አርዓዶም ገብረህይወት ስለ እግርኳስ ህይወቱ ይናገራል

በ1990ዎቹ አጋማሽ በኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ባሳየው የተለየ ብቃት ይታወሳል። በፕሪምየር ሊጉም ለትራንስ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና አየር ኃይል ክለቦች የተጫወተው አብዶኛው አጥቂ አርዓዶም ገብረህይወት በአሁኑ ወቅት ከሚኖርበትና ትምህረቱን እየተከታተለ ከሚገኝበት እንግሊዝ መልስ ሃገር ቤት ይገኛል፡፡

በኢንግሊዝ ሳተርደይ ሊግ እና በሚማርበት ዩኒቨርሲቲ በመጫወት ላይ የሚገኘውና በለንደን ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የስፖርት ሳይንስ ተማሪ የሆነው አርዓዶም ከማትያስ ኃይለማርያም ጋር ቆይታ አድርጓል።

በተለያዩ ክለቦች ተጫውተህ አሳልፈሀል። በኢትዮጵያ ቡና ቆይታህም የሊጉ ቻምፒዮን ሆነሀል። የትኛው ክለብ ቆይታህን ይበልጥ ቦታ ትሰጠዋለህ?

ትራንስ! የአንድ ተጫዋች ወርቃማ ጊዜ  ዋንጫ በማግኘት ብቻ ሊለካ አይችልም። ከዋንጫ በላይ በግልህ በተከታታይ ጨዋታዎች ወጥ የሆነ አቋም ስታሳይ እና ለቡድንህ የሆነ ነገር ስታበረክት እንደሆነ አምናለው። በዚህ መሰረትም በትራንስ የነበረኝ ቆይታ ወርቃማው ጊዜዬ ነው ብዬ አምናለው።

ከተጫዋችነት የተገለልከው በወጣት እድሜህ ነው። ከጉዳት ጋር የተያያዘ ነበር? 
ከእግርኳስ የመገለሌ ምክንያቱ ጉዳት አልነበረም። እንግሊዝ ሀገር የመሄድ አጋጣሚ ስላገኘሁ እና በዛውም እዛ የመጫወት የልጅነት ፍላጎቴን የማሳካት እና የመማር ዕቅድ ስለነበረኝ ነው። በታዳጊ ብሔራዊ ቡድኑ ከገጠመኝ ጉዳት በኋላ ለዓመታት መጫወቴ ምክንያቴ ጉዳት እንዳልሆነ ያሳያል።


ሳላሳካው ከእግርኳስ ተገልያለሁ ብለህ የምታምነው ህልም የትኛውን ነው?

ያላሳካሁት የምለው ውጪ ሀገር ወጥቼ አለመጫወቴን ነው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ሁለት ጊዜ ውጪ ሄዶ የመጫወት ዕድል ገጥሞኝ ነበር። አንድ ግዜ በገብረመድህን ኃይሌ ጥቆማ ደቡብ አፍሪካ ነበር ፤ በጉዳት ምክንያት ዝውውሩ አልተሳካም። ሌላ ጊዜ ደግሞ በ1995 መጨረሻ ላይ እኔ እና ታፈሰ ተስፋዬ ግብፅ ሄዶ የመጫወት ዕድል አጋጥሞን ነበር ፤ እሱም በአንዳንድ ነገሮች ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል።

እንግሊዝ ከሄድክ በኋላ ከኳሱ ጋር ምን ዓይነት ቁርኝት ነበረህ?

እንግሊዝ ሃገር እንደሄድኩ በ5ኛው ዲቪዚዮን ፋየር ዩናይትድ ለተባለ ክለብ 2 ዓመታትን ተጫውቻለው። ከዛ በኋላ ለትምህርት ዩኒቨርስቲ ብገባም ከትምርህርቱ ጎን ለጎን ለዩኒቨርስቲው ክለብ እየተጫወትኩ ነው። አሁን በስፖርት ሳይንስ ዲግሪየን ለመያዝ አንድ ዓመት ብቻ ይቀረኛል፡፡ ኳሱንም እየተጫወትኩት ሳይንሱንም እያጠናሁት ስለሆነ አሁንም ከእግር ኳስ ጋር ያለኝ ቁርኝት ጥብቅ ነው ማለት እችላለሁ፡፡

አሁን ላይ የመጫወት ፍላጎትህ ምን ይመስላል?
በፍላጎት ደረጃ አሁንም የመጫወት ፍላጎቱ አለኝ። ከሃገር ከወጣሁ በኋላም እየተጫወትኩ ነበር። አሁንም ሃገር ቤት ውስጥ ዕድሉን ካገኘው መጫወት እፈልጋለሁ። ሰውነቴ በቃኝ እስከሚለኝም እጫወታለሁ።

እየተማርከው ካለው ትምህርት አኳያ ለእግርኳሳችን ምን አዲስ ነገር ይዘህ መጥተሃል? 

አዲስ ነገር ይዤ መጥቻለው ማለት ባልችልም እኛ ሀገር ከምንከተለው አማተር አካሄድ እዛ በጣም የተለየ ፕሮፌሽናል የሆነ አካሄድ እንዳለ ተገንዝቤያለው። እግር ኳሳችን ላይ ያለው የዘልማዳዊ አካሄድ ይመስለኛል። በጥቂቱ ከታክቲክና ቴክኒክ ውጭ ሌላ ነገር ላይ እምብዛም አይሰራም፡፡ ተጫዋቾች በአካል ብቃት፣ በስነልቦና በአመጋገብ እና በመሳሰሉት የምታበቃበት መንገድ ላይ እዚህ ካለው ዘልማዳዊ አሰራር እዛ ያለው በጣም የተለየ ነው። ምናልባትም ቴክኒካሊ የኛ ሀገር ተጨዋቾች እና እዛ ያሉ ተጨዋቾች ብዙም አይራራቁ ይሆናል ፤ ነገር ግን  የተጨዋቾችን ብቃት ለማሳደግ የሚሰራው ስራ በጣም ብዙ ልዩነት አለው፡፡ ሌላው ይቅር በመሰረታዊ የታክቲክ ዕውቀትን የማስጨበጡ ስራ እንኳ እጅግ የተራራቀ ነው፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ተገንዝብያለሁ ብዬ አስባለሁ።

በቀጣይ ምን አስበሀል ?
ተመልሼ በሃገሬ መስራት እፈልጋለው፤  እግርኳስን አልጠገብኩትም። ጥቂት ዓመታት ብጫወትና ያለኝን ዕውቀት ለታዳጊዎች ባካፍል ደስ ይለኛል፡፡ እያጠናሁት ያለው ትምህርትም ኳሳችንን ከዘልማዳዊ አካሄድ አውጥቶ ወደ ተሻለ ነገር ያሸጋግረዋል ብዬ አምናለሁ እና የበኩሌን አስተዋፆኦ ለሃገሬ ኳስ ማበርከት እሻለሁ፡፡