰልፎ የገባው ዳዊት ያበረከተው አስታውፅዖም ትልቅ ነበር። ዳንኤል በሌለበት ወቅት 9 ጨዋታዎች ላይ የተሰለፈው ዳዊት ነበር። በዚያ ጊዜ 3 ጨዋታ ነው የተሸነፍነው። ሽንፈቱ ላይ የዳዊት የጎላ ስህተት የለም። ተጨዋችን የምትለካው በሚሰጠው አገልግሎት ነው። በዚህ ዳዊት ጥሩ ነበር። የአጃዬ መኖር ግን ምንም ጥያቄ የለውም ትልቅ እስታዋፅዖ ነበረው።

በቡድኑ ውስጥ የነበሩት አስተዳደራዊ እና መሰል ስርአቶች እንዴት ነበሩ ?

በቡድኔ በኩል የነበረ የተለየ ችግር አልነበረም። እግዜር ይመስገን በባህሪያቸው በጣም አላስቸግሩኝም። እኔ በምመራው ቡድኑ ውስጥ ሁሉንም በዕኩል አይን ነው የማያቸው። ሁሉንም እወዳቸዋለሁ። እነሱም ለኔ ክብር አላቸው። በአጠቃላይ ፍቅር አለን። እያንዳንዱን ችግር ተቻችለን እና ተማክረን እናሳልፋለን። በባህሪ በኩል ምንም አይነት የጎላ ችግር አልነበረም። በእውነት ነው የምልህ እርስ በእርስ የነበራቸው መከባበር በጣም ግሩም ነው። አንዳንዴ እግዜር ለሻምፒዮንነት የረዳን ይመስለኛል። ቡድኑ ውስጥ ያሉ ልጆች አመቱን ሙሉ በፍቅር መኖር በጣም ግሩም ነበር። ለምሳሌ ያህል ግብ ጠባቂውን  ዳዊት የመጨረሻው ሳምንት ላይ ታሞብኝ ማንን እደማሰልፍ ግራ በገባኝ ሰዓት ጨዋታው ሁለት ሶስት ቀን ሲቀረው ዳንኤል ካለበት መጥቶ ያለ ልምምድ ወደ ሜዳ ገብቶ አሸንፈን ነበር። አንዳንዴ ተጨዋች ተጎድቶብኝ ያለቦታቸው ያሰልፍኳቸው ልጆች ቦታውን በአግባቡ ሸፍነው ቡድኑን ታድገው ሲወጡ ታይቷል። በእውነት እግዜር በጣም ረድቶናል። በሌላ በኩል አስተዳደራዊ ችግር ነበር። አዲስ አዳጊ እንደመሁኑ ትንሽ ችግሮች ነበሩ። በተለይ ከክፍያ ጋር በተያያዘ። ስፖርት በባህሪው ቶሎ ቶሎ መፍትሄ የሚፈልግ ነው። ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። የአንድ ቀን ውጤት በኋላ ላይ ዋጋ ታስከፍልሀለች። በማዘጋጃ ቤቱ በጀት መተዳደሩ ይሆናል ለዚህ ያበቃው። አሁን ላይ ስፖርቱ ከዛ መላቀቅ አለበት። ይህ ሁሉንም ቡድኖች ይመለከታል። ስፖርቱ ራሱን ችሉ መቆም አለበት። ቡድኑ የተሻለ አደረጃጀት ማፅደቅ ያስፈልገዋል። ይህን ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። ፊታችን ላይ ኢንተናሽናል ጨዋታ አለብን። ከአሁኑ መስተካከል ነው ያለበት።

የወደፊት ቆይታህ ምን ይመስላል ? አንተ ብቻ ሳትሆን ተጨዋቾቹ ጭምር

እኔ አላውቀውም። ምንም ማለት አልፈልግም። እኔም ሆነ ተጨዋቾቹ ከቡድኑ ጋር ብንቀጥል ደስተኞች ነን። ነገር ግን ያሉት መሰረታዊ ችግሮች መፈታት መቻል አለባቸው።

በስተመጨረሻ ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ…

በዚህ አመት ክፉ ደግ አይተናል። በነዚህ ሁሉ ጊዜያት ውጣውረዱን ተቋቋመው ለዚህ ድል ላበቁን ተጫዋቾች ምስጋና ነው የማቀርበው። ከዛ በመቀጠል ለአሰልጣኝ ክፍሉ እና አስተዳደር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከጎናችን የነበሩትን የጅማ እና አከባቢው ህዝብ በጣም ነው የማመሰግነው። በተለይ ከመጀመሪያው እስከዛሬው ድል አብረውን ለነበሩ። በስተመጨረሻም ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ።