መሰረት ማኒ – ብረቷ እመቤት

ሊገባደድ የሰአታት እድሜ ብቻ በቀሩት 2007 የኢትዮጵያ እግርኳስ በርካታ አነጋጋሪ ክስተቶች አስተናግዷል፡፡ ከብሄራዊ ቡድን እስከ ፕሪሚየር ሊግ ፤ ከፌዴሬሽኑ ውዝግቦች እስከ አስደንጋጭ የተጫዋቾች እና የደጋፊዎች ህልፈት ድረስ በርካታ ክስተቶች የእግርኳሱን ቤተሰብ አነጋግረዋል፡፡ የመሰረት ማኒን ያህል በርካቶችን ያስገረመ እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ አዲስ ታሪክ የፃፈ ክስተት አለ ለማለት ግን ያስቸግራል፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ የአመቱን መገባደድ አስመልክቶ በ2007 በእግርኳሳችን ላይ ተፅእኖ ያሳረፉ ሰዎችን እና ተቋማትን ከአንባቢዎቿ ጋር ስትመርጥ 1ኛ ደረጃን ያገችው በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ቡድን በመምራት የመጀመርያዋ ሴት ልትሆን ከ2 ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ የቀራት የድሬዳዋ ከነማዋ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ ናት፡፡

ድረ-ገፃችን መሰረት ማኒን የሶከር ኢትዮጵያ የአመቱ ሰው አድርጎ መምረጡ አሰልጣኟን አስደስቷል፡፡ ስለተሰጣት እውቅናም አመስግናለች፡፡ ‹‹ ይህ ክብር ስለተሰጠኝ በፈጣሪ ስም አመሰግናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ስትሰሩ የነበረውን ስራ ስከታተል ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ስለኔ የሚሰጡት አስተያየቶች የሞራል ስንቅ ሆነውኛል፡፡ ለስኬቴ እና ለስራዬ እውቅና ስለሰጣችሁኝ ከልብ አመሰግናለው›› ስትል ስለ ምርጫው ያላትን አስተያየት ሰጥታለች፡፡

የውድድር አመቱ በስኬት ይጠናቀቅ እንጂ አመቱ ለአሰልጣኝ መሰረት እጅግ ፈታኝ ነበር፡፡ 2007 የውድድር ዘመንን በሴቶች ቡድን አሰልጣኝነት ለመቀጠል ዝግጅት ላይ የነበረችው መሰረት በድንገት ድሬዳዋ ከነማን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የመመለስ ፈተናን ስትረከብ በውስጥም ሆነ በውጭ ከፍተኛ ጫና እንደነበረባት ታስታውሳለች፡፡

‹‹ ድሬዳዋ ከነማን ማሰልጠን ስጀምር በክለቡ ውስጥ በርካታ ሩርምርምታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ‹‹ እንዴት ሴት የወንድ ቡድን ታሰለጥናለች፡፡ የወንዶች ፀባይ እና ባህርይን ተረድታ ቡድኑን ወደ ውጤታማነት መምራት አትችልም›› ያሉ ብዙዎች ነበሩ፡፡ ከብቃቴ ይልቅ በሴትነቴ ምክንያት ብዙ ፈተናዎች ነበሩብኝ፡፡ በስፖርቱ አለም በተለይ በሃገራችን ቡድኖች በወንዶች ብቻ መሰልጠን እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ ያንን ነገር ለብቃት ለመወጣት እና የተጠራጠሩኝን ለማሳመን ብዙ መጣር ነበረብኝ፡፡ ›› ትላለች፡፡

አንደበተ ርቱዋ መሰረት በሃገራችን አሰልጣኞች እምብዛም ያልተለመደ የማሳመን ችሎታ እንዳላት ይነገርላታል፡፡ ይህንን ከንግግሯ መረዳትም አያዳግትም፡፡ አንደበተ ርቱእነቷ የተሰጣትን ከባድ ኃላፊነት እና በሰዎች እምነት ያለማግኘት ፈተናን በብቃት ለመወጣትም ሳይረዳት አልቀረም፡፡

‹‹ ከማሰለጥናቸው ተጫዋቾች ጋር ሁልጊዜ በጨዋታ እና በልምምድ ስለምንገናኝ ከምናገራቸው ንግግሮች ፣ ከአሰለጣጠን ፍልስፍናዬ እና ከግላዊ ባህርዬ መነሻነት እየተቀበሉኝ እና በኔ እምነት እያደረባቸው መጣ፡፡ ይህም ክለቡ ውስጥ የነበረውን ፈተና አቅልሎልኛል፡፡ ተጫዋቾቼ እንዲያደርጉ የምነግራቸውን ነገሮች ስለሚተገብሩ በክለቡ ውስጥ ያለው ከባቢ ወደ መልካም እየተቀየረ መጣ፡፡

‹‹ ያም ሆኖ ከክለቡ ውጪ የነበረው ግፊት ከባድ ነበር፡፡ ‹‹ እንዴት ሴት ሆና ወንዶችን ታሰለጥናለች፡፡ ወንዶች በገብያው ላይ ጠፍተው ነው ሴት የቀጠሩት ፣ ይህንን የሚያክል ከተማውን የሚወክል ክለብ እንድታሰለጥን እንዴት እድል ይሰጣታል ›› ስባል ነበር፡፡ ይህ ነገርም ቡድኔ እስከሚያሸንፍ ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ አሸናፊ ስሆን ነው ሲከተለኝ የነበረውን ጫና ማቅለልና የሰዎችን አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን ያስመሰከርኩት፡፡ በአጠቃላይ ሴት በዚህ ደረጃ ማሰልጠን እንደምትችል ለማሳየት ብዙ ፈተናዎችን ያሳለፍኩበት አመት ነበር፡፡ በመጨረሻ ግን በስራ እና በስኬት አሸንፌያለሁ፡፡ ›› ትላለች፡፡

በእርግጥም አሰልጣኝ መሰረት በስኬቷ የድሬዳዋ ህዝብና የሃገር ውስጥ እግርኳስ ተመልካቹን ልብ አሸንፋለች፡፡ የድሬዳዋ ህዝብ እየሰጣት ያለውን ክብርም እንባ እየተናነቃት ትናገራለች፡፡

‹‹ ከድሉ በኋላ ህዝቡ እና ክለቡ እየሰጠኝ ያለው ክብር አስደናቂ ነው፡፡ የክለቡ አመራሮች ፣ የከተማው ከንቲባ ፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር እና የድሬዳዋ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ለምጠይቃቸው ነገር ቀና ምላሽ ይሰጡኛል፡፡

‹‹ ከደቂቃዎች በፊት (ቃለመጠይቁ ከመደረጉ ደቂቃዎች በፊት) ለመገበያየት ገብያ ውስጥ እየተዘዋወርኩ ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ነጋዴዎች የምገዛቸውን ነገሮች በቅናሽ ይሸጡልኛል፡፡ በነፃ ካልወሰድሽ የሚሉኝም አሉ፡፡ በመንገድ ላይ በምዘዋወርበት ቦታ ህዝቡ የሚያሳየኝ አክብሮት የሚገርም ነው ፤ ሴቶች እንደ አርአያ እንደሚመለከቱኝ ይነግሩኛል ፤ ደጋፊዎችም በኔ ያላቸውን እምነት እና ቡድኑን የበለጠ ለመደገፍ እንደተነሳሱ እየነገሩኝ ነው፡፡ ››

አሰልጣኝ መሰረት ቡድኗን ወደ ፕሪሚር ሊግ ብትመራም ፤ ታሪካዊ አሰልጣኝ ተብላ ብትሞካሽም ፣ የደጋፊች እና የክለቡን እምነት ብታገኝም ሁሉንም ወደ ኋላ አድርጋ በአዲስ መንፈስ ለሌላ ከባድ ኃላፊነት ራሷን እንዳዘጋጀች ትናገራለች፡፡

‹‹ አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም ቡድኑን ለማጠናከር እየሰራን ነው፡፡ ቡድኑ እረፍት ላይ ስለሆነ የተጫዋቾቹ የጨዋታ መንፈስ ተቀዛቅዟል፡፡ ከእረፍት መልስ ሲሰባሰቡ የአሸናፊነት መንፈሳቸው እንዲመለስና ለጨዋታዎች ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ ይጠበቅብኛል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ የውድድር መንፈስ ውስጣቸው እንዲሰርፅ በማድረግ እንዲሁም አዲስ ከፈረሙት ጋር በማዋሃድ ክለቡን ወደ ፊት እንዲጓዝ ለማድረግ እጥራለሁ፡፡ ›› ስትል የአዲስ አመት እቅዷን ትናገራለች፡፡

ሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገፅ አሰልጣኝ መሰረት ማኒ የ2007 ትእኖ ፈጣሪ ግለሰብ ሆና በመመረጧ የተሰማትን ደስታ ትገልፃለች፡፡ የሶከር ኢትዮጵያ አባላትም አዲሱ አመት የስኬት አመት እንዲሆን ምኞቷን ትገልፃለች፡፡

 


 

ለሶከር ኢትዮጵያ ድረ-ገፅ ተከታታዮች አዲሱ አመት የሰላም ፣ የስኬት እና የደስታ እንዲሆን እንመኛለን

መልካም አዲስ አመት !

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *