ሀዋሳ ከነማ ከ ወላይታ ድቻ ፡ የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ሀዋሳ ከነማ ከ ወላይታ ድቻ

ማክሰኞ መስከረም 11 ቀን 2007

11፡00 አዲስ አበባ ስታድየም


 

የማክሰኞው 2ኛ ፍልሚያ ሁለቱን የደቡብ ክለቦች ያፋጥጣል፡፡ ድቻ ለመጀመርያ ጊዘ የፍፀሜ ተፋላሚ ለመሆን በማለም ሀዋሳ ከነማ ደግሞ ለ7 አመት ከራቀው ፍፃሜ ጋር በድጋሚ ለመናኘት አልመው ይጫወታሉ፡፡

ወቅታዊ ሁኔታ

ሀዋሳ ከነማ በቡድኑ ላይ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ሳያደርግ የውድድር ዘመኑን ይጀምራል፡፡ ባለፈው አመት ኣማሽ ቡድኑን የተረከቡት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ዘንድሮ ከክረምቱ ጀምሮ ቡድኑን በሚፈልጉት መልኩ ለማዘጋጀት እድል አግኝተዋል፡፡

አሰልጣን ውበቱ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው በሚፈልጉት ደረጃ ባይገኝም ለጨዋታው እንደተዘጋጁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ዝግጅት የጀመርነው ዘግይተን ቢሆንም ተጫዋቾቼ በመልካም አቋም ላይ ይገኛሉ፡፡ ጊዜ ቢፈልግም ቡድኑን ለማዋሃድ በተቻለ መጠን እየሰራን ነው፡፡ ›› ብለዋል፡፡

ሀዋሳ ከነማ በሀዋሳ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 2 የወዳጅነት ጨዋታዎችን አድርጎ አንዱን በሽንፈት ሌላኛውን በድል ተወጥቷል፡፡ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ የሚመጣው ሰኞ ሲሆን በማግስቱ ከድቻ ጋር ጨዋታውን ያደርጋል፡፡

ወላይታ ድቻ ወሳኝ ተጫዋቾችን በማጣቱ በአዲሱ አመት ለውጦች አድርጎ መጥቷል፡፡ ክለቡ የአሰልጣኙ መሳይ ተፈሪን ኮንትራት ያደሰ ሲሆን ከብሄራዊ ሊግ ተጫዋቾችን አምጥቷል፡፡ በሶዶ ከተማም የቅድመ ውድድር ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የቡድኑ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት በርካቶች ቡድናቸው ላይ ጥያቄ ቢያነሱም የውድድር አመቱ ሲጀመር ጥያቄዎችን የሚመልስ ቡድን እንዳዘጋጁ ተናገረዋል፡፡

‹‹ ወሳኝ ተጫዋቾች በመልቀቃቸው ቡድናችን ላይ ጥያቄ የሚያነሱ በርካቶች ናቸው፡፡ ነገር ግን ያስፈረምናቸው እና ከወጣት ቡድኑ ያሳደግናቸው ተጫዋቾች እምቅ ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ለጨዋታውም ተዘጋጅተናል፡፡ ››

ወላይታ ድቻ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው የዝግጅት ጨዋታ በአርባምንጭ ከነማ 2-1 ተሸንፏል፡፡ ቡድኑ ትላንት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ዛሬ በሱሉልታ ልምምድ ሰርቷል፡፡ ነገም ልምምድ ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ጉዳት እና ቅጣት

በሀዋሳ ከነማ በኩል ተከላካዩ አዲስአለም ተስፋዬ በቅጣት ምክንያት የማክሰኞው ጨዋታ ያልፈዋል፡፡ ቡና ላይ ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ቡድኑን ለግማሽ ፍፃሜ ያበቃው ተመስገን ተክሌ እና አጥቂ አማካዩ ታፈሰ ሰለሞን ደግሞ በጉዳት አይሰለፉም፡፡

በወላይታ ድቻ በኩል ከሃላባ ከነማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት የፈረመው አብዱልከሪም ጀማል በጉዳት ጨዋታውን አያደርግም፡፡

 

ቁልፍ ፍጥጫዎች

ቴዎድሮስ መንገሻ ከ ግርማ በቀለ

በሆሳእና ከነማ የብሄራዊ ሊግ ጉዞ ላይ ድንቅ አቋም ካሳዩ ተጫዋቾች ግንባር ቀደሙ ቴዎድሮስ መንገሻ አንዱ ነበር፡፡ ፈጣን እና የማይገመት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችለው ቴዎድሮስ ለሌሎች ተጫዋቾች የግብ እድል በመፍጠር በኩልም ድንቅ ነው፡፡ በአንፃሩ የሀዋሳ ከነማው ተከላካይ ግርማ የከፍተኛ ልምድ ባለቤት ከመሆኑ በተጨማሪ ጠንካራ ሸርተቴዎችን መውረድ የሚችል ተከላካይ ነው፡፡ ከሆሳእና ከነማ የፈረመው ቴዎድሮስ በዚህ ጨዋታ ከተሰለፈ ባለ ክህሎቱ አጥቂ ከጠንካራው ተከላካይ የሚያደርጉት ፍልሚያ ትኩረት የሚስብ ይሆናል፡፡

በረከት ይስሃቅ ከ ተክሉ ታፈሰ

በረከት ይስሃቅ ከ3 አመታት ቆይታ በኋላ ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡ በማክሰኞው ጨዋታ ተመስገን የማይሰለፍ በመሆኑ የአጥቂ መስመሩን ይመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ተክሉ ታፈሰ ደግሞ በዝውውር የሳሳው የወላይታ ድቻ የተከላካይ መስመርን የመምራት ኃላፊነት ወድቆበታል፡፡ ከበረከት ይስሃቅ እና ጋዲሳ መብራቴ የሚመጡበትን ጥቃት ለመመከት ከተክሉ ብዙ ይጠበቃል፡፡

 

እንዴት መጡ?

ሀዋሳ ከነማ በጥር ወር አጋማሽ አበበ ቢቂላ ላይ ከደደቢት ጋር ባደረገው ጨዋታ መደበኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ 2-2 አጠናቆ በመለያ ምቶች 3-2 በማሸነፍ ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ በሩብ ፍፃሜው ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን በተመስገን ተክሌ ሁለት ግቦች ታግዞ 2-1 በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ተመስገን በወቅቱ ያስቆጠራቸው ግቦች የግል ክህሎቱንና የቦታ አያያዝ ችሎታውን ያሳየባቸው ነበሩ፡፡

ወላይታ ድቻ አበበ ቢቂላ ላይ አዳማ ከነማን 2-1 በማሸነፍ ወደ ሩገ,ብ ፍፃሜው ሲያልፍ በሩብ ፍፃሜው ኤሌክትሪክን በአላዛር ፋሲካ የጭንቅላት ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡

 

እውነታዎች

ሀዋሳ ከነማ ድቻን አሸንፎ ለፍፃሜ ካለፈ ከ2000 በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይሆናል፡፡ በ2000 ሀዋሳ ከነማ በፍፃሜው በኢትዮጵያ ቡና 21 ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል፡፡

ወላይታ ድቻ ይህንን ጨዋታ አሸንፎ ፍፃሜውን ከተቀላቀለ በ6 አመት ታሪኩ (የተመሰረተው በሰኔ 2001 ነው) የመጀመርያው ይሆናል፡፡

ወላይታ ድቻ ወደ ፍጻሜው ካለፈ ከ18 አመት በኋላ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ያለፈ የመጀመርያው የወላይታ ዞን ቡድን ይሆናል፡፡ በ1989 ወላይታ ቱሳ የኢትዮጵያ ዋንጫን ካነሳ በኋላ የወላይታ ዞን ቡድን ዋንጫ ማንሳት ቀርቶ ለፍፃሜ ደርሶ አያውቅም፡፡

ይህንን ዋንጫ ሀዋሳ ከነማ አንድ ጊዜ በ1997 ባንክን አሸንፎ ሲያነሳ ወላታ ድቻ ዋንጫውን አሸንፎ አያውቅም፡፡ መከላከያ (በኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጦር ኃይሎች በደርግ ዘመን ደግሞ ምድር ጦር የሚል ስያሜ ነበረው) ለ12 ጊዜያት ያህል በማሸነፍ ቅድሚያውን ሲይዝ ቅዱስ ጊዮርጊስ (በደርግ ዘመን አዲስ ቢራ) 10 ጊዜ በማሸነፍ ይከተላል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና (ንጋት ኮከብ እና ቡና ገበያ) 5 ጊዜ ኤሌክትሪክ (መብራት ኃይል) ደግሞ 4 ጊዜ ይህንን ውድድር አሸንፈዋል፡፡

 

ያለፉት 3 የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎች ውጤቶች

ሀዋሳ ከነማ – ተሸነፈ – አቻ (በመለያ ምቶች አሸነፈ) – አሸነፈ

ወላይታ ድቻ – ተሸነፈ – አሸነፈ – አሸነፈ

 


ምንጭ ካልጠቀስን በቀር በድረ-ገፁ ላይ የሚወጡ ፅሁፎች በሙሉ የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ፅሁፉን ለህትመት ፣ ለኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎች እና ለድረ-ገፆች ሲጠቀሙ ምንጭ በመጥቀስ ለስራችን ዋጋ ይስጡ

እናመሰግናለን!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *