የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ሲዳሰስ…

ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ ጨዋታ በጳጉሜ ወር የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእስካሁኑ የሀዋሳ ዝግጅቱን እንዲህ ተመልክተነዋል። 

በ2019 በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚስተናገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኬንያ ፣ ጋና እና ሴራሊዮን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባሳለፍነው ዓመት በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ በመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ በጋና የ5-0 ሽንፈትን አስተናግዷል። ሽንፈቱ በሰፋ የጎል ልዩነት የመጣ በመሆኑም ቡድኑ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ሲገደድ ጋና ፣ ሴራሊዮን እና ኬንያ ደግሞ ከአንድ እስከ ሦስተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል። 

ብሔራዊ ቡድኑ ለቻን የማጣሪያ ውድድርን ካደረገ በኃላ ለወራት አሰልጣኝ አልባ ሆኖ ሰንብቶ በቅርቡ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱን በመሾም ሴራሊዮንን ለመግጠም ለ34 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅቱን ከነሀሴ 2 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ እያከናወነ ይገኛል። ቡድኑ በሐምሌ ወር መጨረሻ ወደ ዝግጅት ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም  ከልምምድ ጅማሮው በፊት ባልተለመደ መልኩ ለሁሉም ተጫዋቾች ሙሉ የህክምና ምርመራን ለማድረግ ሲባል ዘግየት ብሎ ነበር ወደ ሀዋሳ ያመራው። በ22 ቀናት የሀዋሳ ቆይታው ምን ምን እየሰራ ነው ፣ ዝግጅቱስ ምን ይመስላል ፣ የገጠሙት መልካም ነገሮች እና ተግዳሮቶችስ የሚሉትን ነጥቦች እንመልከት።

የመጀመሪያ የልምምድ ቀን

ብሔራዊ ቡድኑ ነሀሴ ሁለት ወደ ሀዋሳ በመጓዝ ሮሪ ሆቴል በተደረገለት ደማቅ አቀባበል ታጅቦ ደርሷል። ቡድኑ በዛኑ ቀን ከሰዓት 10፡00 ገደማ የመጀመሪያ ልምምዱን ሲሰራ 27 ተጫዋቾች ብቻ ተገኝተዋል። ከሳምሶን አሰፋ በተጨማሪ ከሀገር ውጪ የሚጫወቱት ሽመልስ በቀለ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ኡመድ አኩሪ እና ቢኒያም በላይ ዘግይተው የሚቀላቀሉ ተጫዋቾች በመሆናቸው ፣ ጌታነህ ከበደ ጀርመን ይገኝ የነበረ በመሆኑ እና ከነዓን ማርክነህ ወደ ሰርቢያ ያመራ ስለነበር ሳይገኙ ቀርተዋል።

የቡድኑ ቀጣይ 21 የልምምድ ቀናት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ልምምዱን መጀመሪያ ከሰራበት የመጫወቻው ኢንተርናሽናል ሜዳ በመቀጠል ያለፉትን 15 ቀናት በሰው ሰራሽ የመጫወቻ ሜዳ ላይ ሲዘጋጅ ቆይቷል። በልምምዱም ከኳስ ጋር የተያያዙ ስራዎች ፣ በአካል ብቃት ፣ በሥነ-ልቡና እና በቅንጅት ላይ አተኩረዋል። በእያንዳንዱ ተጫዋቾች ታክቲካዊ እና የቴክኒካዊ ጉድለቶችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ወሳኝ እና ጠቃሚ ተግባራትን አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና ረዳቶቻቸው በጋራ በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል።

የቡድኑ ከልምምድ ውጪ ያከናወናቸው ተጨማሪ ተግባራት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሰዓት ከሚያደርገው ልምምድ በተጨማሪ በሮሪ ሆቴል በዋና እና በጂምናዝየም ባለሙያዎች በመታገዝ ልምምዶችን ሲሰራ ቆይቷል። በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህር እና የሳይኮሎጂ ከፍተኛ ኤክስፕርት አቶ ሳሙኤል ስለሺ ላለፉት አስር ቀናት በክፍል ውስጥ ብሎም ከክፍል ውጭ በሜዳ ላይ በልምምድ ወቅት ተጫዋቾቹ በቀላሉ እንዳይረበሹ የሥነልቡና ትምህርት እና ስልጠና ሲሰጥም ሰንብቷል።

ከዚህ በተጨማሪም የአዳማ ዩኒቨርሲቲው የስነ ምግብ (NUTRITION) ባለሙያ እና መምህር ተስፋዬ ብርሀኔ አማካይነት የአመጋገብ ጥንቃቄ ላይ በሜድረግ በሜዳ ላይ ጉልበት ሊሆኑ የሚችሉ የስነ ምግብ ዓይነቶች በጥናት በታገዘ መልኩ ለተጫዋቾች ሲቀርብ ቆይቷል። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት የሚዲያ ኦፊሰር እና የትንተና ባለሙያ እንዲሁም ተጨማሪ የአካል ብቃት አሰልጣኝ ከሀገር ውስጥ ባለማግኘታቸው ከውጪ እንደሚያመጡ ተናግረው የነበረ ቢሆንም ሀያ ሁለት ቀን ባስቆጠረው የቡድኑ ቆይታ ባለሙያዎቹ እስከ አሁን አልተቀላቀሉም፡፡ በዚህም ምክንያት አሰልጣኝ አብርሀም ራሳቸው የቪድዮ ትንተናውን እየሰሩ እንደሆነ ታውቋል።

ቡድኑን የገጠሙት አዎንታዊ እና አሉታዊ ጉዳዮች

የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጳጉሜ 4 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ከሴራሊዮን አቻው የሚያናኝ የመጫወቻ ሜዳ ቢሆንም ቡድኑ በዚህ ሜዳ ላይ በቁጥር ጥቂት የሚባሉ ልምምዶችን መስራቱ አግራሞትን አጭሯል። የደቡብ ክልል የመጫወቻ ሳሩን ለመቀየር በተዘጋጀበት ወቅት ለልምምድ ወደ ሀዋሳ የመጣው ቡድኑ ሜዳው በወቅቱ በተለይ በመጀመሪያዎቹ የልምምድ ቀናት አመቺ ባለመሆኑ እና ግቻ ሳሮች በቅለውበት ስለነበረ ከነሀሴ 3 ጀምሮ ወደ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ተዘዋውሮ ልምምዶችን ከ15 ቀናት በላይ ለመስራት ተገዷል። ጠዋት ቡድኑ በጂምናዚየም ከሚወስዳቸው ስልጠናዎች በኃላ በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ከሰአት ከ10 ሰአት በኋላ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ያለፉትን አምስት ቀናት ደግሞ የስታዲየሙ ሳር በመታደሱ ምክንያት ወደ መጫወቻው የሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ሊመለስ ችሏል።

ቡድኑ ውስጥ የህክምና ክፍተቶችም ታይተዋል። በተለይ የቡድኑ ፊዚዮቴራፒስት ይስሀቅ ሽፈራው በብቸኝነት የህክምና ባለሙያ ሆነው ያለአጋር መስራታቸው ተደጋጋሚ ጉዳት በሜደ ላይ ሲያስተናግዱ የተመለከትናቸው ተጫዋቾችን ለብቻቸው ሲያክሙ መቆየታቸው በአብዛኛው ቡድኑን ይመለከት የነበረው ተመልካች ቅሬታ ሆኖ ቆይቷል። ከነዚህ ውጭ ግን የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ከተጫዋቾቹ ጋር ያላቸው መስተጋብር እጅግ አመርቂ የሚባል እና መልካም የሆነ ደረጃ ላይ መገኘቱ በበጎው የሚነሳ ነው።

ከጉዳት ጋር የተያያዙ መረጃዎች

ከመጀመሪያው የልምምድ ወቅት አንስቶ ከኢትዮጵያ ቡና የተመረጠው አጥቂው አቡበከር ነስሩ ተደጋጋሚ ጉዳቶችን በማስተናገዱ ከቡድኑ ስብስብ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል። በተጨማሪም የመቐለ ከተማው የመስመር አጥቂ አማኑኤል ገ/ሚካኤል በተደጋጋሚ በጉዳት ምክንያት በልምምድ የማይሳተፍ ሲሆን በቀጣይ ከጉዳት ጋር ተያይዞ የሚቀነስ ተጫዋቾች ሊሆን እንደሚችል ቢነገርም በዛሬው ልምምድ አገግሞ ወደ ሜዳ ተመልሷል። በሌላ በኩል በልምምድ ጉዳት አስተናግደው የነበሩት ሳምሶን አሰፋ ፣ በዛብህ መለዮ እና ታፈሰ ሰለሞን ከመጠነኛ ጉዳታቸው በመመለስ ወደ ልምምድ ገብተዋል፡፡

ከውጭ የሚመጡ ተጫዋቾች

በግብፅ የሚገኙት ሽመልስ በቀለ ፣ ዑመድ ኡከሪ እና ጋቶች ፓኖም እንዲሁም የስከንደርቡው ቢኒየም በላይ ቡድኑ ጨዋታውን ከሚያደርግበት ቀን ስድስት ቀናት ቀደም ብለው ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሏል፡፡

የዕርስ በርስ እና የወዳጅነት ጨዋታዎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለፉትን ዘጠኝ ወራት ካለአሰልጣኝ እና ከጨዋታ ርቆ እንደመቆየቱ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ማድረግ እጅጉን ያስፈልገዋል። ቡድኑ እስከ አሁን ሁለት የ90 ደቂቃ ጨዋታዎችን በሰው ሰራሹ ሜዳ ላይ አከናውኗል። በመጀመሪያው ጨዋታ ወደ ፊት በማጥቃቱ የነበረባቸውን ችግሮች በሁለተኛው የዕርስ በእርስ ጨወታቸው በሚገባ አሻሽለው መቅረብ ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪ መጠነኛ የሚባሉ የሜዳ ላይ ጨዋታዎችን ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን ከኤርትራ ጋር ነሀሴ 25 እንደሚደረግ ሲጠበቅ የነበረው የወዳጅነት ጨዋታ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ከዝግጅት በመራቁ እና ምላሽ ባለመገኘቱ ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። ሆኖም ለካሜሩን እና ቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድኖች በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ እና በፌዴሬሽኑ ትብብር በተደረገ ጥሪ የምስራቅ አፍሪካዋ ሀገር ምላሽ በመስጠቷ የፊታችን ዕሁድ ከቀኑ በ10 ሰዐት በሀዋሳ ዓለም ዓቀፍ ስታዲየም ዋልያዎቹ ከብሩንዲ አቻቸው ጋር የሚጫወቱ ይሆናል። ከጨዋታው በኃላም አሰልጣኙ የመጨረሻ 25 ተጫዋቾችን የሚለይ ይሆናል፡፡ የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በነገው እለት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ ሲጠበቅ በሴንትራል ሆቴል አርፎ ከነገ በስቲያ ልምምድ አድርጎ እሁድ የወዳጅነት ጨዋታው ይካሄዳል ተብሏል።

የዛሬ ውሎ አዳዲስ ነገሮች

በዛሬው የልምምድ መርሐ ግብር አማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ሳምሶን አሰፋ ወደ  ልምምድ ተመልሰዋል።  በዛብህ መለዮ፣ ዐወት ገብረሚካኤል እና ተመስገን ካስትሮ በአንፃሩ በጉዳት በዛሬው ልምምድ ላይ ያልነበሩ ናቸው። በኃይሉ አሰፋ፣ እስራኤል እሸቱ፣ አቤል ማሞ እና አህመድ ረሺድ መጠነኛ ጉዳት ስላለባቸው በግላቸው ሲሰሩም ተመልክተናል።