ሴንትራል ሀዋሳ የታዳጊዎች ውድድር ትላንት ተጠናቀቀ

ሀዋሳ በሚገኘው ሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል አዘጋጅነት የሚከናወነው የታዳጊዎች ውድድር ለ10ኛ ጊዜ ከነሀሴ 6 ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቶ በትላንትናው እለት ተጠናቋል። 

በመዝጊያው ስነ-ስርዓት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ ም/ል ፕሬዝዳንት ኮ/ል አወል አብዱራሂም፣ የቴክኒክ ኮሚቴ ኃላፊው ኢ/ር ሰውነት ቢሻው፣ የሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍትህ ወልደሰንበት እና የዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ትግል ግዛው በክብር እንግድነት ተገኝነተው የፍፃሜ ጨዋታው ተከናውኗል። ከዚህ ውድድር የተገኙትና በሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ እና ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ምንተስኖት እንድሪያስም በስፍራው ተገኝተዋል። 

በሁለት የእድሜ እርከኖች ከ15 ዓመት በታች 26 ቡድኖች፣ በ13 ዓመት በታች 22 ቡድኖች ሲካፈሉበት በቆየው በዚህ ውድድር በ15 ዓመት በታች ፍፃሜ ሀዋሳ ከተማ ከ ህይወት ብርሀን መደበኛውን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ አጠናቀው በመለያ ምቶች ህይወት ብርሀን 4-3 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። በ13 ዓመት በታች ደግሞ ትዕግስት አኮ ፕሮጀክትን 2-0 አሸንፎ ዋንጫ አንስቷል። 

በመዝጊያው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ባደረጉት ንግግር ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። ” ይህ ለኛ በታዳጊዎች ላይ ስራዎች እንድንሰራ ምሳሌ የሚሆነን ነው። በቅርቡ ሴካፋ ላይ የተጫወቱ ተጫዋቾችን አፍርቷል ሲባል ስሰማ እና ውደድሩን መጥቼ በአካል ስከታተለው ለውስጤ ደስታን ፈጥሯል። በቀጣይ ውድድሩ የተጠናከረ እንዲሆን ድጋፍ የምናደርግ ይሆናል።” ብለዋል።

ውድድሩን በፋይናንስ የሚደግፈው ሀዋሳ ሴንትራል ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ፍትህ ወልደሰንበት በበኩላቸው ለታዳጊዎች ሁሉም አካላት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልፀዋል። ” ይህን አይነት ተግባር ብቻችንን የምናደርገው አይደለም። ባለሀብቶች፣ መንግስት እና ስፖርት የሚወድ ሁሉ ሊደግፈው የሚገባ ነው። እንዲህ አይነት ውድድር ለእግርኳሳችን ዋስትና የሚሆን ትልቅ ውድድር ነው። እኛም አንድ እርሾ ማስቀመጥ አለብን በሚል ነው ውድድሩን የምናካሂደው። ”

ውድድሩን በአስተባባሪነት እና ኮሚቴ ሰብሳቢነት የሚመራው የቀይ ቀበሮዎቹ አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ስለውድድሩ አስተያየቱን ሰጥቷል። “በታዳጊዎች እግርኳስ ላይ እንድሰራ ያደረገኝ ይህ ውድድር ነው። እንዲህ አይነት ውድድሮች ታዳጊዎችን ለማፍራት እና መሰረት ለመጣል ወሳኝ በመሆኑ ትኩረት ልንሰጠው ይገባል። ” ብሏል።