የ2008 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ (ሱፐር ሊግ በሚል ቃል እየተጠራ ያለው ከፕሪሚየር ሊግ በታች የሚገኝ ሊግ፡፡ ፌዴሬሽኑ የሚጠቀምበት ይፋዊ ስም ከፍተኛ ሊግ ነው) በዚህ ሳምንት የውድድር ፕሮግራሙ እንደሚወጣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት ማብራርያ የአዲሱ የውድድር ዘመን የጨዋታ ድልድል በዚህ ሳምንት ይጀምራል፡፡
‹‹ በዚህ ሳምንት የከፍተኛ ሊግ ውድድሩ የሚጀመርበት ቀን ፣ ውድድሩ የሚደረግባቸውን ዞኖች እና የጨዋታ ድልድሉን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡ የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር ጥቅምት 18 የሚጀመር ሲሆን ከ2 ሳምንት በኋላ ለሴካፋ ውድድር ይቋረጣል፡፡ እንደ ከፍተኛው ሊግ ሁሉ በዚህ ሳምንት ውስጥ ከፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ጋር ተነጋግረን ማን ከማን እንደሚጫወት የምናሳውቅ ይሆናል፡፡ ››
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ጉዳይ የክረምቱ የመነጋገርያ ርእስ የነበረ ሲሆን የ2008 ውድድር በ14 ክለቦች እንደሚቀጥል ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡ የከፍተኛ ሊጉ ውድድር ደግሞ በ32 ክለቦች መካከል የሚደረግ ሲሆን ከፕሪሚየር ሊግ የወረዱ 2 ክለቦች በብሄራዊ ሊጉ የማጠቃለያ ውድድር የተሳተፉ 21 ክለቦች እንዲሁም ከብሄራዊ ሊጉ የዞኖች ውድድር የተሸለ ውጤት ያላቸው 9 ተጨማሪ ቡድኖች ተካተው ይደረጋል፡፡
ከድሬዳዋው የማጠቃለያ ውድድር መጠናቀቅ በኋላ የፈረሰው ሼር ኢትዮጵያን ተክቶ በከፍተኛው ሊግ የሚካፈል ተጨማሪ አንድ ቡድን ከብሄራዊ ሊጉ ወደ ከፍተኛው ሊግ አድጓል፡፡