ፌዴሬሽኑ በ2011 የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ለሚደረግባቸው ሜዳዎች የብቁነት መስፈርት አውጥቷል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን በምድብ ሀ የአንድ ሳምንት፣ በምድብ ለ የተስተካካይ ጨዋታዎች እና የሁለት ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀሩት የዋንጫ እና የመለያ ጨዋታም ገና ያልተከናወኑ መርሐ ግብሮች ናቸው። የዘንድሮው ውድድር እስካሁን ባይጠናቀቅም ፌዴሬሽኑ በቀጣዩ የውድድር ዓመት የተሻለ ውድድር ለማከናወን ክለቦች የሜዳዎች የጥራት ደረጃን እንዲያሻሽሉ የሚያሳስብ ደብዳቤ መላኩ ታውቋል።

በጉዳዩ ዙርያ የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ፀኃፊ እና የውድድር ማዘወተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፌደሬሽኑ በቀጣይ የውድድር ዓመት ሊሟሉ ይገባቸዋል በሚል በደብዳቤው ያካታተቸውን መስፈርቶች ገልፀዋል።

– በሳር የተሸፈነ የመጫወቻ ሜዳ

– ለሁለቱም ተጋጣሚ ቡድኖችና ለውድድሩ ዳኞች የተሟላ የልብስ መቀያሪያና ማረፊያ ክፍሎች

-ተመልካቾችን ከመጫወቻ ሜዳው የሚለይ አጥር እንዲሁም የመግቢያ እና መውጫዎች ላይ መዝጊያዎች እንዲኖሩት።

-የተመልካች መቀመጫዎችን ማዘጋጀት

-በተመልካች መቀመጫዎችም ሆነ በሜዳው ላይ ለስፖርታዊ ጨዋነት መባባስ መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ከድንጋይ፣ ጠጠር፣ ዱላ እና የመሳሰሉት የፀዳ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

እንደ አቶ ሰለሞን ገለፃ መስፈርቱ ቡድኖች ለሚያስመዘግቡት 1ኛ እና 2ኛ ሜዳ የሚያገለግል ሲሆን የመጀመርያዎቹ ሁለት መስፈርቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት ይደረጋል። በቀጣይ ዓመት የሚደረገው ውድድር እስኪጀምር ከሁለት እስከ ሦስት ወር ጊዜ ያላቸው በመሆኑ ቀደም ብለው እንዲዘጋጁበት በማሰብ መዘጋጀቱን ገልፀዋል። አክለውም በቀጣይ ዓመት መስፈርቱን የማያሟሉ ሜዳዎች ላይ ጨዋታ እንደማይደረግ ጠቁመዋል።

” ባደጉት ሀገራት ሜዳዎች አጥር የላቸውም። ይህ የሆነው ደግሞ ቀድሞ የማህበረሰቡ ጭንቅላት ላይ መስራት መቻላቸው ነው። በተቃራኒው ወደእኛ ስትመጣ ይህ ስራ አልተሰራም፤ በቀጣይ የምንሰራበት ይሆናል። እስከዛው ግን አጥር እና የመልበሻ ክፍል በማዘጋጀት የጨዋታ ሜዳዎችን ለጨዋታ ብቁ ማድረግ አለብን። ይህን የማይተገብሩ ቡድኖች ፌዴሬሽኑ በሚያወዳድራቸው ውድድሮች ላይ በሜዳቸው የመጫወት እድል እንደማይኖራቸው እንዲያውቁት እንፈልጋለን። በቀጣይ ዓመት ጨዋታዎች የሚከናወኑት መስፈርቱን ባሟሉት ሜዳዋች ላይ ብቻ ነው። በቅርቡ የከፍተኛ ሊግ ኮሚቴ በባለሞያዎች ወይም በሚያዋቅረው ኮሚቴ ቦታው ድረስ በመጓዝ በብቁነታቸው ላይ የሚወስን ይሆናል። አሁን ላይ ግን መስራት የሚገባቸውን ስራ መስራት እንዲጀምሩ በማለት ቀድመን ደብዳቤውን ልከናል። ” ብለዋል።