ዋልያዎቹ ለኬንያው ጨዋታ መስከረም 20 ይሰበሰባሉ

ማክሰኞ መስከረም 8 ቀን 2011

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ2019 የካሜሩኑ አፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታ ዝግጅቱን ከመስከረም 20 ጀምሮ ያካሂዳል። ጨዋታው በባህር ዳር ስታድየም እንደሚከናወን ሲረጋገጥ የተጠሩ ተጫዋቾች ዝርዝርም ይፋ ተደርጓል። 

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታ ኬንያን የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን የሚያደርግበትን ከተማ ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ እንዳልቀየረ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሳውቋል። ፌዴሬሽኑ ለሚድያዎች ይፋ ባደረገው መግለጫ እንዳስታወቀው ከኬንያ የሚደረገው ጨዋታ በታቀለት መርሐ ግብር መሠረት መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ባህር ዳር ስታዲየም ላይ ከቀኑ 10:00 የሚካሄድ ይሆናል።

በአብርሀም መብራቱ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ሴራሊዮንን ሀዋሳ ላይ 1-0 ከረታ በኋላ ለእረፍት የተበተነ ሲሆን የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች መስከረም 19 ከተጠናቀቁ በኋላ ተጫዋቾቹ ተሰባስበው ከመስከረም 20 ጀምሮ ለኬንያው ጨዋታ ዝግጅት እንደሚጀምሩ ተገልጿል። አሰልጣኝ አብርሀም ለሴራሊዮን ጨዋታ ዝግጅት ጠርተዋቸው ከነበሩ ተጫዋቾች ውጪ ለሽመክት ጉግሳ ጥሪ የተደረገለት ሲሆን በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሆኖ የነበረው ሰላሀዲን በርጌቾ፣ ለሙከራ ወደ ሰርቢያ በመጓዙ ምክንያት ከዝግጅት ውጪ የነበረው ከነዓን ማርክነህ እንዲሁም ከመጨረሻ 23 ተጫዋቾች ስብስብ ውጪ ሆኖ የነበረው ተመስገን ካስትሮ ወደ ስብስቡ የተመለሱ ናቸው።

ለኬንያው ጨዋታ የተጠሩት 26 ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡-

ግብ ጠባቂዎች (3)

ሳምሶን አሰፋ (ድሬዳዋ ከተማ)፣ ተክለማርያም ሻንቆ (ሀዋሳ ከተማ)፣ ጽዮን መርዕድ (አርባምንጭ ከተማ)

ተከላካዮች (9)

ሳልሀዲን ባርጌቾ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ አስቻለው ታመነ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ሙጂብ ቃሲም (ፋሲል ከነማ)፣ አንተነህ ተስፋዬ (ድሬዳዋ ከተማ)፣ አብዱልከሪም መሀመድ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ኄኖክ አዱኛ  (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ አምሳሉ ጥላሁን (ፋሲል ከተማ)፣ አህመድ ረሺድ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ተመስገን ካስትሮ (ኢትዮጵያ ቡና)

አማካዮች (9)

ጋቶች ፓኖም (ኤል ጎውና)፣ ሙሉዓለም መስፍን (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ናትናኤል ዘለቀ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ አማኑኤል ዮሀንስ (ኢትዮጵያ ቡና)፣ ቢኒያም በላይ (ስከንደርቡ ኮርሲ)፣ ሽመልስ በቀለ (ፔትሮጀት)፣ ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)፣ በኃይሉ አሰፋ (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ከነዓን ማርክነህ (አዳማ ከተማ)

አጥቂዎች (5)

አዲስ ግደይ (ሲዳማ ቡና)፣ አቤል ያለው (ቅ/ጊዮርጊስ)፣ ዑመድ ኡኩሪ (ስሞሀ)፣ ጌታነህ ከበደ (ደደቢት)፣ ዳዋ ሁቴሳ (አዳማ ከተማ)