” ሁላችንም ትኩረት ያደረግነው ማሸነፍ ላይ ነው ” ቢንያም በላይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በነገው እለት ከሴራሊዮን ጋር የምድበ ስድስት ሁለተኛ ጨዋታውን ያከናውናል። ቡድኑ ለአንድ ወር ያህል ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ከሳምንቱ መጀመርያ ወዲህ በውጪ ሀገራት የሚጫወቱ አራት ተጫዋቾች ቡድኑን ተቀላቅለው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል። ከውጪ ከመጡት ተጫዋቾች መካከል በአልባኒያው ስከንደርቡ ኮርሲ እየተጫወተ የሚገኘው ቢንያም በላይ ከብሔራዊ ቡድኑ እና ከክለብ ህይወቱ ጋር የተያያዘ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ብሔራዊ ቡድኑን ከጥቂት ቀናት በፊት ነው የተቀላቀልከው። እንዴት አገኘኸው ?

ብሔራዊ ቡድኑን ከተቀላቀሉኩኝ አራት ቀኔ ነው። መልካም ጌዜንም እያሳለፍኩ ነው።

ወደ ብሔራዊ ቡድን ዘግይተህ መቀላቀልህ ተፅእኖ አልተፈጠረብህም ?

አዎ አጭር ጌዜ ነው፤ ምክንያቱም ውድድር ላይ ነበርኩ። በፊፋ ህግ መሰረት መቀላቀል የምትችለው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህ ደግሞ ለሁሉም የሚሰራ ነው፤ የሴራሊዮን ቡድን ተጨዋቾችንም ያካትታል። ምንም ምክንያት አያስፈልገንም። የሴራሊዮን ቡድንን ተጋግዘን ማሸነፍ ነው ያለብን። እግዚአብሔር ይጨመርበት ሁሉም የተሰጠውን ኃላፊነት ከተወጣ ጥሩ ቀን ይሆንልናል ብዬ አምናለሁ።

ከአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድን በኋላ በአሰልጣኝ አብርሃም የሚመራው ቡድን ውስጥ ተካተሀል…

ከብሔራዊ ቡድን ራቅ ብዬ ነበር። ምክንያቱ በአሰልጣኝ አሸናፊ ጊዜ ስላልነበርኩኝ ነው። ተመልሼ ወደ ብሔራዊ በመቀላቀሌ ደስ ብሎኛል። በዮሐንስ ሳህሌ ጌዜ ቡድኑ ውጤታማ ነበር። ለቻን አልፈናል፤ እንዲሁም ሴካፋን በሶስተኛ ደረጃ ነው ያጠናቀቅነው። በአሰልጣኝ አብርሀምም ቆንጆ ጊዜ እያሳለፍን ነው። እግዚአብሔር ተጨምሮበት በፊት ከነበረው ብሔራዊ ቡድን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አስበናል።

የኢትዮጽያ ብሔራዊ ቡድን በጋና ሽንፈት አጋጥሞታል። የሴራሌዮን ቡድን ደግሞ ኬንያን አሸንፎ ነው የመጣው። ቡድናችን ከምድቡ 4ኛ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ይህን እንዴት ታይዋለህ ?

ያው እኔ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ትኩረት ያደረግነው ማሸነፍ ላይ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው ውጤት ተፅዕኖ አይፈጥርብንም። ምክንያቱ ያኛው አልፏል። ይህ ስብስብ እንዳ አዲስ ነው የተዋቀረው። አዲስ ተስፋ እና ራዕይ ይዘን ነው የተነሳነው። ከእግዚአብሔር ጋር እናሳካዋለን።

እንደ ኢትዮጵያዊ በአልባንያ ሊግ መጫወትህን እንዴት እንዴት ታያዋለህ ?

አጋጣሚውን ማግኘቴ ዕድለኛ ያስብለኛል። ነገር ግን ጠንካራ ሰራተኛም ነበርኩኝ። ያገኘሁትን ዕድል ተጠቅሜበታለሁ። ቀላል ነገር አይደለም አውሮፓ ውስጥ መጫወት። እዛ ስትጫወት ትልልቅ ተጫዋቹች ጋር የመገናኘት ዕድል ይኖርሀል። ለኔ ባጠቃላይ መልካም ነገር ነው። ሊጋችንም ጥሩ ነው። ኢትዮጵያን ተጨዋቾች ላይ ዕምነት እንዲኖራቸው እና ሌሎች የኔ አይነት ዕድል ያገኙ ጓደኞቼ ጠንክረን በመስራት ለተጨማሪ ተጨዋቾች ዕድሉን ማስፋት መቻል አለብን።

ከጀርመን እስከ አልበንያ ጉዞህ እንዴት ነበር?

በመጀመሪያው ሙከራ ወደ ጀርመኑ ቦርስያ ሞቺጋልባ ያመራው ሲሆን ወደ ኢትዮጽያ ተመልሺያለሁ ምክንያቱም እነሱ ሊያጫውቱኝ ያሰቡት በወጣቶች አካዳሚ ነበር። በጀርመን ህግ የአውሮፓ ዜግነት የሌለው ተጨዋች በዛ አካዳሚ ውስጥ መጫወት ስለማይችልም ነበር። በቀጣይ ሁለት ሶስት ቦታዋች ካመራው ባኃላ በአልባንያው ክለብ እስክንድርቡ መቀመጪያን አድርጊያለሁ።

በአውሮፓ መድረክ ላይም የኢሮፓ ሊግ ተሳታፊ ነበርክ። ውድድሩ እንዴት ነበር ?

እግዚአብሔር ይመስገን ድሮ በቴሌቪዥን የማየውን ውድድር ላይ በአካል በመገኘቴ። እንዲሁም መጫወት መቻሌ ያለው ስሜት ከባድ ነው። ምክንያቱም ደግሞ በፊት የነበርኩበትን ስለሚያስታውሰኝ ነው። ለኔ ከባድ ውድድር ነበር። እንደ እስክንድሪያ ክለብ ታሪክ መስራት ችለናል። በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል።

ዘንድሮ ቡድንህ በተደጋጋሚ ዋንጫ አንስቷል። ስኬቱን እንዴት ታየዋለህ ?

በጣም ደስ ይላል። ሶስት ዋንጫዎችን ማግኘት የቻልነው ዘንድሩ ነው። በሊጉ በጣም ነግሰን ነበር። በተከታታይ ቻምፒዮን ስትሆን ያለህበትን ደረጃ ያመልክታል።

ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ተጨዋች ውጪ ወጥተው እንዲጫወቱ የምትለው ነገር ካለ ?

የተሻለ ነገር የፈለገ ሰው መስራት አለበት። ስህተቶቹን ሁሌም ማረም አለበት። በቴክንኩ በኩል እኛ ኢትዮጽያን ብዙ ችግር የለብንም። ፕሮፊሽናል እግርኳስ የሚፈልገውን ማሟላት ከቻልን ወደፊት ብዙ በአውሮፓ መድረክ ላይ መታየት እንችላለን።

ቀጣይ እቅድህ ምንድን ነው?

እኔ ወጣት ነኝ። ወደፊት ከዚህም የተሻለ ነገር እንደሚኖረኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ይህ የኔ የቤት ስራ ነው። አሁንም ገና ብዙ መስራት አለብኝ። አምናለሁ ያኔ ከዚህም የተሻለ ነገር ይመጣል ከፈጣሪ ጋር።