ጅማ አባ ጅፋር የዲዲዬ ለብሪን ዝውውር አጠናቋል

ዲዲዬ ለብሪ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የቀረውን የአንድ ዓመት ውል በማፍረስ ወደ ጅማ ማቅናቱ ተረጋግጧል።

የሊጉ አሸናፊ ከሆነ በኋላ በነበሩት ቀጣይ ወራት ቁልፍ ተጨዋቾቹን ለማጣት የተገደደው ጅማ አባ ጅፋር ቀስ በቀስ ክፍት ቦታዎቹን በመሸፈን ላይ ይገኛል። ከነዚህም መካከል አይቮሪኮስታዊው አጥቂ ዲዲዬ ለብሪ ወደ ሻምፒዮኖቹ ቤት ለማምራት መስማማቱ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ዝውውሩን አጠናቆ የአባ ጅፋር ተጨዋች መሆኑ ተረጋግጧል።

ክለቡ አምና ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ የጨረሰው ኦኪኪ አፎላቢን እና ሌላኛውን አጥቂ ተመስገን ገ/ኪዳንን እንዲሁም ሳምሶን ቆልቻ እና  እንዳለ ከበደን ከለቀቀ በኋላ ሁነኛ የቦታው ተተኪ ያስፈልገው ነበር። አምና ወደ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመምጣት በሊጉ የመጀመሪያ የውድድር ዓመት ያሳለፈው ዲዲዬ ለብሪ ከካሉሻ አልሀሰን ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር መልካም እንቅስቃሴ ማድረጉ ይታወሳል። በመሆኑም ዘንድሮ በሻምፒዮኖቹ ቡድን ውስጥ ያለውን የፊት አጥቂ ክፍተት እንደሚሞላ ታምኖበት ከቀድሞው ክለቡ ጋር የቀረውን የአንድ ዓመት ውል በማፍረስ በሁለት ዓመት ውል ወደ ጅማ አምርቷል።