የ2007 የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ሰዎች /ተቋማት

ሶከር ኢትዮጵያ በ2007 አመት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ተፅእኖ ያሳረፉ ግለሰቦች እና ተቋማትን መርጣለች፡፡ በምርጫው ሂደት ላይ የሶከር ኢትዮጵያ ኤዲተሮች እና የድረ-ገፁ አንባብያን ተሳትፈዋል፡፡ በምርጫው መሰረትም ድሬዳዋ ከነማን ወደ ፕሪሚር ሊግ የመራው አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ‹‹ የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ሰው›› በሚል ተመርጣለች፡፡ በዚህም መሰረት ሶከር ኢትዮጵያ የእውቅና የምስክር ወረቀት ለአሰልጣኝ መሰረት ማኒ ታበረክታለች፡፡

 

1.መሰረት ማኒ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ያልተሞከረውን አድርገው አሳይተውናል፡፡ ሴት አሰልጣኝ ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያሳልፍ ከመሰረት ማኒ ውጪ በማንም አልተመለከትንም፡፡ 83 ክለቦችን ካሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ሴት አሰልጣኝ ይዞ የቀረበው ብቸኛ ቡድን ድሬዳዋ ከነማ ነበር፡፡ ቡድኑ ዳግም ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመመለስ የማጠቃለያ ውድድሩን በሜዳው ማድረጉ ተጠቃሚ እንዳደረገው ባይካድም ፣ ድሬዳዋ ከነማ ወደ ፕሪሚየር ሊፍ እንዲያልፍ ከሌሎች የተለየ ድጋፍ ተደርጎለታል ቢባልም ለድሬዳዋ ስኬት ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚወጣው ግን የመሰረት ማኒ ጥንካሬ ነው፡፡

እስካሁን ያልተሞከረውን በማድረግ ያሳዩን እንስቷ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ግለሰብ ተደርገው በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠዋል፡፡

2ኛ ዋልያ ቢራ

በ2006 መጨረሻ ወደ ገብያ ብቅ ያለው ዋልያ ቢራ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከባድ ተፅእኖ አሳርፏል፡፡ በሆላንዱ ዝነኛ የቢራ ጠማቂ ሄይኒከን ስር የሚገኘው ዋልያ ብሄራዊ ቡድኑን በ56 ሚልዮን ብር ለአራት አመት ስፖንሰር በማድረግ የእግርኳሱ ቢዝነስ መሪ ተዋናይ መሆን ችሏል፡፡ ድርጅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሲሸልስ እና ባህርዳር ጨዋታዎችን ሲያደርግ ለደጋፊዎች ወጪዎችን በመሸፈን የወሰደ ሲሆን በኢትዮጵያ የእግርኳስ ማርኬቲንግ አመለካከት እንዲሻሻል በትንሹም ቢሆን መንገድ ጠርጓል፡፡ ድርጅቱ ብሄራዊ ቡድኑ ከህዝቡ እና ሚድያው እንዲርቅ እጁ አለበት ተብሎ የሚወራበት ሲሆን በሲሸልስ ብዙዎችን ያበሳጨ የማስተዋወቅ ስራ ሰርቷል በሚል ይተቻል፡፡

የሆነው ሆኖ ዋልያ ቢራ በ2007 በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ተጽእኖ ከፈጠሩ ተቋማት ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋም ተብሎ ተመርጧል፡፡

3ኛ ባህርዳር ስታድየም እና የከተማው ህዝብ

አዲሱ ባህርዳር ስታድየም ከወዲሁ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፍ ጀምሯል፡፡ በ2007 በተደረጉ 6 ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች ክለብ እና ብሄራዊ ቡድኖቻችን ምንም ሽንፈት ያላስተናገዱ ሲሆን በተለይ በ3 ጨዋታዎች ባህርዳር ስታድየም በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ሰርፃለች፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኤምሲ ኡል ጋር በተደረገው ጨዋታ የተገኘው 70ሺህ የሚጠጋ ተመልካች በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ታይቶ የማይወቅ ተብሎ ተሞካሽቶ ነበር፡፡ ሰኔ 7 ከሌሶቶ ጋር በተደረገው ጨዋታ ደግሞ 100ሺህ ህዝብ ተገኝቶ የበለጠ ጉድ አሰኘ፡፡ ከሳምንት በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በቻን ማጣርያ ኬንያን ሲገጥም 107ሺህ ህዝብ ስታድየሙን መሙላቱ ሲነገር ያልተገረመ አልነበረም፡፡

በአጠቃላይ ባህርዳር ስታድየም እና የከተማው ህዝብ በ2007 የኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በርካታ ምልካም ትዝታዎች ጥለው ያለፉ ሆነው በማለፋቸው የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ተፅእኖ ፈጣሪዎች መካከል 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

4ኛ. ዮሃንስ ሳህሌ

የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ በታህሳስ 2007 የደደቢት አሰልጣኝ ሆነው ከተሸሙ ከ6 ወራት በኋላ ማርያኖ ባሬቶ ተክተው የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝነትን ተረክበዋል፡፡

ኢትዮ-አሜሪካዊው ዮሃንስ በበጎም በአሉታዊ መልኩ የእግርኳሱ መነጋገርያ ሆነው ከርመዋል፡፡ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሌሶቶን አሸንፎ ወደ ድል እንዲመለስና ኬንያን ረትቶ ወደ ቻን 2ኛ ዙር ማጣርያ እንዲደርስ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ባበረከቱት አስተዋፅኦ ቢሞገሱም በጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ እና ከሚድያ ጋር በሚገናኙበት አጋጣሚዎች ያላቸው አቀራረብ በብዙዎች ያስተቻቸዋል፡፡ አሰልጣኙ በቅርቡ ሳላዲን ፣ ናትናኤል እና ራምኬን ከቡድኑ መቀነሳቸው ከዲሲፕሊን ጉዳዮች ባለፈ ስልጣናቸውን ለማሳየት የተጠቀሙበት ነው በሚል ትችት በዝቶባቸው ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ከትንሷ ሲሸልስ ጋር አቻ ለመለያየቷ አሰልጣኙ አጥቂዎቹ ላይ ጣታቸውን ቢቀስሩም ብዙዎች ግን ዮሃንስን ተጠያቂ አድርገዋቸዋል፡፡

5ኛ. ሳሚ ሳኑሚ

በ2007 ከመሰረት ማኒ ቀጥሎ ታሪክ የሰራው ሌላው ሰው ሳሚ ሳኑሚ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ ውድድር ከተጀመረበት 1936 ጀምሮ አንድም የውጭ ሃገር ተጫዋች ያላሳካውን ገድል ናይጄርያዊው አጥቂ አሳክቶታል፡፡ በ22 ግቦች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ሳሚ በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በኮከብ ግብ አግቢነት ያጠናቀቀ የመጀመርያው የውጭ ዜጋ ለመሆን በቅቷል፡፡

6ኛ.ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ የሃገሪቱ ትልቅ ክለብ እንደመሆኑ በሃገሪቱ የእግርኳስ ጉዳዮች ላይ ሁሉ ስሙ መኖሩ የማይቀር ነው፡፡ ፈረሰኞቹ ከኤምሲ ኡልማ ጋር በባህርዳር ስታድየም ያደረጉት ጨዋታ በምስራቅ አፍሪካ የክለብ እግርኳስ ታሪክ ከፍተኛውን የተመልካች ቁጥር ያስናገደ ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡ በርካታ የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ጨዋታውን ለመመልከት ወደ ባህርዳር ከማቅናታቸው በተጨማሪ የባህርዳር ህዝብ ስታድየም በመግባት ቅዱስ ጊዮርጊስን ባለታሪክ አድርገውታል፡፡ በአጠቃላይ ከ65 እስከ 70 ሺህ ህዝብ በስታድየም ተገኝቶ የቅዱስ ጊዮርገስ እና ኡልማ ጨዋታን ተመልክቷል፡፡

ከ4 ወራት በኋላ የተመሰረተበትን 80ኛ አመት የሚያከብረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በውጭ ተጫዋቾች የቁጥር ገደብ ላይ የውዝግብ ማዕከል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ የውጭ ተጫዋቾች ቁጥር ገደብን ከ5 ወደ 3 ዝቅ ማድረጉን ቢያስታውቅም ኋላ ላይ ወደ አምስት እንዲመለስ መወሰኑ በብዙዎች በአሉታዊ መልኩ ቢነሳም የቅዱስ ጊዮርጊስን ተፅእኖ ፈጣሪነት ግን አጉልቶ አሳይቷል፡፡

7ኛ. ሎዛ አበራ

2007 ለእንስቷ ኮከብ የእግርኳስ ህይወቷን በአንድ ደረጃ ከፍ ያደረገችበት ነበር፡፡ ሎዛ ከሃዋሳ ከነማ ወደ ደደቢት በተዛወረችበት አመት ከቡድኑ ጋር የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ባለቤት ስትሆን በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስሟ ጎልቶ ተነስቷል፡፡

ሎዛ ከ20 አመት በታች ቡድኑን በአምበልነት እየመራች ካሜሩንን ድል በማድረግ ወደ ተከታዩ ዙር እንዲያልፉ ከፍተኛውን ሚና ተወጥታለች፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መነጋገርያ ቢሆንም የሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ ሆና በ5 ግብ (በማጠቃለያ ውድድር ባስቆጠረችው) ተሸልማለች፡፡ ቡድኗ ደደቢትን ለጥሎ ማለፍ ቻምፒዮንነትም መርታለች፡፡ በከፍተኛ ደረጃ መጫወት ከጀመረች ከ2 አመት ያልዘለለችው ሎዛ ከወዲሁ ከስመጥር ሴት እግርኳሰኞች ተርታ ተሰልፋለች፡፡

8ኛ. ጋቶች ፓኖም

ጋቶች ፓኖም በውድድር ዘመኑ በኢትዮጵያ ቡና እምብዛም የሚጠበቅበትን ብቃት አላሳየም፡፡ ነገር ግን በበርካቶች አእምሮ ውስጥ እንዲቀረፅ ያደረገው በብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ነው፡፡ ከሌሎች የቡድን ጓደኞቹ ገዝፎ የሚታየው ጋቶች ኢትዮጵያ ከሌሶቶ ጋር ባደረገችው ጨዋታ 1-0 ስትመራ ቆይታ የአቻነቷን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ብዙዎች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አሸናፊነት መመለስ የጋቶች ግብ እንደ መነሻ ልትቆጠር ይገባል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡

9ኛ. አዳማ ከነማ

2007 ለአዳማዎች ከውድቀት ወደ ከፍታ የተሸጋገሩበት አመት ነበር፡፡ ቡድኑ በ2006 ወልድያን አስከትሎ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መመለሱን ካረጋገጠ በኋላ በ2 የሴካፋ ውድድሮች ላይ ተሳተፈ፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ደግሞ 3ኛ በመውጣት አስገራሚ ቡድንነቱን አሳየ፡፡

ቡድኑ በ2000 ሚድሮክ ሚሌንየም ፕሪሚየር ሊግ ላይ 2ኛ ከወጣ በኋላ ይህ ስኬት ከፍተኛው ነው፡፡ ይህ ስኬት የተገኘው ግን ከታችኛው ሊግ ባደገበት አመት መሆኑ የክለቡን ፣ የተጫዋቾቹን እና የአሰልጣኙን ጠንካራ ስራ ያሳያል፡፡

10ኛ. ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ

የብራዚላዊው አሰልጣኝ ኔይደር ዶሳንቶስን ስንብት ተከትሎ ኃላፊነቱን የተረከቡት ፋሲል ተካልኝ (ዋና አሰልጣኝ) እና ዘሪሁን ሸንጋታ (ረዳት አሰልጣኝ) ቡድኑን ከውጤት ቀውስ አውጥተው የፕሪሚየር ሊጉ ቻምፒዮን አድርገውታል፡፡ ፋሲል ተካልኝም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአዲስ መልክ ከተጀመረበት 1990 አንስቶ በተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ዋንጫን ያነሳ የመጀመርያው ሰው በመሆን ታሪክ ሰሩ፡፡

የፋሲል ታሪክ ሰሪነት ፣ ቡድኑን ከነበረበት የውጤት ቀውስ ማውጣታቸውና ብዙም ያልተለመደውን አብሮ የመስራት ባህልን በማሳየታቸው ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ 10ኛ ደረጃን እነዲይዙ አድርጓቸዋል፡፡

11953359_964518590275494_7586041599788321644_o (1)

የ2007 የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ሰዎች /ተቋማት አጠቃላይ ውጤት

በምርጫው የእያንዳንዱ አንባቢ ድምፅ በ30% እና የኤዲተሮች ድምፅ 70% ተባዝቷል

(የተጠቀሱት ከ1-15 ያለውን ደረጃ የያዙት ናቸው)

ደረጃ – ስም – ነጥብ

1.መሰረት ማኒ – 58.5

2.ዋልያ ቢራ – 38.7

3.ባህርዳር ስታየምና የከተማው ህዝብ – 36.6


 

4.ዮሃንስ ሳህሌ – 20.4

5.ሳሚ ሳኑሚ – 17.7

6.ቅዱስ ጊዮርጊስ – 16.5

7.ሎዛ አበራ – 15.7

8.ጋቶች ፓኖም – 13

9.አዳማ ከነማ – 11.5

10.ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንታ – 10

11. በኃይሉ አሰፋ – 8

12. የሴቶች ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን – 7

13.ብስራት ኤፍ ኤም – 6.5

14. ምንተስኖት አዳነ – 5

ኑራ ኢማም – 5

በአምላክ ተሰማ – 5

15. ዘላለም ሽፈራው – 4.5 ሆነው ተመርጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *